ፈጣሪ ኢትዮጵያን ከፍ ሲያደርጋት በምድሯ በሰው እጅ ያልተቀረጸ፣ በጥበበኞች እጅ ያልታነጸ መስቀል ሠራላት፣ በመስቀሉም ቃል ኪዳን ሰጣት፣ የዘለዓለም በረከት ተወላት። ኢትዮጵያ የሙሴ ጽላት የተሰጣት፣ መስቀሉ ያረፈባት፣ ደሙ የተጠራቀመበት ቅዱስ ጽዋ ያለባት፣ ሰው እና መላእክት የሚጠብቋት፣ በምድር የተሰጠው በረከት ሁሉ የተሰጣት ልዩ ሀገር ናት። በየቀኑ የፈጣሪ ስም እየተነሳባት፣ የቅዱሳን በረከት እያረፈባት ለዘለዓለም ትጸናለች።

ለምስክርነትም ትቀመጣለች። ለመከራው ቀን ማለፊያ ተመርጣለችና። ከተራሮች ሁሉ የከበረች፣ እግዚአብሔር ክብሩን ሊገልጥባት፣ የመረጣት፣ ያከበራት፣ አስቀድሞ ያዘጋጃት፣ በቅድስና የጠበቃት፣ የቀደሳት ታላቋ ተራራ። በዚያች ሥፍራ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም የፈሰሰበት፣ አጥንቱ የተከሰከሰበት፣ ብርሃን የተገለጠበት፣ የጨለማ ዘመን የተቋጨበት፣ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት መስቀል ተቀምጦባታል። መስቀል አድርጎ የፈጠራት፣ መስቀሉን ያኖረባት፣ በረከቱን ያስቀመጠባትም ናት። እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ከግብፅ ባርነት ወጥተው ወደ ምድረ እርስት ተጓዙ፤ ፈጣሪም በተራራ ላይ እየተገለጠ ያናግራቸው ነበር።

ግሸን ማርያም

የሲና፣ የጽዮንና የታቦር ተራራዎች ተጠቃሾች ናቸው። በሲና ተራራ ተገለጠ፣ ትዕዛዛቱንም ለሙሴ ሰጠ፣ በታቦር ተራራ መለኮቱን ገለጠ፣ በግሸን ደብረ ከርቤ አምባሰል ተራራ መስቀሉን አስቀመጠ፣ ብርሃንንም ገለጠ። በታላቋ ምድር በኢትዮጵያ አፄ ዳዊት ነግሠው በነበረበት ዘመን፣ በግብጽ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች የከፋ በደል ይደርስባቸው ነበር። የበደል ፅዋ የበዛባቸው ግብፃዊያን ክርስቲያኖች በታላቋ ምድር የነገሠው ታላቁ ንጉሥ ያድናቸው ዘንድ ተማፀኑት። ንጉሡ ዳዊትም ከመኳንንቱና ከመሳፍንቱ ጋር መከሩ። ሊዘምቱም ወደዱ። ብዙ ፈረሰኛና እግረኛ ጦራቸውን አሰልፈው የተበደሉትን ነፃ ሊያወጡ ዘመቱ። ይህን የሰማው የዘመኑ የግብጽ ንጉሥ ተሸበረ። ንጉሡ ዳዊት ሠራዊታቸውን አስከትለው ወደ ሱዳን አቀኑ። በዚያም ሲደርሱ ከጦርነት ይልቅ ዓባይን መገደብ ይሻላል ተብሎ ተመከረ።

May be an image of tree and nature
ግሸን ዛሬ

ግብጽ በዓባይ የበቀለች ተክል ናትና። የግብጽ ንጉሥ ተሸበረ፣ ጳጳሳቱን ፈታ፣ ክርስቲያኖችን ለቀቀ፣ በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ የመተማመኛ አዋጅ አስነገረ፣ በኀያልነቱ ሲመካ ከእርሱ የበለጠ ኀያል ከኢትዮጵያ ተነስቶበታልና። ለአፄ ዳዊትም የእጅ መንሻዎችን ላከ፣ ይማሩኝ፣ ይቅር ይበሉኝ ሲል። ብልሁ ንጉሥ ከስጦታዎች ሁሉ አንድ ስጦታ ላይ ልባቸው ከጀለ። በእስክንድርያ የሚገኘውን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልን መቀበል። እንደተመኙት አደረጉት፣ መስቀሉን ይሰጧቸው ዘንድ ጠየቁ። በግብጽ ታላቅ ምክር ተደረገ።

አለመስጠት ግን አልተቻለም። ታላቁን መስቀል በወርቅ ሳጥን አድርገው ለንጉሡ ይሰጡ ዘንድ ወደዱ። ሰጧቸውም። ንጉሡ ዳዊት ለሀገራቸው የተፈቀደውን መስቀል ተቀበሉ። መስቀሉን ይዘው በታላቅ አጀብ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ስናር በተባለ ስፍራ ሲደርሱ አረፉ። ታላቁን ስጦታ አይተው፣ በእጃቸው አስገብተው፣ መንፈሳቸውን አርክተው፣ ዓለምን ተሰናበቷት። በንጉሡ መሞት ምክንያት መስቀሉ በስናር ከረመ። በገዳም ውስጥ ይማሩ የነበሩት የብልሁ ንጉሥ ልጅ ዘርዓያዕቆብ ያባታቸውን ዙፋን ተረከቡ።

ወደ ስናርም አቀኑ። መስቀሉን እና እልፍ ንዋየ ቅድሳትን ይዘው ወደሀገራቸው ገቡ። ፈጣሪም መስቀሉን በመስቀልኛ ቦታ ያኖሩ ዘንድ በራዕይ ነገራቸው። አፄ ዘርዓያዕቆብም መስቀሉን አሸክመው ኢትዮጵያን አሰሱ። በእግዚአብሔር መላዕክ እየተመሩ ሀገሪቷን ዞሯት። አበው መስቀሉ ከአውራጃ ወደ አውራጃ ሲዞር በምስጢር ሀገሪቱን እየባረከ ነበር ይላሉ። መስቀሌን በመስቀለኛ ሥፍራ አስቀምጥ የሚለው ራዕይ እየደጋገመ ይታያቸው ጀመር። ዘርዓያዕቆብ ሱባዬ ያዙ፣ ፈጣሪም መስቀለኛውን ተራራ ግሸን ደብረ ከርቤን ገለጠላቸው።

ከሀገረ እስራኤል ኢየሩሳሌም ሮማውያንን የሸሹ ሰዎች በየመን በሀገረ ናግራን ይኖሩ ነበር። በዚያ ምድር ዓለምን ንቀው የሰማዩን እርስት የሚሹ አንድ ፃዲቅ መነኩሴ ይኖሩ ነበር። ሰውየው የቀደመ ስማቸው ፍሊክስ የኋለኛው ስማቸው ደግሞ ፈቃደ ክርስቶስ ይባሉ ነበር። ከቅዱሱ መናኝ ጋርም ሁለት ጽላቶች ነበሩ፣ የእግዚአብሔር አብና የቅድስት ድንግል ማርያም። ማርያምም ለቅዱሱ አባት በራዕይ ተገለጠችላቸው። ጽላቶቹን ይዘው የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ ወደሚታይበት ሀገር ይሄዱ ዘንድ ነገረቻቸው። የተባሉትን አደረጉ።

12 መነኮሳትን አስከትለው በራዕይ ወደታዬቻቸው ምድር ገሰገሱ። የብርሃን አምድ የተተከለባት ምድር ደረሱ። ፈቃደ ክርስቶስ ሆኖ የበሽሎን ወንዝ ተሻግረው ወደ ተራራው አቀኑ። ተራራው ከሁሉም ተራራዎች ይለያል። ወደላይ ሊወጡ ሲሉ ገደሉን ንብ ሠፍሮበት ነበር። የንቡ ብዛት የማሩ ሰፈፍ ያስደነቃቸው ቅዱስ መናኝ ይህስ አምባአሰል ነው አሉ። አሰል ማለት በአረበኛ ማር ነው። የማር አምባ ሲሉ አምባሰል አሏት። በመስቀል የተቀረጸ ምድር፣ የመናንያን፣ የባሕታዊያን የቅዱሳን፣ የበረከት ሀገር አምባሳል። ፈቃደ ክርስቶስ ወደ ተራራው የምታስወጣቸው አንዲት መንገድ አግኝተው ተከታዮቻቸውን አስከትለው ወደ ተራራው ወጡ።

በዚያም ቤት ሰርተው እንደታዘዙት ሁለቱንም ጽላቶች በመስቀለኛው ተራራ ላይ አስቀመጧቸው። በዚያ ዘመን በኢትዮጵያ ምድር አፄ ካሌብ ነግሠው ነበር። ፈቃደ ክርስቶስ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው አስቀድሞ በየመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችን ሰቆቃ የሰሙት አፄ ካሌብ ከዘጠኙ ቅዱሳን መካከል አባ አሌፍና አባ ጉባ በተባሉ ቅዱሳን መሪነት ወደ የመን ሰው ልከው እንደነበርም ይነገራል። በየመን የነበረውን ሰቆቃም አብርደዋል፣ በግፍ የነበሩትን ነፃ አውጥተዋል ይላሉ። አፄ ካሌብ በመስቀለኛዋ ተራራ ቤተመቅደስ አሳነጹ።

ቤተ መቅደሱን አከበሩ። ዘመን ዘመንን ተካ። አፄ ዘርዓያዕቆብ ነግሠው መስቀሉን የተቀበሉበት ዘመን ደረሰ። ዘርዓያዕቆብም ከስናር ያመጡትን መስቀል በዚያ ቦታ ያስቀምጡት ዘንድ ተነግሯቸው ነበርና መስቀሉን ለካህናቱ አሸክመው፣ በጳጳሳቱ እየተመሩ፣ በሠራዊቱ እየታጀቡ፣ በእልልታና በሆታ ወደ ላይ ወጡ። በተራራውም አስቀመጡት። ቤተ መቅደስም አሳነጹ። በወረሃ መስከረም በ21ኛው ቀን በ1449 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ ከበረ። መስቀሌን በመስቀለኛው ሥፍራ አስቀምጥ ያለው ራዕይ ተፈፀመ። ፈጣሪም ቅዳሴ ቤቱ ሲከብር ኢትዮጵያን ባረካት፣ ከፍ ከፍ አደረጋት። የዘለዓለም ቃል ኪዳን ሰጣት። የማይለወጥ የማይናወጥ ቃል ኪዳን። ግሸን ታላቋ ምድር በልዩ ልዩ ሥያሜዎች ትጠራ ነበር።

ደብረ ነጎድጓድ ፣ ደብረ እግዚአብሔር፣ ደብረ ነገሥት ትባል ነበር። ግማደ መስቀሉ ሲገባ ደግሞ ደብረ ከርቤ ተብላ ተጠራች። በቀደመው ዘመን በታላቋ ተራራ የካህናትና የነገሥታቱ ልጆች ጥበበ ስጋን ከጥበበ ነብስ ጋር እያዋሃዱ ይማሩበት ነበር። ነገሥታቱ ይማጸኑበታል፣ በረከት ይለምኑባታል፣ ልጆቻቸውን የቤተመንግሥት ሥርዓት ያስተምሩባታል። በዚያች ሥፍራ የኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ ከለሜዳ፣ ሐሞት የጠጣበት ሰፍነጉ፣ የተገረፈበት ጅራፉ፣ የታሠረበት ገመዱ፣ የድንግል ማርያም የእናቷ የሀና፣ የአባቷ የእያቄም፣ የሀዋርያው የበርቶሎሚዎስ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዘልዳ፣ ሄሮድስ ያስጨረሳቸው ሕፃናት፣ የአርሴማ እና የሌሎች ቅዱሳን አፅሞች፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ የፈረሱ ጭራና እልፍ ምስጢራት በተቀደሰው ምድር ይገኛል ይላሉ አበው።

በሌላው ዓለም የሌለ በተከበረው ተራራ በግሸን ‟መፅሐፍ ጤፉት“ የተሰኘ ታላቅ መፃሕፍም ይገኛል። በየዘመናቱ የተነሱ ነገሥታት ያበረከቱት ሥጦታም በዚህ በተቀደሰው ምድር ይገኛል። አበው ሃይማኖት አስቸጋሪ መንገድ ናት በመንገዷ ተጉዘው ሲደርሱ ግን መዳረሻዋ ያምራል ይላሉ። ግሸንም እንደዚያ ነው መንገዷ አስቸጋሪ ነው መዳረሻዋ ግን ያመረ ነው። ክርስቶስ ይህች ቦታ እኔ ተወልጄ ያደኩባትን ኢየሩሳሌምን፤ የተሰቀልኩባትን ቀራንዮን፤ የተቀበርኩባትን ጎልጎታን እያሰበ በዚህች ቦታ እየመጣ የሚማጸነውን ሁሉ ቸርነቴ ትጎበኘዋለች፤ ጠለ ምሕረቴም አይለየውም ብሎ ቃል ኪዳን ሠርቶባታል ይላሉ አበው፡፡

ይህን ቃል ኪዳን ለመቀበል ልባቸው የፈቀደና የወደዱ ምዕመናን ቅዳሴ ቤቷ በከበረባት ቀን ከመስቀሉ በረከት ሊቀበሉ ወደመስቀለኛው ተራራ ይወጣሉ። በአንድነት፣ በአንዲት መንገድ፣ ወደ አንድ ተራራ ይወጣሉ፣ በመስቀሉ ግርጌ በአንድነት ይሰባሰባሉ። በአንድነት በረከት ይቀበላሉ። የተቀደሰችው እና የተመረጠችው ግሸን እንደርሷ ሆኖ የተፈጠረ፣ እንደ እርሷ ሆኖ የከበረ የለም። በረከቱን መቀበያው ቀን ደርሶም፣ በረከቱን የሚሹ ሁሉ ወደሥፍራው አቅንተው እየተባረኩ ነው።

በታርቆ ክንዴ – ደሴ፡ መስከረም 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ)

Leave a Reply