«ከዚህ ሃላፊነት ውጪ ቢሰጠኝ ኖሮ አልቀበልም ነበር» የትም.ሚ ብርሃኑ ነጋ

“የተሾምኩበት በትክክለኛው ቦታ ነው፣ከዚህ ሃላፊነት ውጪ ቢሰጠኝ ኖሮ አልቀበልም ነበር” ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው የሚንስትሮች ሹመት የትምህርት ሚንስትር ሆነው የተሾሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተሾምኩበት በትክክለኛው ቦታ ነው፣ከዚህ ሃላፊነት ውጪ ቢሰጠኝ ኖሮ አልቀበልም ነበር ብለዋል፡፡

ይህንን ሃላፊነት እንደማገልገል ከወሰድነው ከዚህ መስሪያ ቤት ውጪ ሌላ ሃላፊነት ቢሰጠኝ አልወስድም ነበር፡፡ ትምህርት በፍቅር የሚሰራ ስራ ነው፡፡የትምህርት ሚንስቴርም ትልቅ ተቋም ነው የተሰጠኝም ሃላፊነት ትልቅ ሹመት ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

ሹመቱንም በዛሬው እለት እንደ ሌላው ሰው ነው የሰማሁት ያሉት ፕሮፌሰሩ፣እድሜ ዘመኔን በማስተማር ስራ ላይ ነው ያሳለፍኩት፣ምናልባት ፔዳጎጂ እንደመስፈርት ይቆጠር እንደሆነ አላውቅም ብለዋል፡፡

የአገሪቱን ቀጣይ እጣ ፈንታ ለመወሰን ሁለት ጉዳዮች ከግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ያነሱት ፕሮፌሰሩ እነዚህም የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ ማሻሻል እና ትውልዱን በትምህርት ማነፅ ነው ብለዋል። አክለውም ላለፉት 40 ዓመታት በችግር የተተበተበው የትምህርት ዘርፍ የሚጠበቅበትን መስራት አልቻለም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችን ነው የካቢኔያቸው አባላት አድርገው በዛሬው እለት ሾመዋል፡፡

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበር ቀጄላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል፤ ቃለ መሃላም ፈጽመዋል፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል

«ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት በመስጠት ዕውቀት መር ትውልድ ለመፍጠር ይሰራል»

“በኢትዮጵያ ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት በመስጠት ዕውቀት መር ትውልድ ለመፍጠር እንሰራለን” ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባዋቀሩት ካቢኔ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

ከሹመታቸው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ “በኢትዮጵያ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና ጥራቱን ለማስጠበቅ በልዩ ትኩረት ለመስራት ተዘጋጅተናል” ብለዋል።

በተለይም በትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚታዩ መሰረታዊ የጥራት ችግሮችን ለይቶ “መፍትሔ መስጠትና የዜጎችን ህይወት ማሻሻል ተቀዳሚው ተግባራችን ይሆናል” ብለዋል ሚኒስትሩ።

በኢትዮጵያ የትምህርት መስክ “እውቀት መር ትውልድ ለመፍጠር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን” ብለዋል።

”የዚህን አገር ትምህርት በመሰረታዊነት መልኩ መቀየር የምንችልበትና ጥራቱን አሁን ካለበት በጣም በከፍተኛ ደረጃ የወደፊቱን ዕውቀት መር የሆነ ኢኮኖሚ ሊያግዝ የሚችል አዲስ ትውልድ በሰፊው መፍጠር አለብን” ሲሉም ገልጸዋል።

የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ቢኖሩም በአገርና በህዝብ ጉዳዮች ያለ ልዩነት መስራት ግዴታ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የተጋረጠባትን ፈተና እንድታልፍ ከፖለቲካ ልዩነት በላይ በአገር ጉዳይ አብሮ መቆም እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል።

የአገር ሉዓላዊነትና ቀጣይነት ጉዳይ ሚዛን የሚደፋ በመሆኑ “አገርን ከችግር ማሻገር የሁላችንም ሃላፊነት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

የተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት በተለያዩ ሃላፊነቶች መሾማቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ “በመተመማን ላይ የተመሰረተ ትብብር ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው” ብለዋል።

የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው በአገር ጉዳይ ግን በጋራ መቆምና ችግሮችንም በጋራ መፍታት የጋራ ሃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

ENA

Leave a Reply