ፊደል ካስትሮ – ከ 600 በላይ ግድያ ሙከራዎች ተርፈው! በማእቀብ ሳትበገር ብርቱ ሆና ቀጥላለች!

ኩባም ለሃምሳ ምናምን አመት በተጣለባት ማእቀብ ሳትበገር ዛሬም ብርቱ ሆና ቀጥላለች!!

የኩባው ፕሬዝደንት ፊደል ካስትሮ ከመኝታቸው ተነስተው ልብሳቸውን ከለበሱ በኋላ ጫማቸውን ለማድረግ ጎንበስ ሲሉ ፡ ተወልውለው በስርአት በሚቀመጡት ጫማዎቻቸው ላይ አቧራ መሰል ብናኝ ተነስንሶ ተመለከቱ ። ተጠራጣሪው ካስትሮ ጫማቸውን ለማንሳት የተዘረጉ እጆቻቸውን ሰብስበው ከሳቸው ጋር በአንድ ጊቢ የሚኖረውን የልዩ ጥበቃ ሃላፊያቸው ጋር ደወሉ።

የቀድሞዉ የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ ወደ ስልጣን እንደወጡ ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙት አሜሪካንን ነበር ። ሆኖም አሜሪካ ኪውባን እንድትደግፍ እና ስለሁለቱ ሃገራት ወዳጅነት ላይ ለመምከር በነጩ ቤተመንግስት ለተገኙት ካስትሮ የሃገር መሪን ክብር በሚመጥን መልኩ የሚያስተናግዳቸው ፕሬዝደንት ጠፋ ።

የወቅቱ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ዴቪድ አይዘአወር የልኡካን ቡድናቸውን እየመሩ አሜሪካንን ለመጎብኘት የሄዱት ካስትሮን ጋዜጠኞች ባልተገኙበትና በዝግ በተካሄደ የአንድ ሰአት የመወያያ ጊዜ ከመስጠት ውጭ በቂ የመነጋገሪያ ጊዜ ሊሰጣቸው ፈቃደኛ አልሆኑም።

ይባስ ብሎም ከካስትሮ ጉብኝት በኋላም አሜሪካ ለኪውባ የወዳጅነት ጥያቄ መልስ ከመስጠት ይልቅ ካስትሮን ከስልጣን ወይም ከምድር ለማስወገድ በስለላ ድርጅቷ ሲአይኤ (CIA) በኩል የኩባ ስደተኞችን አስታጥቃ የእጅ አዙር ጦርነት ከፈተች።

ለዚህ የአሜሪካ ተግባር ሃቫናም (የኩባ ዋና ከተማ) በሃገሯ የሚገኙ የአሜሪካን ኩባንያዎች ዘግታ የቀሩትንም ወረሰች ። አለመግባባቱ ጦዞ አሜሪካ የኪውባን ስደተኞችና ቅጥረኛ ወታደሮችን አሰማርታ መጠነ ሰፊ ወረራ ጀመረች ። ኪውባ ይህን የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት ለመገዳደር ከኮሙኒስት ሃገር ሶቪየት ጋር ወዳጅነቷን ማጥበቅ ነበረባት ።

የካስትሮ መንግስት ከቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ባገኘው የጦር መሳሪያ እርዳታ ተቃዋሚዎቹን ከማጥቃት አልፎ ትላልቅ ድንበር አቋራጭ ሚሳይል ወደ አሜሪካ ከተሞች አነጣጥሮ ጦርነቱን በአሜሪካ በኪውባና በሩሲያ መሃከል እንዲሆን አድርጎ መጠባበቅ ጀመረ ።

የአሜሪካ ከተሞች ከኩባ በሚሰነዘር የኒውክሊየር ጥቃት ሊፈፀምባቸው እንደሚችል ስጋት በመፈጠሩ አሜሪካ ሶቪየት ህብረት መርዳቷን እንድታቆም አለበለዚያ ግን ፀቧ ከሶቪየት ህብረት ጋር እንደሆነ ማስጠንቀቅ ያዘች።

አሜሪካ የተፋጠጠችው ከድሃዋ ኪውባ ጋር ሳይሆን ከምንጊዜም ተፎካካሪዋ ( ሶቪየት ህብረት ( ሩሲያ ) ጋር መሆኑን ስታውቅ ወደቀልቧ መመለስ ጀመረች ። በሁለቱ ሃያላን ሃገራት መፈራራትም ሊፈፀም የታቀደው የአሜሪካ የእጅ አዙር መጠነ ሰፊ ወረራ እቅድ ተሰረዘ።

ኩባ ከጎኗ ቆማ እስኪ የሚነካሽን አያለሁ ባለቻት ሩሲያ አማካኝነት ከአሜሪካን ወታደራዊ ጥቃት ተረፈች ። ይህን የተገነዘቡት የአሜሪካ መሪዎች የሃቫናውን መንግስት በኤኮኖሚ አሽመድምዶ እግራቸው ስር ለማንበርከክ ሌላ እቅድ አወጡ ። ማእቀብ መጣል ።

አሜሪካ ያኔ የጣለችው ማእቀብ ከዛሬ ነገ ኪውባን እጄ ላይ ይጥልልኛል ብላ ብታስብም በፊደል ካስትሮ ጠንካራ አመራርና በህዝቧ ብርታት ማእቀቧ ሊሰራ አልቻለም ። ይህን የተረዱት የአሜሪካ መሪዎች ሁሉም ነገር የሚጠናቀቀው ካስትሮ ከዚህ አለም በሞት ሲሰናበት ነው ብለው በማሰብ ካስትሮን የመግደል ተልእኮ ለስለላ ድርጅቷ ለ CIA ተሰጠው ።

ይህ ተልእኮ በየጊዜው አሜሪካንን በመሯት ሰባት መሪዎች ሳይቀየር ከ 600 ጊዜ በላይ ካስትሮን ለመግደል CIA ወገቡን አስሮ ዶላሩን መንዝሮ መሞከር ጀመረ ።

ፊደል ካስትሮ በመኖሪያ ቤታቸው በሚገኘው የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ጥቂት ደቂቃዎች ለማሳለፍ የመዋኛ ቁምጣቸውን ለብሰው እየሄዱ ሳለ ከብዙ የግድያ ሙከራ ያዳናቸው የልዩ ጥበቃ ክፍል ሃላፊው ካለወትሮው አስቆማቸውና
“ውሃውን መመርመር ሳይኖርብን አይቀርምና ጓድ ፕሬዝዳንትእባክህ አረፍ በል ” አላቸው ።


የውሃው ናሙና ተወስዶ በላቦራቶሪ ሲታይ በርግጥም የመዋኛ ገንዳው ውሃ ለሞት በሚያደርስ የቆዳ በሽታ በሚያመጣ ፈንገስ ተመርዞ ነበር ።


የአሜሪካው C.I.A ይህ የግድያ ሙከራ እንደከሸፈ ሲያውቅ ቦቱሊነም (botulinum) የሚባል አደገኛ ኬሚካል ፕሪዝዳንቱ በሚወዱት ቶስካኖ ሲጋራ ውስጥ በመክተት ወደ ካስትሮ መኖሪያ በስውር አስገብቶ የካስትሮን መሞት መጠበቅ ጀመረ። ነገርግን ይሀው የጥበቃ ክፍል ሃላፊ በሲጋራዎቹ ላይ ባደረገው ድንገተኛ ምርመራ ሲጋሮቹ እንደተመረዙ ታወቀ


በተለያየ መንገድ ፕሬዝዳንቱን ለመግደል ሳይታክት የሚሞክረው C.I.A ፕሬዝዳንቱ የሚውጡትን አይነት ተመሳሳይ ክኒን በመድሃኒት ብልቃጣቸው ውስጥ በመክተት ለመግደል ያደረገውም ሙከራ ከሸፈ።


በስለላ ድርጅቱ በተመለመለች የሚወዷት ፍቅረኛቸው ተመርዘው ይህችን አለም እንዲሰናበቱ የታሰበውም ሙከራ ሳይሳካ ቀረ ።
ይህ ሙከራ ይሳካል ተብሎ የታሰበው የካስትሮ የቀድሞ ፍቅረኛ በነበረችው በማሪታ ሎሬንዝ ነበር:፡ ካስትሮን ለመግደል ከምትኖርበት አሜሪካ ወደ ኩባ ሃቫና የተመለሰችውና ድርጊቱን ከፈፀመች በዶላር እንደሚያንበሸብሿት በCIA ቃል የተገባላት ማሪታ ሎሬንስ ካስትሮን ለማግኘት ብዙም ችግር አልገጠማትም ነበር።
ሆኖም ካስትሮን አግኝታ ፊት ለፊቱ ስትቆም ፍቅር አሸነፈና ያንን ክፋት የመፈፀም ወኔዋ ከዳት ። እቅፉ ውስጥ ሆና እያለቀሰች ፊደል አንተን እንድገድል ነው የመጣሁት ነገር ግን ልገድልህ አልችልም። ምንም ያደረከኝ ነገር የለም ብላ የስለላ ድርጅቱን እቅድ ነግራ የታሰበውን እቅድ አከሸፈችው ።

በስለላ ድርጅቱ በልዩ ትእዛዝ ተመርቶ ካስትሮ ቢሮ እንዲገባ ተሞክሮ የነበረው #እስክርቢቶም ወደቢሮው ሳይደርስ በቁጥጥር ስር የዋለው ግቡን ሳያሳካ ነበር ። ይህ እስክርቢቶ እጅግ መርዛማ ኬሚካል እንዲያመነጭ ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ ፡ ካስትሮ በስክርቢቶው መፃፍ ሲጀምሩ ኬሚካሉ መትነን ይጀምርና መተንፈሻ አካላቸውን መርዞ ከመቅፅፈት ለሞት የሚያበቃቸው ነበር።

አንድ ሌላ ቀን ደግሞ ፕሬዝደንት ካስትሮ ከመኝታቸው ተነስተው ልብሳቸውን ከለበሱ በኋላ ጫማቸውን ለማድረግ ጎንበስ ሲሉ ፡ ተወልውለው በስርአት በሚቀመጡት ጫማዎቻቸው ላይ አቧራ መሰል ብናኝ ተነስንሶ ተመለከቱ። ተጠራጣሪው ካስትሮ ወዲያውኑ እጆቻቸውን ሰብስበው ከርሳቸው ጋር በአንድ ጊቢ የሚኖረውን የልዩ ጥበቃ ክፍል ሃላፊ ጋር ደወሉ ። ጫማዎቻቸው በጓንት ተይዘው ወደላቦራቶሪ ተልከው የተገኘው ውጤት ልማደኛው CIA ፕሬዝደንቱን በአቧራ መሰል ገዳይ ኬሚካል በጫማቸው ውስጥ በመበተን ያቀደው ሙከራ እንደነበር ታወቀ::

– ከገዳይ ባክቴሪያ በተሰራ መሃረብ

– ለሃቫናው ሂልተን ሆቴል አስተናጋጅ (ዌይተር) ማባበያ በመስጠት ካስትሮ የሚወዱትን ሚልክ ሼክ በመመረዝ ለመግደል መሞከር
በአልሞ ተኳሾች
– ለንግግር በሚወጡበት ፖዲየም ስር ፈንጂ በመቅበር

እና በሌሎች ብዙ የግድያ ሙከራዎች ካስትሮ በተለያዩ የአሜሪካን ፕሬዝዳንቶች ትእዛዝ ማለትም
በፕሬዝዳንት አይዘንአወር: 38 ጊዜ
በ ኬኔዲ: 42 ጊዜ
በ ጆንሰን: 72 ጊዜ
በ ኒክሰን: ዘመነ መንግስት 184 ጊዜ
በ ጂሚ ካርተር: 64 ጊዜ
በ ሬገን: 197 ጊዜ
በ ቡሽ : 16 ጊዜ የግድያ ሙከራ ሲደረግባቸው
በመጨረሻም በ ክሊንተን: 21 ጊዜ የመግደል ሙከራ የተደረገባቸውና ኩባን ለግማሽ ክፍለዘመን የመሩት የኩባው ፊደል ካስትሮ ከተደረገባቸው ከ 600 በላይ ሙከራዎች ተርፈው በ90 አመታቸው በተፈጥሮ ሞት መሞታቸው አስገራሚ ነው። ኩባም ለሃምሳ ምናምን አመት በተጣለባት ማእቀብ ሳትበገር ዛሬም ብርቱ ሆና ቀጥላለች!!
.
Wasihune Tesfaye

Leave a Reply