ትግራይና አሁን ትህነግ በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ሕዝብ መረጃ አልባ ሆኗል። ትህነግ የሚያሰራጨውን መረጃ እንኳን መስማት የማይቻልበት ደረጃ ነው ያለው። ኤሌክትሪክ የለም ቲቪና በኤለኤክትሪክ የሚሰሩ የመረጃ መቋደሻዎችን መጠቀም አይቻልም። ባትሪ እንዳይጠቀሙ ገበያው ላይ የለም። የነበረውም አልቋል። በዚህም የተነሳ ሰላማዊ ዜጎች ከመረጃና ከግንኙነት ውጭ ሆነዋል። ውስኖች በጄኔሬተር ቢጠቀሙም ከቁጥር የሚገቡ አይደሉም። ዝርዝሩ አሳዛኝም አሳሳቢም ነው። “እስከመቼ”ሲል የሚጠየቀው አስተየት ሰጪ “ስንት ዓመት በዚህ መንገድ ይቀጥላል? ይላል።

በአውሮፓ የሚኖሩ ሶስት የትግራይ ተወላጆች ለጊዜው ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠየቀው እንዳሉት ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሕዝብ ተቆልፎበታል። ለምሳሌ እነሱ በትግራይ ምን እየሆነ እንዳለ መረጃ የላቸውም። ቤተሰቦቻቸውን በስልክ ካገኙ ወራቶች ተቆጥረዋል። ትህነግም ቢሆን ጥርት ያለ መረጃ አያቀርብም። እናም ግራ ተጋብተዋል።

በድፍን ትግራይና ትህነግ በሃይል “ወሮ” ይዟቸዋል በሚባልባቸው አካባቢዎች የስልክና ኢንተርኔት እንዳይቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ማን ነው? የሚለው ጥያቄ አሁን ላይ ጎልቶ እየወጣ ያለው ለዚህ ይመስላል። በትግራይም ሆነ በወረራ በተያዙት አካባቢዎች፣ ባለው ቀውስና የድርቅ ሁኔታ የተነሳ ጉዳዩ ከድርጅት ድጋፍና ፍቅር በላይ ግለሰበዊ ወይም ቤተሰባዊ እየሆነም ነው።ስልክና ኢንተርኔት ቢከፈት ወይም ቢጀመር ትግራይ ያሉ ወገኖች በየትኛውም ስፍራ ካሉ ወገኖቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ባልደረቦቻቸው ወይም ከፈለጉት ጋር ግንኙነት ይጀምራሉ ማለት ነው። ስጋታቸውን እየጨመረ መሆኑንን ያስረዱት የትግራይ ተወላጆች አገልግሎቶቹ ቢጀመሩ ዘመዶቻቸውን ያገኛሉ። እነሱ የሚያናግራቸው ሰዎች እውነቱን ያስረዱዋቸዋል። ስለ አሉበት ወቅታዊ ቁመና በወጉ ለመረዳት ይቀላል።

“መረጃ ከምንም በላይ ቁልፍ ጉዳይ ነው” የሚሉት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ኢንተርኔትና ስልክ እንዳይቀጠል አብዝቶ የሚፈልገው ማን እንደሆን አይገባቸውም። ግን መንግስት ኢንተርኔትና ስልክ አገልግሎት ላይ ቢያውል የሚጎዳው አንዳችም ነገር አለ ብለው አያስቡም። ይልቁኑም ትህነግ ሊጎዳይ ይችላል የሚል ዕምነት ነው ያላቸው። ምንም ሆን ምን አሁን ላይ ጉዳዩ የድርጅት ድጋፍና ተቃውሞ ሳይሆን ቤተሰባዊና ግለሰባዊ ይዘት እየይዘ መምጣቱን ያስረዳሉ።

“ቤተሰብ በምን ሆኔታ ላይ እንደሆነ አናውቅም፣ ምን ይብሉ፣ ይጠጡ፣ ይልበሱ…” እንደማያውቁ፣ ረሃብ አስከፊ እየሆነ መምጣቱን ከሚዲያዎችና አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚሰሙ በመጠቀስ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ በርካቶች በስጋት እየተሰቃዩ መሆናቸውን አመልከተዋል። አንድ መፍትሄ እንዲበጅ ሰላም ወዳዶች ሁሉ ጉዳዩን ከስሜታዊነት በመራቅ ሊመለከቱት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በወልደያ፣ በላሊበላና ቆቦ ትህነግ በሚቆጣጠራቸው የአማራ ክልል ግዛቶች አገልግሎቱ ቢጀመር ሕዝቡ በተመሳሳይ ግንኙነቱን ከተጠቀሱት ከተሞች ውጪ በመላው አገሪቱን በውጭ አገር ካሉ ጋር ሁሉ ያደረጋል። በሁለቱም ደረጃዎች ሕዝብ የድምጽ ብቻ ሳይሆን የመስል መረጃም ያስተላልፋል።ያሰራጫ። በማህበራዊ ሚዲያዎች ይተነፍሳል።

ትህነግ ከዕርዳታ ሰራተኞች ባገኘውና አስቀድሞ ባዘጋጀው የዓለም ዓቀፍ መገናኛ የሳተላይት አውታሮች አማካይነት ለሚፈልገው ዓላማ “ይጠቅመኛል” ያለውን መረጃ ከማስተላለፍ ያገደው ነገር የለም። በትግራይና በተጠቀሱት የአማራ ክልል አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመኖሩ ሰዎች በባትሪ ድንጋይ የሚሰሩ ሬዲዮኖችን ከፍቶ እንኳን መረጃ መስማት አልቻለም። እናም ህዝቡ ከተለመዱት የጀርመንና የአሜሪካ ሬዲዮም ተለይቷል።

የላሊበላ አካባቢ ተወላጅ እንደሆነ ያስታወቀውና አሜሪካን አገር በታክሲ ስራ የሚተዳደረው ሰብስቤ እንደሚለው የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት እዲከፈት ቢወሰን እንኳ ትህነግ እሺ ያላል ብሎ እንደማያምን ይናገራል። ሸሽተው ከከተማ ከወጡ ወገኖች መስማቱን አስታውቆ እንዳለው ላሊበላ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል። ዝርፊያ ተፈጽሟል። በርካታ የሰብአዊ ቀውስ ደርሷል። በፊልም ቀርጸው ያስቀመጡ፣ የሰነዱ አሉ።ስለዚህ አገልግሎቱ አሁን ቢከፈት የተፈጸመው ሁሉ ይፋ ስለሚሆን ትህነግ ይፈቅዳል ብሎ አያስብም።

ቤተሰቦቹን ከገኘ ወራት ያስቆጠረው አስተያየት ሰጪ፣ እሱ ገንዘብ እየላከ የሚረዳቸው ቤተሰቦች በምን ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ አለመቻሉ ጭንቀት ውስጥ ከቶታል። አንድ መፍትሄ ሊፈለግ እንደሚገባ ያምናል።

ትህነግ መከላከያ ላይ ጥቃት ሲፈጽም አስቀድሞ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎትን አቋርጦ ነበር። የመንግስት ሃይል ትህነግን አሸንፎ ወደ መቀለ ሲመለስ ወዲያውኑ የተቋረጠውን አገልግሎት የጀመረ ቢሆንም ትህነግ እንደገና ወደ መቀለ ሲመለስ ይሰሩ የነበሩ አገልግሎቶችን ዳግም እንዳቆማቸው ይታወሳል።

ዛሬ በትግራይም ሆን በሃይል በተያዙ የአማራ ክልል ይዞታዎች ሕዝብ መረጃ አልባ ሆኖ፣ የሚተነፍስበት መንገድ ጠፍቶት በሃያ አንደኛው ዘመን መገባደጃ ላይ በጨለማ እየኖረ ነው። ይህ አሳሳቢ ጉዳይ መልክ እንዲይዝ የሚናገሩ፣ ጉዳዩ ከግለሰብና ድርጅት ፍቅር በላይ በመሆኑ ሁሉም ወገን በያለበት ጫና ሊፈጥር ይገባል።

“ሕዝብ ለስልጣን ጥመኞች ሲባል መረጃ አልባ፣ መተነፈስ የማይችል ሆኖ መኖር የለበትም” የሚለው የሁለቱም ወገኖች አስተያየት ነው። መንግስት ኢነተርኔት ቢከፍት፣ ስልክ ቢያስጀምር ትህነግ እንደሚጎዳና በስፋት እንደሚጋለጥ የሚያምኑ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ሊገፋበት እንደሚገባ አመላክተዋል።

Leave a Reply