የደቡብ ዞን የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ዋና አዛዥ ሰላማዊ ትግልን ዛሬ ተቀላቀሉ

አዲስ አበባ መስከረም 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦነግ ሸኔ የደቡብ ዞን አዛዥ የሆኑት ጃል ጎሊቻ ዴንጌ በሸኔ እየተደረገ ያለውን አካሄድ በመቃወም ከቡድኑ ተለያዩ፡፡

ከ14 ዓመት በላይ በደቡብ ዞን ግንባር የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን ሲመሩ የነበሩት ጎሊቻ ዴንጌ በዛሬዉ ዕለት የትጥቅ ትግል ትተው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵየ በተፈጠረው የዴሞክራሲና የሰላም አማራጭ ለመታገል ወስነዉ ተቀላቅለዋል፡፡

ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ መግለጫ የሰጡ ሲሆን÷ ከዚህ በኋላ መዋጋት አስፈላጊ አይደለም ሲሉ የሸኔ አካሄድ ከዓላማ እያፈነገጠ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ሸኔ ከህወሓት ጋር ጋብቻ መፈፀሙ ህወሓት ትላንት በኦሮሞ ህዝብ ላይ የፈፀመውን በደል መርሳት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሌሎች የሸኔ አባላት ቆም ብለው እራሳቸውን እንዲፈትሹና በጫካ ውስጥ ሆኖ ከዚህ በኋላ መታገል አስፈላጊ አለመሆኑን በማንሳት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጃል ጎሊቻ ዴንጌን በቦሌ አቀባበል ያደረጉት የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ፥ ጃል ጎሊቻ ስላደረጉት ውሳኔ መንግስት በመልካም ጎኑ ይመለከታል ሲሉ ሌሎች የሸኔ አባላት የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ በዚህ መፍታት እንደማይቻል ተረድተው የመንግሥትን ጥሪ እንዲቀበሉ አሳስበዋል፡፡

መንግስት በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር በሩ ክፍት መሆኑንም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

በዳግማዊ ዴግሲሳ እና በታሪኩ ለገሰ

See also  አሜሪካ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ስትል ኢትዮጵያን እንድትደግፍ ጥሪ ቀረበ

Leave a Reply