በሁለት ወር 700 ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር ከዲያስፖራ ተገኝቷል

በሁለት ወራት ብቻ ከዳያስፖራው ከ668 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የ2014 በጀት የመጀመሪያ ሩብ አመት አፈፃፀምን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ባለፉት ሁለት ወራት (ሃምሌ እና ነሃሴ) ብቻ ከዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ ተልኮ ከ668 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ (ሬሚታንስ) መገኘቱን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ 4 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ዳያስፖራው በተለያዩ የልማትና የድጋፍ ስራዎች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በሶስት ወራት ውስጥ ዳያስፖራው ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በስጦታና በቦንድ ግዥ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። በተመሳሳይ ወራት ዳያስፖራው ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ59 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ዳያስፖራው መለገሱንም ጠቅሰዋል። የዳያስፖራው ተሳትፎ ለአጠቃላይ አገራዊ ፕሮጀክቶች ግንባታና የልማት ስራዎች እየተጠናከረ መምጣቱን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply