ዓለም ጆሮ የነፈገው የቆቦ ጭፍጨፋ!! በቆቦ መጅምላ መቀበርም ብርቅ ነው!!

ምስክርነቱ የካድሬ ወይም የጮሌዎች አይደለም። ድንጋጤውና ሰቀቀኑ ከፊታቸው ያልተገፈፈ ነዋሪዎች በአይናቸው ብረት ያዩትና ተርፈው ለእማኝነት የበቁ ናቸው። ጥያቄ ያለው ” ማን ይህን ፈጸመ” ሳይሆን፣ “ይህ ለምን ይፈጸማል? ምንስ ምክንያት ይቀርብለታል? ዓለምስ አማራ ሲጨፈጨፍ ስለምን ጆሮውን ይደፍናል?” የሚለው ነው።

“አሸባሪው ህወሓት በአንድ ቀን ከ600 በላይ ንፁሃንን ጨፍጭፏል” ሲሉ ከቆቦ ከተማ እና ዙሪያዋ የተፈናቀሉ የዓይን እማኞች መናገራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለወትሮው አማራ ክልል ለተፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች ዳተኛነት የሚታይበት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንም ጉዳዩን ” ሰጋሁ” ሲል ወዲያውኑ በትኩሱ ይፋ ቢያደገውም፣ ሌላ ጊዜ የመረጃ ምንጫቸው የሚያደርጉት ሚዲያዎች፣ “የመብት ተሟጋች ነን” የሚሉ፣ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የክብር ዲግሪ የሰጣቸው አቶ ኦባንግ ሜቶና ይኑር ይሙት የማይታወቀው ድርጅታቸው ምን አለ? ለሚለው ጥያቄ ዜጎች መልስ የላቸውም።

የትህነግ ጭፍራ በመሪዎቹ ትዕዛዝ ጭፍጨፋውን የመረጠው የከተማዋ ነዋሪ ተናንቆ ካባረረው በሁዋላ ዳግም ተመልሶ መሆኑ ተመልክቷል። ምስክሮቹ እንዳሉት ከሆነ ጭፍጨፋው በከባድ መሳሪያና ቤት ለቤት የተፈጸመ ነው። ዝግጅት ክፍሉ በዘመድ ዘመድ ባገኘው መረጃ ዘግናኝ የስለት ግድያ ሁሉ ተፈጽሟል። ትህነግ ይህን ለምን እንደሚፈጽም ገብቶት የሚያስረዳ የለም። ቆቦ ብቻ ሳይሆን እግሩ ገብቶ በወጣበት ሁሉ ለፈጸመው ጭፍጨፋ ሌላ ወረራ የፈጸመ አካል የነበረ ይመስል ” በገለልተኛ አካላት ይጣራ” ሲል የሚደመጠው ትህነግ ማንን ሊወነጅል እንዳሰበ ፍንጭ አልሰጠም። ሰለባዎቹ ከአይናቸው ይልቅ ገና ወደፊት ትህነግ የሚፈጥርላቸውን አዲስ የምናብ ጠላት እንዲወነጅሉ እንደሚጠበቅም መረዳት አይቻልም።

አሸባሪው ህወሓት ከባድ መሳሪያ በመጠቀም በአንድ ቀን ከ600 በላይ ንፁሃንን እንደጨፈጨፈ ከቆቦ ከተማ እና ዙሪያዋ ተፈናቅለው በዞብል የተጠለሉ የዓይን እማኞች በመንግስት ሚዲያ መናገራቸው ” በገለልተኛ አካል ሚዲያ ይሁን” ካልተባለ በስተቀር ጭፍጨፋውን ማስተባበል አይቻልም። ገለልተኛ የሚባሉት ሚዛነ ሰባራ ሚዲያዎች ቆቦም ሆነ ሌሎች ስፍራዎች ስለተፈጸመ ጭፍጨፋ ለመዘገብ ፈቃደኛ ካልሆኑና ዓላማቸው ሌላ ከሆነ በየትኛው ሚዲያ ይናገሩ?

አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ጭፍራ የአስራ አንድ ዓመት እድሜ ወንድ ታዳጊ ሳይቀር ገሎ፣ የጅምላ መቃብር እንዳይገኝ ” አትቅበሩ” ብሎ መከልከሉ የገለጹት አርሶ አደሮች ” አስከሬን በጅብ እንዲበላ ተደረገ” ሲሉ የሃዘናቸውን መራራነት ይገልጻሉ።

May be an image of 5 people, people standing and outdoors

“ቡድን በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማና ዙሪያዋ በሚኖሩ ወገኖች ላይ ግፍ ፈፅሟል፤ ከተማዋን ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት እና የግለሰብ ንብረት ዘርፏል፤ ከተማዋን አውድሟል” ሲሉ በህይወት የተረፉ ተፈንቃዮች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ልክ በሌሎች አካባቢዎች እንደሆነው ተገለዋል። ተዘርፈዋል። ከተማቸው ወድሟል። ከዚህ በላይ ” ሂሳብ ማወራረድ” አለ?

“የሽብር ቡድኑ አባላት ሴት ሕፃናትን ጭምር አስገድደው ለ6 ደፍረዋል፤ ከሴቶች የጆሮ ጌጥ ዘርፈዋል፤ ቀለበት ወስደዋል፤ የአንገት ሐብል ቀምተዋል፤ የሚፈልጉትን ልብስ አስወልቀው ለብሰዋል፤ ሰዓትና ሽርጥ ሰርቀዋል፤ የአርሶ አደሮችን ቤት ነዳጅ ተጠቅመው አቃጥለዋል” ብለዋል የዓይን እማኞቹ፡፡

የሽብር ቡድኑ በቆቦ ከተማ እና ዙሪያዋ ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ የፈፀመው ግፍ ሰላም የነሳቸው የከተማዋና ዙሪያዋ ወጣቶች ተደራጅተው በግንባር ተፋልመዋቸው ነበር። የወጣቶቹን ጠንካራ ፍልሚያ መቋቋም የተሳነው ወራሪ ቡድን ጳጉሜ 4 ቀን 2013 ዓ.ም የቆቦ ከተማን ለመልቀቅ ተገደደ። ይሁን እንጅ ከጎብዬና ሮቢት አካባቢዎቾ የነበረውን ወራሪ ኃይላቸውን በማቀናጀት ዲሽቃ፣ ብሬል እና ዙ-23 የተሰኙ ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም የሚፋለሟቸውን ወጣቶች በመበተን የቆቦ ከተማን በድጋሜ ከያዙ በኋላ ከ600 በላይ ንፁሃንን በገፍ እንደጨረሱ ምስክሮቹ ያስረዳሉ።

በተለይ ወንዶችን የ11 ዓመት ሕፃን ሳይቀር ከየቤቱ እያደኑ ገድለዋል፤ የተገደሉ ወገኖች እንዳይቀበሩም በመከልከል በጅብ እንዲበሉ አድርገዋል ሲሉ መናገራቸውን የአሚኮ ዘገባ ያስረዳል። ሰለባዎቹ “አማራ ጠልነታቸውን በግልጽ ለማሳየት የማይፈፅሙት ግፍ የለም” ሲሉ የሆነውን ሁሉ ለሚዲያው ነግረዋል። እነዚሁ በዞብል አነስተኛ ከተማ የተጠለሉት የቆቦ ከተማና ዙሪያዋ ቀበሌ የዓይን እማኞች፣ ሕዝቡ በከፋ ችግር ውስጥ ስለሆነ መንግሥት አካባቢውን መልሶ እስከሚቆጣጠር ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ሊደርሱ እንደሚገባ ተናግረዋል። በሽብር ቡድኑ ላይ ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ የከፋ እልቂት ሊፈጸም ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

May be an image of 2 people, people standing and outdoors

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነ ቆቦ የቤት ለቤት ጭፍጨፋ መፈጸሙ ከተሰማ ወዲህ ድርጅቱ ያለው ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መበት ኮሚሽኑ ባወጣው አጭር መግለጫ እንዳለው በቆቦ ከተማ እና በዙርያው ባሉ የገጠር ከተሞች በሕወሓት ኃይሎች « የሲቪል ሰዎች መኖርያ አካባቢዎችን ፣ የቤት ለቤት አሰሳ እና ግድያ ፣ ዝርፍያ እና የሲቪል መሠረተ ልማቶች ጥቃት ጭምር መፈጸሙን » ሪፖርቶች ደርሰውናል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኮሚሽኑ በአካባቢው የሚያደርገውን ምርመራ እንደሚቀጥል ገልጿል። በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች በማናቸውም ወቅት ሲቪል ሰዎችን የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዲያከብሩ ኮሚሽኑ በመግለጫው አሳስቧል።

የአይን እምኞችን የጠቀሱ በቲውተር እንደገለጹት ብሄርን መሰረት ያደረገው የቤት ለቤት ጭፍጨፋ የተከናወነው በትግራይ ተዋጊዎች አማካይነት እንደሆነ፣ ከተማዋ ውስጥ ያለው የመሰረተ ልማት ተቋሞች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መዘረፋቸውንና መውደማቸውን አመልክተዋል።

ሃዋሳ ጋርዲያን የሚባል ድረ ገጽ ቀደም ሲል ጭፍጨፋ እንደተካሄደ ጠቅሶ ዘግቦ ነበር። የትህነግ ሃይል በወረራ ይዟቸው በነበረባቸው ቦታዎች የጅምላ ጭፍጨፋ ማካሄዱ በስፋት እየተገለጸ ነው። ቀደም ሲል ማይካድራ ከተፈጸመው ውጪ በአፋርም ተመሳሳይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ምስክሮችና ሰለባዎች ሲያስረዱ መታየቱ ይታወሳል።

” ከአማራ ጋር የማወራርደው ሂሣብ አለኝ” በሚል በገሃድ የተናገረው ትህነግ በገሃድ የወደመ ንብረት፣ የሞቱ እንሳሳትና ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው በግልጽ እየታዩ ምስክረነት ቢሰጡም ” አላደረኩም በገለልተኛ ሃይል ይጣራ” የሚል ምላሽ ሲሰጥ መሰንበቱ የሚታወስ ነው።

ጆ ባይደን የአማራ ክልልን እንደሚጨምር ጠቅሰው ትዕዛዝ ያወጡት ይህ ሁሉ እየሆነ ነው።

Image

Leave a Reply