በጸጥታው ም.ቤ ኢትዮጵያ በሚገባ ተከላከለች – መረጃ ይቅረብ ማራት እንጀምራለን – ጉተሬዝ

በጸጥታው መክር ቤት ስብሰባ ላይ አሜሪካን ተከትለው ተመሳሳይ ደብዳቤ ሲያነቡ የነበሩትን የተመለከቱ ” አሉላ ሰለሞን በጸጥታው ምክር ቤት ብዙ ሆኖ ሪፖርት አቀረበ” ሲሉ በአሜሪካና ተከታዮቿ ሚዛን አልባነት ተሳልቀዋል። ኢትዮጵያ ህግና ደንብን በመጥቀስ የቀረበባትን ክስ መከላከሏ ያስደሰታቸው አድናቆት አሰምተዋል። ” ማስረጃ ይቅረብልኝ፣ ያለምንም ማወላወል ማጣራት እንጀምራለን” ሲሉ አኦኒ ጉተሬዝ አመልክተዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት ትናንት ማምሻውን በኢትዮጵያ ጉዳይ ሲመክር ቪኦኤ በትግርኛ፣ ኦሮሚኛና በአማርኛ በየመካከሉ እየገባ የሚለውን ይል ነበር። ገና ከጅምሩ ስብሰባውን በቀጥታ እንደሚያስተላለፍ ማስታወቂያ በመደጋገም ቪኦኤ በሶስቱ ቋንቋ ማስታወቂያ ሲያሰራጭ ” ምን ሰምተው ነው” የሚል የማህበራዊ ጉምጉምታ ጎን ለጎን ይሰማ ነበር።

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ሲመክር በዚህ ሁለት ወር ብቻ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ይህ በገሃድ የታየው ብቻ ሲሆን በየኮሪዶሩና በዝግ የተደረጉትን ዱላታዎች አያካትትም።

አሜሪካ ከኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያ በላይ አዛኝ ሆና በቀርበችበት ፍጹም ሚዛን የሳተ አስተያየት የተባረሩት የተመ ሰራተኞች ወደ ስራቸው የማይመለሱ ከሆነ የጸጥታው ምክር ቤት እርምጃ እንዲወስድ አሳስባ ነበር። የአየር ላንድ ተወካይም አሉላ ሰለሞን የጻፈላቸው የሚመስለውን ሪፖርት እየተወራጩ አንብበዋል። በኢትዮጵያ ህዝብ ተቃራኒ የቆሙት በንባብ ያሰሙት ተመሳሳይ አቋምና ይዘት ያለው ደብዳቤ መሆኑንን የተሰሙ ” ከድግምግሞሽ ይልቅ ሰብሰብ አድርጎ እንዲያቀርብላቸው ስታሊንን ወይም አሉላ ሰለሞንን ቢጋብዙ የተሻለ መዝናኛ ይሆን ነበር” የሚል ሽሙጥ በማህበራዊ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ስብሰባው የተጠራው ኢትዮጵያ ሰባት የተመድ ሰራተኞችን ከሀገር በማስወጣቷና የሰሜን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ሁኔታ ላይ ለመወያየት ሲሆን፣ ስብሰባው እንዲካሄድ የጠየቁት፦ አሜሪካ ፣ ዩኬ (UK)፣ ኖርዌይ ፣ ኢስቶኒያ ፣ ፈረንሳይ እና አየርላንድ ነበሩ።

አንቶኒዮ ጉተሬዝ ምን አሉ?

ከኢትዮጵያ ጋር የተዋጣ ግንኙነት እንዲኖር ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አሁንም እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። እንደውም “ለኢትዮጵያ መንግስት ታደላለህ” በሚል ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲወቅሷቸው እንደነበር አመልክተዋል።

ለአምባሳደር ታዬ ባቀረቡት ጥያቄም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን ድረስ ለተመድ የገባ ደብዳቤ የለም፤ ከተባረሩት ሰባት የተመድ ሰራተኞች ዙሪያ የቀረበ ማስረጃ ደብዳቤ ስለመኖሩ የማውቀው ነገር የለም።

ገተሬዝ የተመድ ባለስጣናትና ሰራተኞቹን ኢትዮጵያ የማባረር መብት የላትም ያሉ ሲሆን ግለሰቦቹን በማባረር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግ ጥሳለች ብለዋል። አያይዘውም ማንኛውም የተመድ ሰራተኛ የፈጸመው ህግን ያልተከተለ ተግባር ካለ ልናውቅ እንፈልጋለን ሲሉም ማስረጃ እንዲቀርብላቸው አመልካተዋል። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የላከችው ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው አመልክተዋል።

አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ

ንግግሮች መደረግ ያለባቸው በኢትዮጵያ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መካከል እንዲሆን ጠይቀው ባፋጣኝ ማስረጃውን ለማቅረብ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። እንዲሁም “ሀሳብዎት እና ልቦናዎት” ከኛ ጋር በመሆኑ ከልብ እናመሰግናለን ሲሉ ክብረት ሰጥተዋቸዋል።

ኢትዮጵያ በተመድ ሰራተኞች ላይ ስለወሰደውች እርምጃ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ፣ በዓለም አቀፍ ህግ ሀገራት መብቶቻቸውን መጠቀም እንደሚችሉ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለውሳኔውም ምንም አይነት ማብራሪያ የማቅረብ ግዴታ እንደሌለበት አስታውቀዋል።

ሀገራት የተለያዩ የተመድ ሰራተኞችንና የሀገራት ዲፕሎማቶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሀገራቸው ማስወጣታቸውን አስታውሰው የተለያዩ አገራት ተመሳሳይ እርምጃ ሲወስዱ ተመድ ስብሰባ አድርጎ ስለማወቁ በለሰለሰ አንደበት ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃውን ስለ መውሰዱ ለማንኛውም አካል ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ እንደሌለበት ህግ ጠቅሰው ተናግረዋል። የተመድ ሰራተኞች የገለልተኝነት መርሆችን በጣሰ መልኩ ለህወሓት የሚወግኑ መሆናቸውን ሁሉንም ሳይሆን በጥቂቱ ዘርዝረው አመልክተዋል።

የተመድ ሰራተኞች ያልሞቱ ሰዎችን በረሃብ ሞተዋል በሚል የሀሰት መረጃዎችን ማሰራጨት፤ የመገናኛ መሣሪያዎችን ለህወሓት ወገን ማድረስ፤ መከላከያ ወጥቶ ህወሃት መቐለ ሲመለስ ከቡድኑ ጋር ደስታቸውን ሲገልጹና ዳንኪራ ሲያወርዱ እንደነበር ፤ ከሳዑዲ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ሶስተኛ ሀገር በማምጣት ለቡድኑ እንዲዋጉ ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ህወሓትን የሚደግፉ ጹሑፎችን ማዘገጀት ላይ ተጠምደው እንደነበር አስታውቀዋል።

ማን ይገባል፤ ማን ይወጣል ፣ ማን ይቆያል የሚለውን የሀገር መሰረታዊ ሉዓላዊ መብት መሆኑንን በማስታወስ ተመድ አዲስ ስነምግባር የተላበሱ ሰራተኞች እንዲመድብ ጠይቀዋል።

የተቀሩት ምን አሉ

ሁሉም ንግግር አግባብ እንደሆነ አመልክተዋል። ሰብአዊ እርዳታ ሊደርስ እንደሚገባ እንደሚያምኑ ጠቁመዋል። ሩሲያ በአማራና በአፋር የደረሰው ጉዳት በትግራይ ከደረሰው የሚያንስ እንዳልሆነ አመልክታለች። ሶስት አገራትን የወከሉት የቱኒዚያ ተወካይ በተመሳሳይ ስለ ንግግር ካነሱ በሁዋላ ልክ እንደ ቻይና፣ ህንድ፣ ሩሲያ ሁሉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያከበረ፣ አንድነቷንና መንግስቷን የተቀበለ አግባብ መከተለ ግድ እንደሆነ ገልጸዋል።

ስብሰባው በምን ተቋጨ

ኢትዮጵያ አሉኝ የምትለውን ማስረጃ ለጉተሬዝ እንድታቀርብ፣ ማስረጃ ካቀረበች ተመድ ምርመራ እንደሚጀምር ተገልጾ ያበቃ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በወኪሏ አማካይነት ማስረጃዋን ባስቸኳይ እንደምታቀርብ በማስታወቅ ስብሰባው መዶሻ ተመቶ አብቅቷል።

አሳሳቢ

በትግራይ፣ በአፋርና አማራ ክልል የምግብ እጥረት በየደረጃው፣ ረሃብና ድርቅ እየከፋ ሳይሄድ ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁም ሊያደርጉ እንደሚገባ የሁሉም እምነት ነው። ሕዝብ ከማንም የፖለቲካ ተቋምና ፖለቲከኞች በላይ በመሆኑ ይህ ሊተገበር እንደሚገባና ለተቸገሩ ሁሉ እርዳታ እንዲደርስ ንጹህ ህሊና ያላቸው ሁሉ ጫና ሊያደርጉ ይገባል። ትህነግም የያዛቸውን ተሽከርካሪዎች በመልቀቅ ድጋፍ ማድረግ ይገባዋል። ደጋፊዎቹም ይህን መግፋት አለባቸው።

Leave a Reply