ኦሮሞና -ኢሬቻ

አረንጓዴ ቅጠል፤ አበባ…ይዞ፤ዋቃን በወንዝ ወይም በሀይቅ ዳርቻ ወይም በተራራ ላይ የማመስገን፤ የማክበር ፤የማምለክ በአል ነው እሬቻ።የፀሎት ቀን ነው እሬቻ


ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን
(ሮቤሳ ቀዌሳ) እንደፃፈው

ከ12,000 አመታት በፊት ነው። ያኔ የኩሽ አምላክ፤ የፀሃይ እና የሰማያት አምላክ ተደርጎ የሚታሰበው አስራ(Osiris-Ka) ነው። ሶስት ልጆች አሉት። ታላቁ ወንድ ልጅ ሴት(Set)፤ ታናሹ ኦራ(Horus) እና እህታቸው አሲስ(Isis)። አሲስ በሌላ ስሟም አቴቴ ወይም አድባር ትባላለች።ልጆቹ የኩሽ ህዝብ በሰፈረበት በኑቢያ እና በጥቁር ምስር በጊዜው አጠራር ከመት/ Kemet ( ወይም ግብጥ) ኑሮ መስርተዋል።

ታላቁ ልጅ ሴት ታናሹን ኦራ በሆነ ቅራኔ ወይም ቅናት ይገድለዋል።እህትዬው አሲስ በጊዜው ወግ (አዝና.. ምናልባትም አልቅሳ… ወይም ማቅ ለብሳ) በናይል ወንዝ አቅራቢያ ኦራን ትቀብረዋልች። ለመታሰብያም የኦዳ ዛፍ መቃብሩ ጎን ትተክላለች።

አሲስ ለገዳይም ለሟችም እህት ናትና የሁለቱ ቤተሰዎች ደም እንዳይቃቡ ትሰጋለች። … (.”ሀዘኔ ቅጥ አጣ፤ ከቤቴም አልወጣ”እያለች ሊሆን ይችላል)…አባቷን ማለትም የፀሀይን አምላክ-አስራን በወንድሞቿ ቤተሰቦች መሃል ሰላም እንዲያሰፍን ትለምነዋለች። አስራ (Osiris-Ka) የአሲስ ፀሎትን ይሰማል። ልመናዋን መስማቱን ለማሳየትም… ዝናብ አዝንቦ የኦዳውን ዛፍ እንደ ድንኳን ዘርግቶ ያሳድገዋል። ያለመልመዋል። ይህም እርቀሰላም ለማውረዱ ምልክት ይሆናታል። ሰንደቅ አላማ!

በየአመቱ መስከረም ሲጠባም የናይል ወንዝ ይሞላል። …ከወንዙ አጠገብ ለኦራ እንደ ሀውልት የተተከለው ኦዳ ዛፍም ይለመልማል። በቤተ ዘመዱ መሀል እርቀሰላም ለመውረዱ መታሰቢያነት በአል መከበር ይጀመራል። ሰላም ያሰፈነውን የፀሀይ
አምላክ ለማመስገን የሟቹ ኦራ መንፈስም አብሮ ይገኛል።(ኦራ ኦሞ…ኦሮሞ ይለዋል ጋሽ ፀጋዬ)

በአሉ ሲከበርም ኢዮ ካ /Eyo Ka/ እየተባለ ችቦ ተይዞ…የፀሀይ እና የሰማይ አምላክ ይወደሳል። ኢዮ ሃ…የሚለው ባህላዊ መዝሙር ከዚያ የተወረሰ ነው። ለኩሽ እንግዳ የሆኑት፤ ክርስትናም ሆነ እስልምና ከመምጣታቸው በፊት ካ(ka) ለኩሽ ህዝብ የአምላክ መጠሪያ አንድ ስም ነው።ዛሬ ባሉት የኩሽ ህዝቦች አምላክን ዋካ(Wa Ka)… ዋቃ (Wa Qa) ወይም ዋቀዮ (Wa-Ka-Ayyoo) ብሎ መጥራት ከዚያ ነው መነሻው። (አካ ሱማ-አክሱም ይለዋል ሌላ ቦታ ጋሽ ፀጋዬ።)

ኢዮ ካ…ኢዮ ሃ… ሲባልም ” ካ” ን ማወደስ ነው። ገዳ (Gada -Gaada)…ወይም ካ አዳ (Kada -Ka Ada) ደሞ የአምላክ ህግጋትን፤ ትእዛዛትን ማከናወን ነው። ከነዚህም አንዱ እሬቻ ነው። አሲስ ወይም አቴቴ ወይም አድባር በተጋደሉት ወንድሞቿ ቤተሰበዎች መሃል ሰላም መስፈኑን በፀሎቷ መልስ ያገኘችበት ነው።… እሬቻ፤ በናይል ወንዝ ዳርቻ የተከለችው የኦዳ ዛፍ ለምልክት ሆኖ የለመለመበት መታሰቢያ በአል ነው።…እሬቻ፤ይህን ሁሉ ላደረገ አምላክ ምስጋና ማቅረቢያ በአል ነው።

በኦሮሞ ዘንድ በገዳ ትዛዛት እየተመሩ የሁሉን ፈጣሪ አንድ አምላክ ዋቃን ማምለክ ዋቄፈና (Wakefena) ይባላል። ዋቄፈና ለኦሮሞ ሃይማኖቱ ነው። እሬቻ የእምነቱ አካል ነው። ህዝቡ ተሰብስቦ ለምለም ቄጠማ፤ አረንጓዴ ቅጠል፤ አበባ…ይዞ፤ዋቃን በወንዝ ወይም በሀይቅ ዳርቻ ወይም በተራራ ላይ የማመስገን፤ የማክበር ፤የማምለክ በአል ነው እሬቻ።የፀሎት ቀን ነው እሬቻ።

.እሬቻ ብዙ አይነት ቢሆንም ዋናዎቹ ሁለት ናቸው።እሬቻ መልካ (Irecha Melka) እና እሬቻ ቱሉ (Irecha Tullu )። …እሬቻ መልካ ፤በውሃ ዳርቻ ክረምት እንደወጣ ይከበራል።ይበልጡን ምድርን በዝናብ ያጠገበውን ዋቃ በምስጋና የመዘከር በአል ነው። …እሬቻ ቱሉ ፤በተራራ ጫፍ ላይ በበጋው መሀል ይከበራል።ዝናቡ እንዳምናው በወቅቱ እንዲመጣ ዋቃ ይለመናል።ይበልጡን የፀሎት በአል ነው።ቢሆንም…ቡራኬው፤ ምስጋናው፤ ፀሎቱ በሁለቱም እሬቻ አይቀርም።

… ለተራራው ወይም ለወንዙ አይሰገድም። እነሱን ለፈጠረ ፤አምላክ ነው የሚሰገደው። በኦሮሞ ባህል ልምላሜ እና ውሃ የአምላክ መንፈስ ማደርያ፤ ንፁህ የአምልኮት ስፍራ ነው። ለፀሎት ምቹ እና ሰላማዊ ቦታ ነው። ..እናም በእሬቻ መልካ በአል…የተፈጥሮን ኡደት ሳያዛባ ያስቀጠለ ዋቃ ይመሰገናል። ዋቃ ይከበራል። ዋቅ ይመለካል::

Leave a Reply