ፍቅረ ማርቆስ ደስታ- ኢትኖግራፈሩ ደራሲ

የኢትዮጵያ የልብ-ወለድ ድርሰት (creative writing) ከሚታዩበት ድክመቶች አንዱ እንደ ሌሎች ሀገራት ድርሰት ፈርጀ ብዙ አለመሆኑ ነው። ደራሲዎቹ በአብዛኛው የሚያተኩሩት በሁለት ጭብጦች ላይ ነው- ፍቅር እና ወንጀል። ከዚያ ወጣ ብለው ሌሎች ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለመዳሰስ ሲሞክሩ አይታዩም።

ይሁን እንጂ ከተለመደው የድርሰቶቻችን አጻጻፍ ዘውግ ወጣ ብለው የራሳቸውን ልዩ የስነ-ጽሑፍ ዘይቤ እና የአትኩሮት ፈርጅ ለማስተዋወቅ የደከሙ ጥቂት ደራሲያን አሉ። ከእነዚያ ጥቂቶችም አንዱ በፎቶው ላይ የምትመለከቱት የብዕር ገበሬ ነው። ይህ ደራሲ ለየት የሚለው በርካታ ሰዎች (በተለይም ከተሜዎች) ብዙም ትኩረት የማይሰጡትን የብሄረሰብ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ተንተርሶ ግማሽ ደርዘን ያህል መጻሕፍትን ለተደራሲያን በማበርከቱ ነው።

—–

ፍቅረ ማርቆስ ደስታ ይባላል። በ1955 በጎጃም ክፍለ ሀገር ነው የተወለደው። በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ዲፓርትመንት በዲግሪ ተመረቀ። በተመሳሳይ ጊዜ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሆኖ በደቡብ ኦሞ ዞን፣ ጂንካ ከተማ ተመደበ። እዚያ መኖር ሲጀምርም በዞኑ ባሉት አስራ ስድስት ብሄረሰቦች ቋንቋ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ጌጣ ጌጥ፣ የኢኮኖሚ ስምሪት፣ ባህላዊ ዳኝነት፣ ማህበራዊ ህይወት፣ ሙዚቃ፣ ዳንኪራ፣ አፈ-ታሪክ፣ ስነ-ቃል ወዘተ ተማረከ።

ፍቅረ ማርቆስ ያየውን ነገር በማድነቅ ብቻ አልታቀበም። ከመምህርነት ሙያው ጎን ለጎን ያየውንና የሰማውን ነገር በጥልቀት አጥንቶ ለመክተብ ወሰነ። በዚህም መሠረት ከብሄረሰቦቹ መካከል እርሱ ላለበት አካባቢ ቀረብ የሚለውን የሀመርን ህዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ኪነ-ጥበብ እና ትውፊት በማጥናት ያገኘውን ውጤት እንደ ግብአት ተጠቅሞ ኢትኖግራፊያዊ የፈጠራ ጽሑፎችን መጻፍ ጀመረ። በ1987 የመጀመሪያ ድርሰቱ የሆነውን “ከቡስካ በስተጀርባ”ን ለህትመት አበቃ።

—-

ፍቅረ ማርቆስ መጽሐፉን ለህትመት ሲያበቃ ይዞት የተነሳው ጭብጥ ስለፍቅር እና ወንጀል መጻፍ በለመዱት ደራሲዎች እና በዚህ ዐውድ የተጻፉትን ድርሰቶች ማንበብ በለመደው ተደራሲ ዘንድ አጓጊ እና አነጋጋሪ መሆን አልቻለም ነበር። በአንትሮፖሎጂ እና ታሪክ ጥናት ዘርፍ የተሰማሩ ምሁራን ግን ስራውን በጣም ነው ያደነቁለት። አንዳንዶቹም በዘመኑ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ላይ የተለያዩ ግምገማዎችን ጽፈውበታል። ከዓመት በኋላ ደግሞ መጽሐፉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ባለው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም “ፍኩይ” የተሰኘ ሽልማት ተሸልሟል።

See also  አቶ ወርቁ አይተነው የገንዘብ ቀውስ እየገጠማቸው መሆኑ ተሰማ

በዚህ የተነቃቃው ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ በ1990 በብዙዎች ዘንድ የሚወደደውንና የእርሱ masterpiece ስራ ለመሆን የበቃውን “ኢቫንጋዲ”ን ለአንባቢያን አበረከተ። በተከታዮቹ ዓመታትም ” የዘርሲዎች ፍቅር”፣ “አቻሜ” እና “የንስር ዐይን” የተሰኙትን መጻሕፍት አሳተመ። በ1995 ገደማ አምስቱንም መጻሕፍት በአንድ ላይ አጠቃልሎ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሞ ሲያበቃ መጽሐፉን “Land of the Yellew Bull” በሚል ርእስ ለህትመት አበቃ።

——-

ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ በመጽሐፎቹ የሀመርን ህዝብ በማስተዋወቅ ብቻ አልቆመም። በብሄረሰቡ ደንብ መሠረት የሀመሮች አካል ሆኖ ከእነርሱ ጋር ኖሯል። ሀመሮች ደራሲው በብዕሩ የዋለላቸውን ውለታ በደንብ በመገንዘባቸው እንደ አንጋፋ ልጃቸው ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ በ2004 “እሄዳለሁ” ብሎ ሳያስታውቃቸው ወደ አሜሪካ በመሻገሩ በጣም ተናደውበት ነበር።

ፍቅረ ማርቆስ በአሜሪካ ለአስር ዓመት ያህል ከቆየ በኋላ አምና ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ታዲያ ደራሲው ወደ ሀመሮች ዘንድ ሲደርስ በዝምታ አልታለፈም። “በባህላችን መሠረት ጠፍቶ የመጣ ሰው ወደ ህዝቡ የሚቀላቀለው ከተገረፈ በኋላ ነው” ሲሉት ለመገረፍ አላቅማማም። ቅጣቱን ከተቀበለ በኋላም ከሚወዳቸው የሀመር ብሄረሰብ አባላት ጋር ተቀላቅሏል።

——-

ሀመር የሚባለው ኩሻዊ ቋንቋ ተናጋሪ ብሄረሰብ በኢትዮጵያ ምድር ለረጅም ጊዜ ነው የኖረው። በቀድሞ ዘመናት ስለዚህ ህዝብ ባህል፣ ታሪክ እና ትውፊት የነበረን እውቀት በጣም ውስን ነው። የሀመር ማንነት ወለል ብሎ የታየን ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ ባደረገው የብዕር ተጋድሎ ነው። ደራሲው ብዙ የለፋበት ብሄረሰቡን የማስተዋወቅ ስራ ውጤት ማምጣቱንም በራሱ ዐይን ለማየት ችሏል።

ለምሳሌ በድሮ ዘመን የ”ኢቫንጋዲ”ን ምንነት የሚያውቅ ሰው እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ባለፉት ሀያ ዓመታት ግን “ኢቫንጋዲ” በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ጽንሰ ሐሳብ ለመሆን ከመብቃቱ ባሻገር ለብዙ የፈጠራ ስራዎች መነሻ ሲሆን አይተናል። በዚህ ረገድ ጎሳዬ ተስፋዬ የተጫወተው “ኢቫንጋዲ” የተሰኘው ተወዳጅ ዘፈን እንደ አብነት ሆኖ ሊነሳ ይችላል።

———–

ኢትዮጵያ ውብ ናት! በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የውበቷ ፈርጦች መካከል አንዱ ብሄርና ብሄረሰቦቻችን፣ ቋንቋዎቻችን፣ የብሄሮቻችን ቱባ ባህል፣ ትውፊት፣ ኪነ-ጥበብ እና ታሪክ ነው። በዚህ በኩል እንደ ኢትዮጵያ የታደሉት ጥቂት ሀገሮች ብቻ ናቸው። እነዚህ በፈጣሪ የተሰጡንን ውበቶች እንደ ትልቅ ጸጋ ቆጥረን በደንብ ከያዝናቸውና ከተጠቀምንባቸው የፍቅር ማጎልበቻ ከማድረግ አልፈን ከፍተኛ ገቢ ልንዝቅባቸው እንችላለን።

See also  “መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ ሲሰጠው አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ በሚያስችል ቁመና ላይ ነው”

ይህንን ለመረዳት ካሻን አሁንም የደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታን ስራዎች እንደ ምሳሌ ማንሳት ይበቃል። ፍቅረ ማርቆስ የደረሳቸው ስራዎች በኪናዊ ውበታቸው ከማማር አልፈው ብዙ ቱሪስቶች የሀመርን አካባቢ እንዲጎበኙ በማነሳሳት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። እኛም ካወቅንበት የብሄረሰቦቻችንን ባህል፣ ቋንቋ፣ ትውፊት እና ታሪክ የወንድማማችነት ማጠናከሪያ፣ የእርስ በራስ መማማሪያ እና የውብ ኢትዮጵያዊነት ማጎልበቻ ከማድረግ አልፈን ትልቅ የሀገር ገቢ ማመንጫ አውታሮች ልናደርጋቸው እንችላለን።

—–

ፎቶ-በጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ

አፈንዲ ሙተቂ

መስከረም 3/2014

Leave a Reply