በኦሮሚያ አርሶ አደሮች “የኢትዮጵያ አቡካዶ” ወደ ውጭ መላክ ጀመሩ

በኦሮሚያ ክልል አርሶ አደሮች የኢትዮጵያን ስም የያዘ “የኢትዮጵያ የአቮካዶ” ምርት የክልሉ ፕሬዝዳንትና የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በተገኙበት ከቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ወደ ስፔን ሃገር መላክ ጀመሩ። አርሶ አደሮች ተገቢዉን ድጋፍና ዕገዛ ካገኙ በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ የግብርና ምርቶችን ማምረት እንደሚችሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በውቀቱ ተናግረዋል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የአቮካዶ ምርቶቹን አምርተዉ ወደ ስፔን ሃገር ለላኩት አርሶ አደሮችና ለሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የዕዉቅና ምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።

Advertisements

በማህበር ተደራጅተዉ አቮካዶ በማምረት ላይ ከሚገኙ 54 አርሶ አደሮች መካከል 160 ኩንታል የአቮካዶ ምርት ወደ ስፔን የላኩትን ስምንት አርሶ አደሮችና ሌሎችን ጨምሮ በዚህ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላትና ድጋፍ ላደረጉ ባለሃብቶች ምስጋና አቅርበዋል።

አርሶ አደሮች ተገቢዉን ድጋፍና ዕገዛ ካገኙ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የግብርና ምርት ማምረት ይችላሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በተመሣሣይ ስራ ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች በቀጣይነት ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

አቮካዶን በብዛትና በጥራት ማምረት ከቻልን የአርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ: የዉጪ ምንዛሬን ማምጣትና የስራ ዕድልን መፍጠር እንችላለን ያሉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በግብርናዉ ዘርፍ ዉስጥ ያሉ ማነቆዎችን በዕቅድና በስትራቴጂ እንቀርፋለን ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸዉ ክልሉ የጀመረዉ ስራ የሚበረታታ ነዉ ብለዋል። የተገኘዉን መልካም ልምድ በሌሎች ክልሎች እንዲስፋፋ እንሰራለን ለዘርፉም ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የመንግስት ሃብት አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪዉ ዶ/ር ግርማ አመንቴ ባለፉት ሶስት አመታት ከ6600 ሄክታር የሚበልጥ መሬት በተመረጡ የአቮካዶ ዝርያዎች መልማቱን ተናግረዋል።

ለዉጪ ሃገር ገበያ የሚቀርቡ የአቮካዶ ምርቶችን በብዛትና በጥራት የማምረት: የማሰባሰብና ወደ ዉጪ የመላክ ስራዉም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ዋና ዳይሬክተሩ አበበ ዲሪባ ከዘርፉ ያገኘናቸዉን ልምዶች በማጠናቀር የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቀጣይነት እንሰራለን ብለዋል። አንዳንድ ባለሃብቶችም በዘርፉ ያለንን ልምድ ለአርሶ አደሮች ለማካፈል ዝግጁ ነን ብለዋል።

ወንድማገኝ አሰፋ ኦቢኤን

Leave a Reply