‹‹ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ማካተት አንዱ የሰላም ምንጭ ነው›› -የሃይማኖት መሪዎች

በምስረታ ላይ ባለው አዲስ መንግስት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለማካተት እየተደረገ ያለው ጥረት አንዱ የሰላም ምንጭ በመሆኑ መለመድና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሰጡ የሃይማኖት መሪዎች ገለጹ። አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በአገሪቱ ላይ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የደብረ ቢታንያ አቡነ ተክለሃይማኖትና ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መላዕከፀሐይ ጸጋዬ ሀዲስ እንደገለጹት፤ አገሪቱ ላይ እየታየ ያለው የሰላም መጥፋት በእጅጉ አሳሳቢ በመሆኑ መንግስትም ሆኑ ሌሎች ፓርቲዎች ለአገር ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋል። እየተመሰረተ ባለው አዲስ መንግስት ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን ማቀፍና ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ሥራ አንዱ የሰላም ምንጭ በመሆኑ ሊለመድና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ብዙ ሀብትና ለዓለም ሊተርፉ የሚችሉ ምሁራን ያላት ባለፀጋ አገር ብትሆንም ሀብቷን በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተጠቀመችበት ያስታወሱት አስተዳዳሪው፤ የሚመሰረተው መንግስት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠትና ህዝቡን አስተባብሮ በመምራት አገሪቱ ያላትን ሀብት በአግባቡ እንድትጠቀም ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች አልፋ የመጣች በመሆኗ ህዝቡ ዘላቂ ሰላምና እረፍት ስለሚያስፈልገው በመደማመጥና በመነጋገር ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ የህዝቡ ትኩረት ወደ ልማት እንዲመለስ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በሌላም በኩል አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ከሁሉም በፊት ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ዑለማ ምክር ቤት አባልና የሰላም ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሀመድ ሲራጅ ገልጸዋል።

ሼህ መሀመድ ሲራጅ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ሰላም ከሌለ ልማት ማልማትም ሆነ ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ስለማይቻል የሚመሰረተው መንግሥት ቅድሚያ ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ሰላም ባልተረጋገጠበት የሚሰሩ ሥራዎች ሁሉ ዋጋ አይኖራቸውም ያሉት ሼህ መሀመድ፤ ሰላም ከአንድ አቅጣጫ ይመጣል ብሎ መፈለግ አግባብ ስላልሆነ መንግሥት ከሚሰራው ሥራ በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን ወደ ስልጣን ለማምጣት እየተሰራ ያለው ሥራ መንግሥት በሰላም አጀንዳ ላይ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፤ ፓርቲዎችም መፎካከርም ሆነ ወደ ኃላፊነት በመምጣት ህዝብን ማገልገል የሚቻለው በአገሪቱ ላይ ሰላም ሲሰፍን መሆኑን ተገንዝበው የተከፈተውን እድል በመጠቀም ለአገር ሰላም የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ሉተራን ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንት ቄስ ሙሴ አላዛር በበኩላቸው፤ ፓርቲ በጊዜ ሂደት ሊቀየር አልያም ሊጠፋ ይችላል። አገር ግን የማትለዋወጥ የጋራ ሀብት በመሆኗ ከመፎካከር ባለፈ በመቀራረብና በመነጋገር በጋራ መስራት ያስፈልጋል። እየተመሰረተ ባለው የመንግስት አስተዳደር ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማካተት ያላቸውን እውቀትና ልምድ ለአገር ጥቅም እንዲያውሉ ማድረግ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የአብሮነትና የአንድነት ስሜት ለመሸርሸርና ለማጥፋት ከተለያዩ አቅጫዎች ጥረቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ስልጣን ህዝብን ለማገልገል የሚሰጥ ትልቅ ኃላፊነት በመሆኑ የሚመሰረተው መንግስት የሰላም መረጋገጥና የህዝቦች ደህንነትን ማረጋገጥ የመጀመሪያ ሥራው ማድረግ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

የአገር ሰላም ለመንግስት ብቻ የሚተው ሥራ ባለመሆኑ የእምነት አባቶችም ሆኑ መላው የአገሪቱ ህዝብ ጣታችንን ወደ ሌላው መጠቆም ሳይሆን የየድርሻችንን በመወጣት በኢትዮጵያ ውስጥ የምንመኘው አይነት ሰላም እንዲሰፍን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መድህን ማህበራዊ አገልግሎት ማዕከል ውስጥ አገልጋይ የሆኑት ሲስተር ስንቅነሽ ገብረማርያም እንደሚሉት፤ አዲስ የሚዋቀረው መንግስት ከምንም በላይ አስተማማኝ ሰላም ማስፈንና ሰው ወጥቶ ሲገባ ለህይወቱ ዋስትናና መተማመኛ እንዲኖረው መስራት አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ የመንፈስ፣ አካልና ሀብት ስብራት ስለደረሰበት ሁላችንም ከመንግስት ጋር ተረባርበን አገራችንን ወደ ጽኑ ሰላም መውሰድ አለብን ብለዋል።

ህዝቡ የፍቅርና አንድነት ትልቅ ፍላጎት አለው ያሉት ሲስተር ስንቅነሸ፤ ሆ ብሎ በአንድነት የተነሳውም ይህንን ፍቅርና አንድነት ለማምጣት ስለሆነ የሚመሰረተው መንግስትም ይህን የሚያግዝና ከሁሉም ጋር ተጋግዞ የአገሪቱን ሰላም እና የህዝቦችን ደህንነት የሚያረጋግጥ እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

You may also like...

Leave a Reply