“ከሽብር ቡድኑ ነፃ በሚሆኑ አካባቢዎች ለሕዝቡ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማት በአፋጣኝ ሥራ እንዲጀምሩ ይደረጋል” የጤና ሚኒስቴር

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴርና የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች በሸድሆ መቄት አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል በመገኘት በአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን የተዘረፉና የወደሙ ንብረቶችን ተመልክተዋል።የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጄ ዱጉማ (ዶክተር) ምልከታው በሆስፒታሉ ላይ የደረሰውን ጉዳት በመለየት አስፈላጊውን ቁሳቁስ ለማሟላት ይረዳል ብለዋል።

“በምልከታችን የሸድሆ መቄት አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል በደረሰበት ዘረፋና ውድመት አገልግሎቱን ከዜሮ መጀመር እንዳለበት ተገንዝበናል” ነው ያሉት ። ዶክተር ደረጄ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሆስፒታሉ ቁሳቁስና መድኃኒቶች ተዘርፈዋል፣ ወድመዋል ብለዋል። በገንዘብ ሊተመን የማይችል የመረጃ ሀብትም እንደወደመ ጠቁመዋል።ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት በአጭር ጊዜ ውስጥ እናቶች የወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት እንዲጀመር፣ የሕፃናት ክትባትና መደበኛ የሕክምና አገልግሎት እንዲጀመር ይደረጋል። ከሽብር ቡድኑ ነፃ በሚሆኑ አካባቢዎችም ለሕዝቡ ሰፋ ያለ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የጤና ተቋማት በአፋጣኝ ሥራ እንዲጀምሩ ይደረጋል ነው ያሉት። በቂ የሆነ የመድኃኒት ግብዓት አቅርቦትም እንደሚኖር አስረድተዋል።ሚኒስትር ዴኤታው ለሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎችን በማሟላት፣ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ የወደመውና የተዘረፈውን በመተካት ኅብረተሰቡን እንክሳለን ብለዋል።የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ታሪኩ በላቸው የሆስፒታሉ አጠቃላይ የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች መዘረፋቸውንና መውደማቸውን እንዳረጋገጡ ነው የገለጹት።

በክልሉ ወራሪው ቡድን በደረሰበትና ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ሁሉ የጉዳት መጠኑን የሚያጠና ግብረኀይል ተቋቁሞ ምልከታ እየተደረገ ነው ብለዋል። ቡድኑ ለመዝረፍ ያስቸገረውን ቁሳቁስ ኾን ብሎ ማውደሙን መታዘባቸውንም አብራርተዋል።እስካሁን ባለው መረጃ በክልሉ ሙሉ በሙሉ አገልግሎታቸው የተቋረጠ 20 ሆስፒታሎች፣14ቱ ሆስፒታሎች ደግሞ የተዘረፉና የወደሙ፣ አገልግሎታቸው የተቋረጠ 277 ጤና ጣቢያዎች፣ ከነዚህ ውስጥ 153ቱ የተዘረፉና የወደሙ፣ 1ሺህ 162 ጤና ኬላዎች አገልግሎታቸው ያቋረጠና 642ቱ የተዘረፉና የወደሙ፣ 29 አምቡላንሶች የተዘረፉና የወደሙ፣ 2 የደም ባንኮች በሽብር ቡድኑ ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን አቶ ታሪኩ አስረድተዋል።ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት እንዳይችሉ ተደርጓልም ብለዋል። በመሆኑም ሕፃናት፣ አረጋውያን እና እናቶች የሕክምና አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ምክትል ኀላፊው ገልጸዋል።ከአሸባሪው ቡድን ነፃ በሆኑ አካባቢዎች በአስቸኳይ የጉዳት መጠንን በመለየት የጤና ተቋማቱ ሊሟላላቸው የሚገባውን ግብዓቶች እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።“ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት አገልግሎት ባለመሥጠታቸው የሚያልፍ ሕይወት መኖሩን በመገንዘብ ግብዓቶችን ለማሟላት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

ምክትል ኀላፊው በአጭር ጊዜ ውስጥ አጋር አካላትንና ኅብረተሰቡን በማነቃነቅ የጤና ተቋማቱ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ይደረጋልም ነው ያሉት።ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከመቄትተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

(አሚኮ)

Leave a Reply