ጉተሬዝ”ሰራተኞቻችንን እናምናለን” አሉ፤መረጃና ማስረጃ አለኝ- ኢትዮጵያ

የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ሊመክር ነው። የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያ የድርጅቱን ከፍተኛ ሰብዓዊ አስተባባሪዎች ጨምሮ ሰባት የድርጅቱን ሰራተኞች ለማባረር መውሰኗን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ” ደንግጫለሁ” ሲሉ አስታወቁ። አዲስ አበባ የተቀመጠው የአሜሪካን ኤምባሲ በበኩሉ ውሳኔውን በማውገዝ ዋይት ሃውስ ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድ የሚል መልዕክት አስተላፈዋል። ሌሎችንም ጋብዘዋል። ኢትዮጵያ በበኩሏ ከበቂ በላይ መረጃና ማስረጃ እንዳላት፣ ከልክ በላይ በመታገስ መምክረሯን፣ ከዚህ በላይ በመታገስ አገር ሲፈርስ ዝም ማለት እንደማትችል አስታውቃለች።


ይህን ያንብቡ – አገር ሲፈርስ በዝምታ የሚያይ መንግስት የለም፤ ሁሉ አቀፍ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን


ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ አቤቱታ ስታቀርብና እርዳታና ስውር ደባ እየተቀላቀሉ መሆኑንን በማመልከት ሚዛናዊ ብይን እንዲኖር ስትጠይቅ ዝምታን የመረጡት ዋና ጸሃፊው ሁኔታውን በማስመልከት በቃል አቀባይ ጽህፈት ቤታቸው በኩል ባስተላለፉት መግለጫ እንዳሉት ኢትዮጵያ የድርጅቱን ከፍተኛ ሰብዓዊ አስተባባሪዎች ጨምሮ ሰባት የድርጅቱን ሰራተኞች ለማባረር መወሰኗን በመስማታቸው ደንግጠዋል።

“ሁሉንም ሰብዓዊ ተግባራት በሰብዓዊነት፣ ያለ አድልዖ፣ በነጻና ገለልተኛነት መርሆዎች የሚመሩ ናቸው” ሲሉ ያስታወቁት ጉተሬዝ፣ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒቶችን ጨምሮ ህይወት አድን ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ኢትዮጵያ በበኩሏ እርዳታ መደረጉን ሳይሆን ጎን ለጎን በርዳታ ስም የማስታጠቅ፣ ልዩ ድጋፍ የመስጠት፣ በተናበበ መልኩ አዲስ አበባ ተቀምጠው የተዛባ መረጃ በማስተላለፍ፣ ኢትዮጵያን በማጠልሸትና በመረጃ የተያዙ በዓለም ዓቀፍም ሆነ በአገሪቱ የማይፈቀዱ ተግባራት ላይ መሳተፋቸውን ለይታ ነው የተቃወመችው። የመንግስት ሃላፊዎች በገሃድ እንዳሉት መረጃም ማስረጃም አለ።

ኢትዮጵያ ይህን ብትልም “የተመድ የኢትዮጵያ ስታፍ አባላት ላይ ሙሉ መተማመን አለኝ” ሲሉ ጉቴሬዝ አስታውቀዋል። ድርጅታቸው ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን አሁንም ተባባሪ ለመሆን ቁርጠኛ መሆኑንም አመልክተዋል። ጉተሬዝ በድርጅታቸው ሰራተኞች ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ሲያስታወቁ ከኢትዮጵያ ወገን አለ የተባለውን መረጃ ለመመርመር ወይም ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በይፋ እንዳስታወቁ ተደርጎ እንደሚቆጠር ነው የተመለከተው።

ጉተሬዝ ሰራተኞቹ ስራቸውን በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸው በመግለጫው ተመልክቷል። ይህን አስመልክቶ እስካሁን በኢትዮጵያ በኩል የተባለ ነገር የለም። ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ያለቻቸውን ሰባት የድርጅቱን ሰራተኞች በ72 ሰዓታት ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ከማዘዟ በስተቀር በንግግር እንዲቆዩ የቀረበውን ጥያቄም ሆነ ተመሳሳይ ጉዳይ አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ሁለት መግለጫና ማብራሪያ ያለው ነገር የለም። ይልቁኑም አጉልቶ ያቀረበው መረጃና ማስረጃ በመያዝ ውስኔ ላይ መድረሱን ነው።

በተመሳሳይ ዜና ኢትዮጵያ በ72 ሰዓታት ከሀገሪቱ እንዲወጡ ያዘዘቻቸውን ሰባት የተመድ ግለሰቦች ጉዳይ መነጋገሪያነቱ አጀንዳ ሆኗል። አሜሪካ ውሳኔውን በገሃድ ተቃውማለች።

ኢትዮጵያ የተመድ ሠራተኞችን ከአገር ለማስወጣት የወሰነችው፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ ነው የሚል የማስጠንቀቂያ ሪፖርት ከወጣ በኋላ መሆኑንን አሜሪካ እንደ አንድ ጉልህ የመቃወሚያ ፍሬ ሃሳብ አንስታለች። በትህነግ ወረራ ሳቢያ ለስቃይና ለንግልት ብሎም ለረሃብ ስለተጋለጡ የአማራና የፋር ክልል ነዋሪዎች አሜሪካ አልተነፈሰችም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በአፋጣኝ ውይይት እንደሚያደርግ ተሰምቷል። የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላ ሪቬየር ይህን ተናግረዋል። በተመድ የአየርላንድ አምባሳደር ጄራልዲን ባይረን ኔሰንም ስብሰባው በጣም በቅርቡ ይካሄዳል ብለዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ የተለያየ ስብሰባ ቢያካሂድም አቋም መያዝ እንዳልቻለ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ የህዝቡን ፍላጎትና ውሳኔ አክብሩ በሚል በተደጋጋሚ ማስታወቁ አይዘነጋም።

Leave a Reply