ብርሀን ፍለጋ ቤቴን አላቃጥልም !! (ግልፅ ደብዳቤ ኢትዮጵያ ጠል ለሆኑ ኢትዮጵያውያን)

የገዛ አገርህን እንደ ጠላት፣ ጠላቶቿን ደግሞ እንደ ልብ ወዳጆችህ እያየሀቸው ኢትዮጵያ ሲከፋት እየፈነጠዝክ ሲደላት እየቆዘምክ መኖር አመል የሆነብህ የዚህ ሰፈር ፌዘኛ እንዴት ነህ ? ኢትዮጵያ እንዴት ይዛሀለች ? እንደ ተስፋይቱ ምድር በፍቅራቸው የተነደፍክላቸው ግብፅና አሜሪካስ እንዴት ናቸው ?

ይቺን ደብዳቤ ከዛሬ ነገ እፅፍልሀለሁ ብዬ ሳመነታ 2013 አለፈና አምና ስትዝትብን የከረመችው ወዳጅህ አሜሪካ ዘንድሮም እንደ አመሏ ቧ ማለት ጀምራለች፤ ግብፅም በዚያ ግድብ ቂም ካቄመችብን ሁለት አሀዝ አመታት ቢቆጠሩም በቀጥታ ብቅ ብላ ልትደፍረን ባለመቻሏ ከመሸጥ እስከ ማፍረስ የሚደርስ ሙሉ ውክልና ለወጊዎቻችን ሰጥታ በእጅ አዙር ልትደቁሰን በአዲስ መልክ ደፋ ቀና ማለት መጀመሯን አየሁና ይቺን ሀሳቤን ልፅፍልህ ተነሳሁ።

ካለችህ የሙሾና የሀሜት ጊዜ ቀንሰህ ፅሁፌን ስለምታነብልኝ የተለመደውን ምስጋናዬ አልነፍግህም።

አንድ አልገባ ያለኝን ሀሳብ ላጫውትህ ?

አሜሪካ የምትባለው የአለማችን ህጋዊ አምባገነን፣ ህጋዊ ወራሪ፣ ህጋዊ ገዳይ፣ ህጋዊ ዘራፊ፣ ህጋዊ ደፋሪ፣ ያለከልካይ ሲያሻት ማእቀብ ሲያሻት ደግሞ ቦንብ ጣይ የሆነችው አገር በዲሞክራሲ ታፔላ እጇን ሰተት አድርጋ ከታበት ሰላም የለገሰችው አገር ካለ እስቲ አንድ አገር ጥራልኝ። ከበቀደሟ አፍጋኒስታን እስካለፉት አመታት ኢራቅ፣ የመን፣ ሊቢያ ወዘተርፈ ብታይ ባልተቀደሰ እጇ ነካክታቸው የጆፌ አሞራ መፈንጫ አርጋቸዋለች።

ኢትዮጵያን ለማናወጥ እንደ ቁርጥ ቀን ጆከር ካርታ የምትጠብቀው የግብፁ አልሲሲ እንዴትና በማን ሴራ ስልጣን እንደተቆናጠጠ ከኔ በላይ ታውቀዋለህ። የግብፅ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ የመረጠው የሙርሲ መንግስት አካሄድ አልጥም ያላቸው አሜሪካኖች አልሲሲን ጉብ ሲያረጉ የግብፅን ህዝብ መናቃቸው አይደለም ? ከናንተ በላይ እኔ ነኝ የማውቅላችሁ የሚሉበትም ምክንያት ጠፍቶህ እንዳልሆነ አውቃለሁ።

ከሁለት አመት በፊት በፃፍኩልህ ደብዳቤ ላይ እንደገለፅኩልህ ላንተ ተብሎ በልዩ ትእዛዝ ተቀጥቅጦ ከሰማይ የሚወርድልህ ስህተት አልባ የአገር መሪ የለም። አብይ አህመድ የተባለ መሪ ጠልተህ ኢትዮጵያን የጠላህ ለታ ብትታከም ለዚህ ሁሉ ችግር ባልተዳረግን ነበር። መሪ ይመጣል፣ መሪ ይሄዳል።

ገና ለገና የበሬው ቆለጥ ወድቆልኝ እበላዋለሁ እያልክ ባዶ ሆድህን ከበሬው ኋላ ድክ ድክ እያልክ ከምትሮጥ ቆም በልና በአቅራቢያህ ከሚገኝ ምግብ ቤት ጎራ በል።

እጁን ታጥቦ፣ ፈጣሪውን አመስግኖ፣ ተረጋግቶ እጁን ወደ ማእድ የሚዘረጋ ተመጋቢ ጠፍቶ እንጂ የስልጣን መሶቡ ሰፊ ነው። የምትግጠው አጥንት ብታጣ የተከተፈ ስጋ አታጣም፣ እንቁላል ብታጣ በስጋው መረቅ የረጠበ ፈትፈት ያለ እንጀራ አታጣምና ሰከን በልልን።

አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ዞራ ባስነጠሰች ቁጥር የስንፍና ቃል ከመናገር ተቆጠብልኝ። ያለፈውን አመት 2013 ከአሜሪካ ግልምጫ ጋር ፊትለፊት ተጋፍጠን ከመጣብን ፈተና ያነሰ እንጂ የበለጠ ችግር አይመጣብንም። እቀልብላችኋለሁ የምትለንን 7% ህዝባችንንም ቢሆን ፆም የሚያሳድር አምላክ የለንም።

እንደ አገር እስከዛሬ ካሳለፍነው በረዶና ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ የባሰ ዝናብ እንደማይመጣብን እርግጠኛ ሆኜ እነግርሃለሁ። የበሰበሰ ዝናብ እንደማይፈራ በስብሰን አይተነዋል።
ከነጫጮቹ ጫና የተላቀቀ አዲሱን አሰላለፍ ልንጀምር ነውና ባታግዘን እንኳን ዝም በማለት ተባበረን። ያለችኝን አንድ አገር አሲዤ ቁማር ለመጫወት የሚያበቃኝ ህሊና እንደሌለኝ ዛሬም አረጋግጥልሀለሁ።

ታደሰ ተክሌ ነኝ
8/01/14https://www.facebook.com/tadeko02

Leave a Reply