የአገር ደህንነት – በትህነግና ሌሎች ሽብርተኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላ

የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ በሕወሓት ቡድን እና በሌሎች ሽብርተኞች ላይ የሚወሰደውን የተቀናጀ እርምጃ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል የብሔራዊ መረጃና ደህነት አገልግሎት አስታወቀ። አበይት የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶችን ለማስቀረት ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ገልጿል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በ2013 ዓ.ም አፈጻጸም እና በ2014 የሥራ ዘመን ዕቅድ ዝርዝር ተግባራት ዙሪያ ውይይት አድርጓል።በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ሀገራዊ አንድነትን ለማፍረስ ዒላማ ያደረጉ የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶችን በመቀልበስ ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።ተቋሙ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በተከናወኑ ስራዎች ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን አመልክተዋል። የደህንት ስጋቶችን በመከላከል የሁለተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እንዲከናወን ተቋሙ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ከተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ካለው የሕልውና ዘመቻ ጋር ተያይዞ በተከናወኑ ስራዎች በአገሪቷ ላይ የተደቀነውን ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ማስቀረት መቻሉንም ነው ያስረዱት።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የውስጥና የውጪ ሽብርተኝነትን በመከላከል፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያና የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ረገድም ውጤታማ የተባሉ ኦፕሬሽኖች መከናወናቸውን ተናግረዋል።የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ሕልውና እና አንድነት ለማስጠበቅ ሕወሃትን ጨምሮ በሽብርተኞች ላይ መወሰድ የተጀመረው የተቀናጀ እርምጃ ይቀጥላል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በሚከናወነው ሶስተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ሌሎች አበይት የብሄራዊ ደህንነት ስጋቶችን ለማስቀረት ከፌደራልና ከክልል የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።

ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ያሉ የደህንነት ስጋቶችን በመተንተን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅና ወቅቱ የሚፈልገውን ተቋማዊ አቅም ለመገንባት የተጀመሩ የማሻሻያ ስራዎች በበጀት ዓመቱ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ ማስታወቁን የዘገበው ኢዜአ ነው።

Leave a Reply