“አገር ሲፈርስ በዝምታ የሚያይ መንግስት የለም፤ ሁሉ አቀፍ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን”

ኢትዮጵያ አገር ሲፈርስ ዝም ብሎ የሚመለከት መንግስት እንደሌላት በማስታወቀ መንግስት ሁሉ አቀፍ ወታደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገደድ ይፋ አደረገ።ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት የተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ኤጀንሲዎች ውስጥ ሲሰሩ የነበሩት ሃላፊዎች ሲያከናውኑ የነበረው ህገወጥ ተግባራት ከበቂ በላይ መረጃ መኖሩ ተመለከተ። የሚሰማና በነጻ ህሊና የሚፈርድ ካለ ሃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው የአንድን ሉዓላዊት አገር ደህንነትና ሰላም በሚፈታተን ደረጃ ተሳትፎ በማድረጋቸው ሊቀጡ በተገባ ነበር።

መንግስት ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው መሰረቱን ሰብአዊነት ያደረገ የተናጠል ውሳኔ ቢወሰንም ትንኮሳውና ሰላማዊ ዜጎችን ማጥቃቱ ባለመቆሙ ነው። ካሁን በሁዋላ የዓለም መንግስታት ይህን ትንኮሳ ማስቆምና ኢትዮጵያን ከድህነት ለመውጣት የምታደረገውን ርብርብ ከበመደገፍ ባሻገር፣ ክፋትና ሽብርን በገሃድ ማውገዝ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ማክበር እንደሚገባቸው በማሳሰብ ነው። ” ይህ ካልሆነ” አሉ የመንግስትን አቋም ያስታወቁት አቶ ሬድዋን፣ ” ይህ ካልሆን ኢትዮጵያ ሁሉ አቀፍ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ትገደዳለች” ብለዋል። አያይዘውም ይህ የሚሆነው በኢትዮጵያ አገር ሲፈርስ ዝም ብሎ የሚመለከት መንግስትና ሕዝብ ባለመኖሩ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዳኤታ ሬድዋን በቪዲዮ በሰጡት መመረጃ ” የምናወቀው በርካታ ማስረጃ አለን” ብለዋል። ጦርነቱ እንዲቆምና የርዳታ ስራው በሚገባ እንዳይከናወን የሚፈለግበት ምክንያት ለመንግስት ግልጽ እንዳልሆነ ያመለከቱት አቶ ሬድዋን በርካታ ጊዚያት ምክር መሰጠቱን አመልክተዋል።

አንዳንድ አገሮችን በማባበል፣ አንዳንዶቹን በማስፈራራት ኢትዮጵያን የማካለብና የማዋከብ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ያመለከቱት አቶ ሬድዋን በርዳታና ከርዳታ ጋር በማያያዝ ሌላን አካል የማስታጠቅ ተግባር ሲከናወን ቆይቷል። መንግስት በተደጋጋሚ መምከሩን ገልጸዋል። አሁን ግን ይህን ማስታመም የማይቻልበት ደረጃ መደረሱን ገልጸዋል።

ከእርዳታ ጋር በተያያዘ አገር ውስጥ ገብተውና ከአገር ውጭ ሆነው ኢትዮጵያን የማጠልሸት ፕሮፓጋንዳ ላይ የተሰማሩ፣ በግልጽ ባይናገሩትም ከትህነግ ጋር የሚሰሩ መሆናቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ወዳጅና አጋር አገራት ኢትዮጵያን እውነት ላይ ተመርኩዘው መደገፋቸውን ታሪክና አገር ትልቅ ክብር እንደምትሰጥ ያመለከቱት አቶ ሬድያዋን፣ ይህ ድጋፍ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ አሁንም ጥሪ ታቀርባለች ብለዋል።

በመለያየት ሊያፈርሱን የሚተጉትን ለመመከት ከወትሮው በላይ አንድ መሆን እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ሬዲዋን ፣ በዚህ አግባብ ጥሪው በድጋሚ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መተላለፉን ጠቁመዋል። ሚኒስትሩ አያይዘውም ” እንደከዚህ ቀደሙ እንዳለፍናቸው በርካታ ችግሮች፣ በምርጫና በግድባችን ያሳየነውን ጥንካሬ ደግመን እናሳይ” ብለዋል።

ችግሩ ብዙ፣ሴራው የተወሳሰበ፣ ወጥመዱ ሰፊ መሆኑንን በመረዳት ህዝብ በመቻቻል፣ በመነጋገርና በመያያዝ ይህን ጊዜ ማለፍ እንዳለበት፣ ከአካባቢ ስሜትና አጀንዳ በመራቅ ነገሮችን አስፍቶ ማየት እንደሚገባው መንግስት ማሳሰቡን አቶ ሬድዋን አስታወቀዋል። ከመንግስት በሚወጣ መመሪያና አቅጣጫ መሰረት ለመጓዝ ትኩረት እንዲደረግም መክረዋል።

ለሰላምና ለሰብአዊነት ሲባል መንግስት ፖለቲካዊ እርምጃ ወስዶ ተኩስ አቁም ማወጁ ዋጋ እንዳስከፈለው ያመለከቱት አቶ ሬድዋን፣ ካሁን በሁዋላ ሕዝብ ሰላሙን እንዲያጠብቅ፣ ዓለም እውነቱን ተረድቶ ክፋትንና ሽብርን እንዲያወግዝ መንግስት ማሳሰቡት አመልክተዋል። አያይዘውም ሚኒስትሩ ” አገር ሲፈርስ ዝም ብሎ የሚመለከት መንግስት የለም” ሲሉ በማብራሪያቸው መጨረሻ አስታውቀዋል።

” በየትኛውም ዓይነት ሰበብና ምክንያት አገር አገር እንዲፈርስ አይፈቀድም” ሲሉ ያስታወቁት አቶ ሬድዋን፣ መንግስት ከዚህ በሁዋላ ሁሉን አቀፍ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ይፋ አድርገዋል። መንግስት ሁሉን አቀፍ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ይፋ ያደረጉት አቶ ሬዲዋን፣ ይህ እንዳይሆን ኢትዮጵያ ደጋግማ ለምናለች፣ ለሰብአዊነት ሲባል ዋጋ መክፈሏን ደጋግመው አመልክተዋል። በሚያሳዝን መልኩ ግን ይህን ድካሟን እውቅና ሰጥተው በበጎ ያደነቁ ጥቂት ናቸው።

በተመሳሳይ ዜና አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ውሳኔውን ለሌሎች ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ አመልክተዋል። ከኢፕድ የተዋስነውን ዜና ከስር እንዳለ አቅርበነዋል።

“ሀገር ለቀው እንዲወጡ በታዘዙ የውጭ ዜጎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰነ፣ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው” – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩና ከተሰማሩበት ዓላማ ውጪ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ሰባት የውጭ ዜጋ ሠራተኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰነ፣ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡

በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ 7 ሠራተኞች በ72 ሰዓታት ውስጥ ከሀገር እንዲወጡ የኢትዮጵያ መንግሥት ማዘዙን ተከትሎ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ግለሰቦቹ ከሀገር እንዲወጡ የታዘዙት ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጪ ሲንቀሳቀሱና በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው።

እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፣ ማንኛውም ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋምም ሆነ ግለሰቦች ሲገቡ ፈቃድ አላቸው፤ የሚሰሩትም በፈቃድ ነው። የትኛውም ተቋም እና ግለሰብ ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ከተገኙ ተግባሩ ሕገ-ወጥ ነው፤ ከሀገር እንዲወጡ በታዘዙት ግለሰቦች የሆነውም ይኸው ነው፡፡

“አንዳንዱ ለሕክምና ሥራ እና ለጤና አገልግሎት ይመጣና፣ ጤናን በሚያዛቡ እና የኅብረተሰቡን ሰላም በሚያደፈርሱ ተግባራት ላይ ይሰማራል፤ ለውኃ ቁፋሮ ይመጣና ሀገር ሲቆፍር ይውላል፤ ይህ ዓይነት ተግባር ደግሞ በየትኛውም ሀገር አይፈቀድም፤” ያሉት አምባሳደር ዲና፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌላም ሀገር የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት፣ የአንድን ሀገር ደህንነት፣ የአንድን ሀገር ሰላም የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ክልክል መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

መንግሥት ደግሞ እነዚህን ኃይሎች የማስቆም ኃላፊነት ያለበት እንደመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃም በዚህ መሠረት የተወሰደ ነው ሲሉ አስረድተዋል። እነዚህ አካላት ይማራሉ፣ ከስህተታቸው ታርመው ይመለሳሉ በሚል መንግሥት ትዕግሥት ማሳየቱን አመልክተዋል። ይህ መልካም ቢሆንም እነርሱ ይህን ተገንዝበው ያለመታረማቸው አሳዛኝ ነው፤ በመሆኑም ከዚህ ሁሉም ትምህርት ሊወስድበት ይገባል ሲሉ አምባሳደር ዲና መናገራቸውን የዘገበው ኢፕድ ነው።

Leave a Reply