ሔርሜላ – እስከዛሬ የት ነበረች?

ነጻ አስተያየት – By Solomon yami ll September 27. 09. 2021

የሚከተለውን ከታች ያለውን ዜና አነበብኩ። ዜናውን ማህበራዊ ገጾች እየተቀባበሉ ሲያራግቡት ተመለከትኩ። ተዋንያኗ ሔርሜላ የምትባል ከትግራይ የሆነች የሲቢኤስ “ጋጤኛ” ናት። ጉዳዩም የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የትግራይን ሕዝብ የስልጣን መጠቀሚያው አድርጎል በሚል ከድርቅና ረሃብ ትርፍ ፍለጋ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሳ መቃወሟ ወይም ማጋለጧ ነው።

አውራ አምባ ጋዜጣ ሲያዘጋጅ የነበረው ዳዊት ከበደ ሆን ተብሎ ወደ አሜሪካ እንዲወጣ ተደርጎ፣ ሆን ተብሎ የሲፒጄ ሽልማት እንዲሸለም ተደርጎ ( የበረከት ልጆች የሚባሉት እነማን እናዳሸለሙት ይታወቃል) የጀግና ረሃብተኛ የሆነው ዳያስፖራ አነገሰው። በአንቀልባ ተሸክሞ ሚስጢሩ ያለበት ሰፈር ድረስ ወስዶ ቀረቀረው። ከዛም ስራውን ሲጨርስ ወደ ጌቶቹ ሄዶ የሰራው የሚታወቅ ነው። ዛሬም ከመቀለ አዲስ አበባ ተመልሶ ” ደመራው ወዴት ወደቀ?” እያለ ሽሙጥና መርዙን ይረጫል።

ኤርሚያስ ለገሰ በ1997 ዓ.ም ምስኪኖች አናት አናታቸውን እየተወጉ ሲደፉ በቲቪ መስኮት እየወጣ ” አሸባሪዎች” እያለ በምስኪኖች ደም ላይ ሲደንስ የነበረ ባንዳን ዳያስፖራው ሲያሞካሽ ነበር። በገንዘብ እየረዳ ሲሞሽረው ነበር። ወገኖቻችን “ድምጻችን ተነጠቀ ” ብለው ከአውሬው የትህነግ ዓልሞ ተኳሾች ሲደፉ፣ ኤርሚያስ ሲፈጠር “ሽንቱ” እስኪመስል ድረስ ጥፍጥፎ የሰራውን በረከትን ተክቶ በህዝብ ጣርና ለቅሶ ሲዛበት መኖሩ ተዘንግቶ ዳያስፖራው ውስጥ ዛሬ ድረስ የሚያለቀልቁለት አሉ። የመረጃ ቲቪን ባለቤቶች ጨምሮ። ወደፊት ታሪክ ይፈርደዋል።

ብዙ መጥቀስ ይቻላል። ሔርሜላ ከዚህ ሁሉ ሂደት ጋር ለማመሳሰል ወይም ለማወዳደር ሳይሆን በማህበራዊ ሚዲያዎች የነበረው ማህበራዊ ጩኸት ያለፈውን ስላስታወሰኝ ነው። እንደ አንድ ባለሙያ ሄርሜላ የመከላከያ ሰራዊት ሲታረድ የት ነበረች? ትህነግ በራሱ ሚዲያ ማስተባበል በማይችልበት ደረጃ ” በመብረቃዊ ጥቃት በ45 ደቂቃ መከላከያን …” ብለው በምትሰማው ቋንቋ ሲዛበቱ ሄርሜላ ምን ትሰራ ነበር? በተቀጠረችበት ሚዲያ የትኛውን ሚዛናዊ ሪፖርት አቅርባለች? ወይም ለማቅረብ ሞክራ ተከልክላለች? ወይስ ” የተስፋይቱ ምድር ምስረታ” ሲጨናገፍ ነው ትህነግ የትግራይን ሕዝብ እንዳገተው የታያት።

ዛሬ ዘግይታም ቢሆን ይህንን ማናገሯ መልካም ቢሆንም፣ ወደ እውነት ለመመለስ መሞከሯ የሚበረታታና ለሌሎችም ድፍረት የሚሰጥ ቢሆንም ለዚህ አስተያየት ሰጪ፣ ሄርሜላ ከልቧ ወደ ሚዛናዊነት ተመልሳ ከሆነ ቅንጣቢ ሃሳብ ላይ ሳትቸከል ሰፊ፣ ተደጋጋሚና፣ ጥልቅ መረጃዎችን ለትግራይ ሕዝብ ስትል ልታዘጋጅና አየር ላይ ልታውል ይገባል።

ከዚህም በላይ በምትሰራበት ተቋም አማካይነት ወደ መቀለ ሄዳ ህዝብ አናግራና መረጃ ሰብስባ ወገኖቿን በመታደግ ለኢትዮጵያም ሰላም የበኩሏን ልታበረክት ይገባል። በውጭ ሆነው ” ግፋ በለው” የሚሉትን ወገኖችም ቢሆን ዝም ልትል አይገባም። ይህንን ስል በመንግስት በኩልም ያለውን ችግር በሚዛናዊነት ነቅሳ መመልከትን ያካትታል። በዚህ ደረጃ ሙያዊ ካባዋን ለብሳ ካልሰራች በአንድ ጭላፊ አሳብ ይህን ያህል ማራገቡ ልክ አይሆንም። ልክ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ሔርሜላ አይታ አይታ የተባለው አጉል ተስፋና ምኞት ሲመክን ላቅረበችው ” ከደሙ ንጹህ ነኝ” ቅንጣቢ አሳብ አድማቂና አጨብጫቢ ክለመሆን አያልፍም። ሔርሜላም ይህን የምትረዳ ይመስለኛል። ለትግራይ ምስኪኖች ካዘነች ልትገፋበትና የበለጠ ሃላፊነት እንደሚሰማት ልታሳይ ይገባል። ለአስተያየት ያነሳሳኝ የኢዜአ ዜና ከስር ያለው ነው።

መንግስት የወሰደውን ሕግ የማስከበርና የሕልውና ዘመቻ በመተቸት ለአሸባሪው ህውሓት ጠበቃ የነበሩ ታዋቂ ትግራዋይ ጋዜጠኞች እውነትን ወደ መወገን እየመጡ መሆናቸው እየታየ ይገኛል። የሕግ ማስከበር ዘመቻውን በመተቸት ለአሸባሪው ህወሓት ጠበቃ የነበሩ ጋዜጠኞች እውነትን ወደ መወገን እየመጡ ነው።

በተለያዩ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ዘጋቢ በመሆንና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሲቢኤስ የዜና መረጃ መረብ በመስራት ላይ የምትገኘው ታዋቂዋ ኢትዮ አሜሪካዊት ትግራዋይ ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ህዝብ ለስልጣን ጥቅሙ ብሎ እየተጠቀመበት እንደሆነ በትዊተር ገጿ አመላክታለች።

”የኢትዮጵያ መንግስት ጥሩ ሆኖ እንዳይታይ የሽብር ቡድኑ አባላት ሰብአዊ ድጋፉ ለትግራይ ህዝብ እንዳይዳረስ አድርገውታል” ስትል አሸባሪው ቡድን ለስልጣኑ ሲል በትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰ የሚገኘውን መከራ አመልክታለች።

ጋዜጠኛዋ በቅርቡ በለቀቀቻቸው ጽሑፎች “የኢትዮጵያ መንግስት በተናጠል ያወጀውን ተኩስ አቁም አሸባሪው ህወሓት ለምን ጣሰ? ወደ አማራና አፋር ክልሎችስ ወረራ በማካሄድ ንጹሃንን ለመግደልና ውድመቶችን ለመፈጸም ለምን ፈለገ?” ስትል ጠይቃለች።

የተመድ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ወደ ትግራይ የእርዳታ እህል ጭነው ከተላኩት 466 ተሽከርካሪዎች የተመለሱት 38ቱ ብቻ ናቸው ያለውን ሪፖርት አጽንዖት በመስጠት የሽብር ቡድኑ በትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ግፍ አውግዛለች።

“እርዳታ ጭነው የገቡ መኪናዎች አለመመለስ ለምን ሆነ ይህ ለህዝቡ እርዳታው እንዳይሰራጭ አያደርግም ወይ?” በማለት ነው ቡድኑ እየፈጸመ የሚገኘውን ነገር የኮነነችው።

አሸባሪው ቡድን በከፈተው ጦርነት “ምን ያህል ህጻናት እስኪያልቁ ነው የሚጠበቀው” በማለትም ሔርሜላ ትጠይቃለች።

ባለፉት አስር ወራት በትግራይ ተከሰተ የተባለውና የሰማሁት ነገር አይመጣጠንም አሁንም ነገሮችን በተለየ አይን በመመልከት ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ እናምጣ ብላለች።

ወቅቱ በውጭ የምንገኝ ደጋፊዎች ቆም ብለን ራሳችንን የምናይበትና ከጭፍን ድጋፍ ወጥተን መፍትሔ የምናመጣበት ጊዜ ሊሆን ይገባል ስትል ነው ያመለከተችው።

Leave a Reply