እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ – ዐቢይ አሕመድ

ስለ መስቀል በዓል ስናነሣ አንድ መታሰብ ያለበት ጉዳይ አለ። ከፈተና በኋላ ድል፣ ከጨለማ በኋላ ብርሃን፣ ከመውደቅ በኋላ መነሣት እንደሚኖር። የጠፋ ሁሉ ጠፍቶ እንደማይቀር፤ የመስቀሉ ታሪክ ያስተምረናል።

ባለፉት ሦስት ዐሠርት ዓመታት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከልባችን ላይ እንዲፋቅና ስለ ሀገር ያለን ፍቅር ከውስጣችን እንዲጠፋ በብዙ መልኩ ሤራ ተሠርቷል። እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንድንተያይ ብዙ ተንኮል ተጎንጉኗል። በደስታም ሆነ በኀዘናችን፣ በድልም ሆነ በችግራችን አንድነትና ኅብረታችንን እንዳናስቀድም ተደርገናል። ምኞትና ፍላጎታችን በክልልና በብሔር ዙሪያ ብቻ ታጥሮ ትልቁን ሀገራዊ ምስል እንዳናስተውል ተሞክሯል። ሳይወዷት የመሯት ጠላቶቿ፣ ኢትዮጵያ በትንሽ በትንሹ እየፈረሰች እንደሆነ እያሰቡ ይደሰቱ ነበር። “አሁን ያለችው ኢትዮጵያ እኛ ብቻ እንድናስተዳደራት የተሠራች ናት፤ እኛ እስከፈቀድን ድረስ የምትኖር፣ በሌላ እጅ ከገባች በቀላሉ የምትፈርስ ናት” እያሉ በዕብሪት አፋቸውን ሞልተው ይናገሩ ነበር። ሕዝባዊ አንድነታችን ላልቶ እንደተበጠሰና እነርሱ በፈለጉ ጊዜ ሀገራችንን በቀላሉ ሊያፈርሷት እንደሚችሉ ደጋግመው ዝተዋል። ዳሩ ግን ሁሉም ነገር እንደተናገሩት አልሆነም። ኢትዮጵያዊነት እንደ ክርስቲያኖች መስቀል የመለያየት አፈር የተጫነው ቢመስልም አልጠፋም። አንድነታችን የሰለለ ቢመስልም አልተበጠሰም። ለሀገር ያለን ቀናዒነት የተዳፈነ ቢመስልም አልቀዘቀዘም ነበር።

ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በክርስቲያኖች ዘንድ የፈውስና የኃይል ምንጭ ተደርጎ ይታመናል። ለሕመማቸው ፈውስን፣ ለመከራቸው ጊዜ ጽናትን፣ በተሰበሩ ጊዜ ብርታትን፣ በተበታተኑ ጊዜ ኅብረትን አምጥቶላቸዋል። ይኽ ሁኔታ ያላስደሰታቸው የዚያን ዘመን ጨቋኞች ሤራ ሲያስቡ ዋና ትኩረታቸውን ያደረጉት የመስቀሉን ደብዛ ለማጥፋት ነበር። ከሰው ደብቀው ቀበሩት። ቦታውንም የቆሻሻ መጣያ እንዲሆን አዘዙ። ለ300 ዓመታት ከየነዋሪው ቤትና ከየሰው ግቢ ተጠርጎ የሚወጣ ቆሻሻ እየተጣለበት ቆይቶ ግዙፍ ተራሮችን መሰለ። ነገር ግን ክፉዎች እንዲህ ለክፋት መትጋታቸው በመስቀሉ ቤዛነት የሚያምኑትን አላሸነፈም። ተራራ ንደው፣ ቁልሉን ደርምሰው፣ አቧራውን ጠርገው፣ መስቀሉን ከማግኘት አላገዳቸውም።

ባሳለፍነው ዓመት አሸባሪው ጁንታና የኢትዮጵያ ጠላቶች በሐሰት ፕሮፓጋንዳቸው የሀገራችንን ስም ሊቀብሩ ተባብረው ሲሠሩ ነበር። በውሸት የተቀመሙ ዜናዎቻቸውን በሚያሠራጩባቸው ሚዲያዎች አማካኝነት ያልተፈጠረውን ተፈጠረ፣ ያልሆነውን ሆነ እያሉ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያ ቀና ብላ እንዳትታይ ዐቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አድርገዋል። ዓላማቸው ግልጽ ነው። የእነርሱ ጥቅም የሚከበረው በእኛ መሸነፍ ውስጥ እንደሆነ ያውቃሉ። በውንጀላዎቻቸው ተሸንፈን ጉልበታችን ሲብረከረክ በቀላሉ እጅ እንሰጣለን፤ ለእኩይ ፍላጎታቸው ተገዥ እንሆናለን ብለው አስበዋል። በተሸናፊነት ሥነ ልቡና ውስጥ ገብተን ዳግም በእግራችን መቆም ካልቻልን፣ ያኔ እስከመጨረሻው የእነርሱ ጥቅም ባሪያዎች ሆነን እንደምንቀር ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለዚህም የቻሉትን ያህል የውሸት ቆሻሻ ሰብስበው፣ የእኛን እውነት የሚጋርድ ግዙፍ ተራራ መፍጠር ችለዋል።

መስቀሉን አርቀው የቀበሩ ሰዎች መስቀሉ ለዘላለም እንደተቀበረ የሚቀር መስሏቸው ነበር። መስቀሉ አፈር ተጭኖት ስለተከለለ ትውስታው ከምድረ ገጽ እንደሚሰረዝ፣ እምነቱ ከክርስቲያኖች ልብ ተፍቆ እንደሚጠፋ አስበዋል። ነገር ግን ሐሳባቸው እውነት የመሰለው እንደ ንግሥት እሌኒ ያሉ ብርቱዎች መስቀሉን ፍለጋ እስኪነሡ ድረስ ብቻ ነው። የእነርሱ ዓላማ ስኬት የተመሠረተው በሌሎች ስንፍና ላይ በመሆኑ፣ ብርቱ ፈላጊዎች ቆርጠው በተነሡ ጊዜ፣ የመስቀሉ መጥፋት ጉዳይ ያከትምለት ጀመር። “ጠፋ”ጠፋ የሚለው ዜና “ተገኘ” በሚለው ዜና ተተካ። እንደተተካም ቀረ።
ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ለመፈለግ በተነሣች ጊዜ፣ ነገር ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆኖ አልጠበቃትም። መስቀሉ ስለመቀበሩ እንጂ የት እንደተቀበረ እንኳን አታውቅም ነበር። በዙሪያዋ የነበሩ ሰዎችም መንገድ ከመጠቆም ይልቅ ተስፋ በማስቆረጥ የተጠመዱ ነበሩ። የመስቀሉ ጉዳይ ያበቃ ያከተመለት ጉዳይ እንደሆነ ነበር የሚነግሯት። እሷ ግን እጇን አጣጥፋ ከመቀመጥ ይልቅ እምነትና ተስፋዋን ይዛ በመፈለጉ ጸናች። ተስፋ አስቆራጮች የሚናገሩትን ትታ እምነት የጣለችበትን የዕጣን ጢስ ተከተለች። ተከትላም አልቀረች። ጢሱም መስቀሉ የተቀበረበትን ትክክለኛ ቦታ መጠቆም ብቻ ሳይሆን፣ ከብዙ ድካምና ልፋት ታደጋት። የዕጣኑ ጢስ ወደ እውነተኛው ቦታ የሚያደርስ ምልክት ሆናት።

ለዘመናት በሤረኞች ተንኮል ደብዝዞ የጠፋ የመሰለው አንድነትና ኢትዮጵያዊነታችን ወደ ቦታው እየተመለሰ ነው። ይሄንን የሚያሳዩ ምልክቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መታየት ጀምረዋል። እንደ እሌኒ ያሉ ጀግኖች፣ ሤረኞች የቀበሩት የመሰላቸውን ኢትዮጵያዊነት እያወጡት ነው። ከመላ ኢትዮጵያ፣ አያሌ እሌኒዎች መጥተው ታሪክ እየሠሩ ነው። ድሮ በክልሎች መካከል የነበሩ መሥመር የሳቱ ፉክክሮች አሁን በትብብር ተለውጠዋል። “አትምጣብኝ አልምጣብህ” የሚሉ ክፉ ንግግሮች “ለችግርህ ደራሽ እኔ ነኝ” በሚል ተተክተዋል። በየጓዳችን ተወሽቀን ስለ ጓዳችን ብቻ አብዝተን መጨነቃችን ቀርቶ ዛሬ ሀገራዊ ጥቅማችንን ላለማስነካት በዓለም ፊት በአንድ ድምፅ መናገር ጀምረናል። ኢትዮጵያዊ ማንነታችን በእርግጥም በደማችን ውስጥ ስለመኖሩ አሁን በግልጽ ይታያል። ኅብርነታችን መለያያችን ሳይሆን የአንድነት ጌጣችን መሆኑን እንደ መስቀሉ ከፍ አድርገን አሳይተናል።

አሁን ኢትዮጵያ በየተሠማሩበት መስክ ሉዓላዊነቷን ላለማስደፈር የሚባትሉ ልጆቿ ጥቂቶች አለመሆናቸውን እያየች ነው። ከጠላት ጋር አብረው ከጀርባ የሚወጓት ክፉ ልጆችዋ ዕለት በዕለት ቀን ሲጨልምባቸው፣ ወደ አመድነት ሲለወጡ፤ በተቃራኒው ለክብሯ ለሚጨነቁ ደጋግ ልጆችዋ ፈተናው እየቀለለ፣ የድል ውጋጋን በመታየት ላይ ነው። የጨለማው ጊዜ ተወግዶ ብርሃኑን፣ የፈተና ጊዜ አልፎ ድሉን የምናይበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አልጠራጠርም። የሤረኞች ምንቸት ወጥቶ፣ የኢትዮጵያዊነት ምንቸት እየገባ ነው።

የመስቀልን በዓል ስናከብር ግዛታዊ አንድነታችንን ለማስጠበቅ በዱር በገደሉ የሚወድቁ እኅቶቻችንንና ወንድሞቻችንን እያሰብን መሆን አለበት። እነርሱ እንደ ደመራው አንድ ሆነው ለኢትዮጵያ የሚሠው ህያዋን ችቦዎች ናቸው። ዛሬ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተጠብቆ ያለው እነርሱ በሚከሰክሱት አጥንትና በሚያፈሱት ደም ነው። በተመሳሳይ በጁንታው ጥቃት የተጎዱ ዜጎቻችንን አለሁ ልንላቸው፣ ከጎናቸው ልንቆም ይገባል። የከፈሉት ዋጋ ለኢትዮጵያ የተከፈለ ዋጋ ነው። የታመሙት የሁላችንን ሕመም ነው። ከቤት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መልሶ የማቋቋም፣ የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን የመገንባትና የወደሙ ጤና ተቋማትን በምትካቸው የመሥራት ኃላፊነት በእያንዳንዳችን ትከሻ ላይ የወደቀ ነው። ይሄንን ዐውቀን ከአሁኑ ወገባችን አሥረን መነሣት አለብን። ካላጎነበሳችሁ አንረዳችሁም የሚሉ ወገኞች ይኖሩ ይሆናል። ለኢትዮጵያ ሲባል ሐሞትና ከርቤ ለመጠጣት እንገደድ ይሆናል። ጥርሳችን ነክሰንና አንጀታችን አሥረን እንጋፈጠዋለን። ተጋፍጠንም እናሸንፈዋለን።

በዓሉ የሰላም፣ የመረዳዳትና የመተጋገዝ እንዲሆን እመኛለሁ።

በድጋሚ እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

መስከረም 15፣ 2014 ዓ.ም

You may also like...

Leave a Reply