“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ፈሪሓ እግዚአብሔር ከሌላቸው ሰዎች እጅ አላቀዋል”

አባ መርቆሪዮስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን “እንኳን ደስ አለዎት” አሉ- “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ፈሪሓ እግዚአብሔር ከሌላቸው ሰዎች እጅ አላቀዋል” ብለዋል

አባ መርቆሪዮስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሰየማቸው “እንኳን ደስ አለዎት” አሉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባት አባ መርቆሪዮስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ከሌሎች ብጹዓን አባቶች ጋር በመሆን ዛሬ ደስታቸውን ገልጸዋል።

“የእንኳን ደስ አለዎት” መልዕክቱን አባ መርቆሪዮስ በተገኙበት ብጹዓን አባቶች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጽህፈት ቤታቸው በንባብ አቅርበዋል።

በዚሁ ወቅት ብጹዕ አቡነ መርቆሪዮስ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ፈሪሓ እግዚአብሔር ከሌላቸው ሰዎች እጅ አላቀዋል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፉት የመሪነት ዘመናቸው በኢትዮጵያ ላይ የተደቀኑ ዘርፍ ብዙ ችግሮችን መቀልበሳቸውን አመልክተዋል።

በመልዕክቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለሁለት ተከፍላ የቆየችውን ቤተክርስቲያን አንድ እንዳደረጉ አስታውሰው፤ “የኢትዮጵያን መልከዓ ምድር አረንጓዴ ማልበስ ችለዋል” በማለት ጥረታቸውን አድንቀዋል።

አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን የኢትዮጵያን ክብርና ልዕልና የማስጠበቅ ተግባራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀው፤ ቤተክርስቲያኗም በጸሎት እንደምታግዛቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በቀጣይ በስጋት ውስጥ ያሉ ቅርሶችን የማዳንና የተፈናቀሉ ዜጎችን የመታደግ ስራ እንደሚሰሩም እምነታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በበኩላቸው ”ለተሰጠኝ ቡራኬ ደስተኛና ትልቅ አክብሮት አለኝ” በማለት የብጹዓን አባቶቹን የደስታ መልዕክት ተቀብለዋል።

ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ ያለፈች አገር መሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አሁንም የገጠማትን ፈተና ታልፈዋለች፤ ታሸንፋለች” ብለዋል።

አባቶች በጸሎታቸው እንዲያግዟቸው የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ”የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተቋም ናት፣ ሁሉንም እኩል እንደምታገለግል ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

(ኢዜአ)

Leave a Reply