በውስጥ ጉዳያችን ላይ ለሚደረግ ጣልቃ ገብነት የሚቀርብን ማንኛውንም ምክንያት አንቀበልም አንታገስም

“በየትኛውም መልኩ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገባን ሀይል ኢትዮጵያ አትታገሰም” አቶ ደመቀ መኮንን


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኒዮርክ እየተካሄደ ባለው 76 ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡

አቶ ደመቀ በንግግራቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መርሆዎች የጋራ ተጠቃሚነት እና በሀገራት ሉዓላዊነት ውስጥ ጣልቃ የማይገባ እንደሆነ በግልጽ መቀመጡን አውስተዋል፡፡

“ሀገሬ ከሶስት ዓመት በፊት ለውጥ በማድረግ ለዲሞክራሲ፣ ለሰው ሀብት ልማት፣ ለሰብዓዊ መብት እና ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ ለተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ፍላጎቶች ላላቸው ቡድኖች የውይይት እና የአንድነት በር እንዲከፈት አድርጋለች” ብለዋል፡፡

በዚህም አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን ሪፎርሙ ያለፈተና አልተከናወነም ሲሉ ለጉባዔተኛው አብራርተዋል፡፡

በዚህ ሂደት ጥቅሜ ተነካብኝ ያለው ጠቅላዩና ወንጀለኛው ቡድን የሀገር መከላከያ ሰራዊታችንን ከጀርባው ካጠቃ እና በርካታ ጥፋት ካጠፋ በኋል መንግስት ህግን ለማስከበር እና ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ እርምጃ መውሰዱንም ተናግረዋል፡፡

መንግስት የሰብአዊ ድጋፍ ሲያደረግ ቡድኑ ድጋፉ እንዲደናቀፍ እና የዜጎች ስቃይ እንዲበረታ አድርጓል፡፡

በውሸት ፕሮፖጋንዳ የተካነው ቡድን በርካታ አፍራሽ ተግባራትን ፈጽሟል፡፡ የውሸት ክስተቶችን አስተጋብቷል፤ ቀድሞ በተዘጋጅ ስም የመጣፋት ዝንባሌ ከፍተኛ ዘመቻ አድርጓል፡፡

ህዝባችን ካለበት ችግር አንጻር በቂ ነው ባይባለም መንግስት የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ መንግስታዊ ግዴታውን ለመወጣት በመስራት እና የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲመረመሩ እንዲሁም እርምጃዎች እንዲወሰዱ አድርጓል ብለዋል አቶ ደመቀ መኮንን፡፡

የጥፋት ቡድኑ በሚከፍላቸው የፕሮፖጋንዳ ሚዲያዎች አማካኝነት እና በተሳሳተ የፖሊሲ አተያይ የውጭ ፖሊሲ መርህ ሲጣስ ተስተውሏል ያሉት አቶ ደመቀ መርሆዎች መከበርም አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ከወዳጆቻችን የሚመጣውን ገንቢ ምክረ ሀሳብ በመልካም ጎኑ የምንመለከተው ሲሆን፣ አሁን የገጠምን ፈተና ከኢትዮጵያ አቅም በላይ አይደለም ብለዋል፡፡

በጥፋት ቡድኑ ላይ ኢትዮጵያ የጀመረችውን አርምጃ መደገፍ የቀጠናውን ሰላም መደገፍ ነው ሲሉ አቶ ደመቀ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

በየትኛውም መልኩ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገባን ሀይልን ግን ኢትዮጵያ አትታገሰም ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፡፡

ኢትዮጵያ ከሁሉም ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት ያላት ሲሆን ከሱዳን ጋር ያላትን የድንበር አለመግባባት በዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗንም ገልፀዋል፡፡

የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት የትውልድ ጥያቄን ምላሽ የያዘ እና ከወንዙ ተጠቃሚ ሀገራት ጋር የጀመርነውን ድርድር መርህን ተከትለን ውይይት የምናደረግ ሲሆን ሁሉንም ተጠቃሚ እንዲያደርግ ጽኑ አቋም አለን ብለዋል አቶ ደመቀ መኮንን፡፡

ነገር ግን የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክታችን በቅኝ ግዛት ሌጋሲ እና ጠቅላይነት አይቆምም ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናግረዋል፡፡ EBC

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ዛሬ እኩለ ሌሊት ላይ ያደረጉት ንግግር ዋና ዋና ነጥቦች…‼

👉 የሰው ልጅ ትክክለኛው ክብሩ እና ነጻነቱ የሚረጋገጠው በራሱ ችሎታ መኖር ሲችል ነው፤

👉 ድህነትና በውጭ አገራት ላይ የሚኖር ጥገኝነት የፖለቲካ፣ የአስተዳደር፣ የጸጥታ እና የሰብአዊ ልማት ተግዳሮቶችን ይፈጥራል፤

👉 ከሦስት ዓመት በፊት አገሬ ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጉዞ ጀምራለች፤

👉እኛ ያስተዋወቅናቸው ለውጦች፣ ዴሞክራሲን፣ ሰብአዊ መብቶችን፣ ሰብአዊ እድገትን እና ክልላዊ መረጋጋትን አስከትለዋል፤

👉በተለዩ የፖለቲካ ፍልጎት ባላቸው ቡድኖች መካከልም ለውይይት እና አንድነት መንገዶችን ከፍቷል፤

👉 ለውጡ ያለ ተግዳሮት የመጣ አልነበረም፤ እንደማነኛውም ዴሞክራሲ የእኛም የዴሞክራሲ ሂደት በተግዳሮቶች የታጀበ ነበር፤

👉 በኢትዮጵያ እኩልነትን እንደ ግዞት የሚቆጥሩ ቡድኖች ስርአት አልበኝነትን ለማስቀጠል የሚቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገዋል፤

👉 በእነዚህ የሁከት ጌቶች እጅ ውስጥ በነበርንበት ዘመን ሊታሰቡ የማይችሉ ሰብአዊ ግፎች በዜጎቻችን ላይ ተፈጽሟል፤ ንብረት ወድሟል፤

👉 ይህ ግፍና ሰቆቃ አልበቃቸው ብሎም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይም ጥቃት እስከ መፈጸም ደርሰዋል፤ በዚህ ጥቃትም ሴትና ወንድ ወታደሮቻችን ተገድለዋል፤

👉 መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማስከበር ስራ ሰርቶ ሲያበቃ ሰብአዊ ፍልጎቶችን ለማሟላት እየሰራ በነበረበተ ወቅት እነዚህ አዋኪ ቡድኖች የዜጎችን ስቃይ ማባባስ ቀጥለዋል፤

👉 እነዚህ ወንጀለኛ ቡድኖች የውሸት ፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በማካሄድ እስኪገርመን ድረስ ዓለምን አሳስተዋል፤

👉 እኛ የምንወስዳቸው ጥንቃቄ የተሞላባቸው እርምጃዎች ከገጠመን ህልውና ፈተና ጋር ተመጣጣኝ ናቸው፤

👉 ምንም እንኳን አላስፈላጊ ጫናዎች ቢኖሩብንም ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የፖለቲካ ነፃነት የማስጠበቅን ከባድ ግዴታ እንወጣለን፤

👉 ከወዳጆቻችን የሚደረግን ትብብር በደስታ የምንቀበለው ቢሆንም ትክክለኛና ገንቢ አካሄድን መከተል እንዳለባቸው ልናሰምርበት እንፈልጋለን፤

👉 በውስጥ ጉዳይ ላይ ድጋፍ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት የችግሩን ውስብስብነት ከስር ከመሰረቱ መረዳት ያስፋልጋል፤

👉 ከዚህ ውጭ በውስጥ ጉዳያችን ላይ ለሚደረግ ጣልቃ ገብነት የሚቀርብን ማንኛውንም ምክንያት አንቀበልም አንታገስም፤

👉 አሁን የገጠመች ተግዳሮት በእኛ ግዛት ክልል ውስጥ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፤ ለአካባቢውም የሚተርፍ ነውና ይህንን የአካባቢ ስጋት የሆነ ቡድን ለማስወገድ የሚደረግን ጥረት መደገፍ አካባቢውን መታደግ መሆኑን ማወቅ ይገባል፤

👉 ኢትዮጵያ ምንጊዜም የነጻነት ፋና የሰላም ምልክት ናት፤

👉 ለሌሎች አገራት ስጋት ሆነን የማወቅ ታሪክ የለንም፤ አሁንም ለአካባቢያችን እና ለዓለም መረጋጋት ድጋፋችን ይቀጥላል፤

👉 እኛም በዚህ ወሳኝ የአገራችን ወቅትም ተመሳሳይ ድጋፍን እንሻለን፤ ይገባናልም፤

👉 ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም ከራሳችን ውሃ እንዳንጠጣ ዛቻ እየተሰነዘረብን የፖለቲካ ጉዳይም ሆኖብን በዓለም ፊት አቅርቦናል፤

👉 ግድባችን የሚሊዮኖችን ቤት በብርሃን የሚሞላ የህዝብ ፕሮጀክት ነው፤

👉 በየዘመኑ የነበሩት ትውልዶች ምኞት የሆነው በተፈጥሮ ሀብታችን የመጠቀም ፍላጎት በቅኝ ግዛት ህግና በአንድ ወገን ብቻ ተጠቃሚነት አይገታም ‼

የአቶ ደመቀ መኮንን ሙሉ ንግግር ከስር ተያይዟል። EPD

Leave a Reply