” አንዳንድ የአሜሪካና የአውሮፓ የተራድኦ ድርጅቶች የተለያዩ ደባዎችን እየሰሩ ነው “- የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አንዳንድ የአሜሪካና የአውሮፓ የተራድኦ ድርጅቶች ለተፈናቃይ ወገኖች እርዳታ ለማቅረብ ተቀባይነት የሌላቸውን ምክንያቶች እያቀረቡ ነው ብሏል።

በኮሚሽኑ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ-ኢብኮ በሰጡት ቃል፥ የተራድኦ ድርጅቶቹ “ጦርነት ባለበት እንዴት እንገባለን”፣ “የተረጋጋ ሠላም አምጡልን” እንዲሁም “ሃብት የለንም” የሚሉ ተቀባይነት የሌላቸውን ምክንያቶችን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ መርሁ በሚያዘው መሰረት የተራድኦ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ተንቀሳቀሱ ድረስ የኢትዮጵያን ህግ ጠብቀው የሰብዓዊ እርዳታ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው ያሉት አቶ አበበ የተራድኦ ድርጅቶቹ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ገብተው እርዳታ የማቅረብ የውል ግዴታ ቢቀበሉም ተግባራዊ አለመሆኑን ገልፀዋል።

መንግስት የተራድኦ ድርጅቶቹ ገበተው እርዳታ እንዲያቀርቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ የሚፈልጉ አንዳንድ የአሜርካና የአውሮፓ የተራድኦ ድርጅቶች የተለያዩ ደባዎችን እየሰሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ደበበ፥ “ይህን ደባ ለማለፍ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ በወሮታና ኮምቦልቻ በቂ የእለት ደራሽ እርዳታ ክምችት አለ” ሲሉ አስረድተዋል። ችግሮችን በቅርበት ተረድቶ አፈጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችልም የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከለት በባህር ዳር፤ ኮምቦልቻና አፋር ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ማዕከላቱ የጤና፣ ውኃ፣ ምግብና የስነ ልቦና እና የጸጥታ ችግሮችን በቅርበት ለመፍታት እንደሚያስችሉ ነው ለብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃል የጠቆሙት።

Leave a Reply