ከጊዜ ጋር ትንቅንቅ የገባው – መልሶ ማጥቃት

ጦርነቱን ዝናቡ ሲያቆምና መሬቱ ሲጠግ የማስጀመርና በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ ዕቅድ እንዳለ በገሃድም በጎንዮሽም ሲነገር ሰንብቷል። በትህነግ በኩል ደግሞ ክረምት ሳይጫን በአማራ ክልልና አፋር ሰፊ ቦታዎችን በመያዝ የመደራደሪያ አቅም ለማሳደግ ዕቅድ እንደነበር በተመሳሳይ ሲሰማ ነበር።

እንድተሰማው ትህነግ አማራ ክልልን አጥለቅልቆ ባህር ዳርና ጎንደርን በመቁረጥ ወደ አዲስ አበባ ለማምራት ቀን እየቆረጠ ነበር። አማራ ክልልና መከላከያ ባስቸኳይ መልሶ ማደረጃት በማካሄድ ወረራ የተባለውን የትህነግ አካሄድ ለመመከት ሲረባረቡ የአውሮፓ ሚዲያዎች የትህነግን ፈጣን ሩጫ ከታሊባን በፍጥነት መላ አፍጋንን መቆጣጠር ጋር በማያያዝ ለመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እስር ቤትና የፍርድ ሂደት ግምት ሲያመላክቱ ነበር።

በመካከሉ እየገቡ “ በባህር ዳር፣ በጎብደር፣ በደብረብርሃን በይፋት …” እያሉ የአዲስ አበባ ጉዞ ካርታ ሲያመላክቱ የነበሩት አቶ ጌታቸው “ የአብይ ሰራዊት” የሚሉትን የኢትዮጵያ መከላከያ “የነተበ፣ የፈረሰ፣ አቅም አልባ፣ ዋጋ ቢስ…” እያሉ ጉዟቸውን የሚገታ ምድራዊ ሃይል እንደማይኖር ሲያስታውቁም ነበር።

ዶክተር ደብረ ጽዮንም የጅቡቲን መንገድ በመቁረጥ ዕርዳታ ወደ ትግራይ ማስገባት እንደሚጀመሩ ለእነ ማርቲን ፕላውት በገለጹት መሰረት “ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ መንግስት ነገሮች እየጨለሙ፣ ጸሃይ እየጠለቀች ነው” ሲባል ነበር።

በቅርቡ ይፋ የሆነው ድብቁ የትህነግ ሰነድ እንደሚያስረዳው ድርጅቱ አስቀድሞ ለጦርነት ሲዘጋጅ እንደነበርና ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰራዊት መገንባቱ ሲሰማ “ አምላክ ነው በተአምራቱ ያተረፈን” ያሉ መንግስት ላለፉት ሶስትና አራት ወራት በስፋት፣ ለአለፉት አንድ በስትራቴጂክ መስኩ መከላከያውን ሲያዘምንና በሰው ሃይል ሲያጠናክር መቆየቱ አግባብ እንደሆነ አምነዋል።

የአማራ ክልል መሪ የነበሩት አቶ አገኘሁ “ በሰው ማዕበል ወረውናል፣ እኛም በተመሳሳይ መንገድ ጦርነቱን እናስኬደዋለን” በሚል ክተት ከጠሩ በሁዋላ የትህነግ ሩጫ ቢቆምም፣ በሁሉም ክልል የሚገኙ የልዩ ሃይል አባላት ወደ ግንባር በመሄድ ድጋፍ ቢሰጡም፣ የመከላከያ አባል በመሆን በደስታ አገራቸውን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ወጣቶችን በማሰለጠን የሰው ሃይሉን ከትህነግ ጋር በአጭር ጊዜ ማመጣተን እንደቻለ መረጃዎች ይመስክራሉ።

Advertisements

አብዛኛ ቦታዎች ወደነበሩበት ሁኔታ የተመለሱ ሲሆን የወሎ ግንባርን ጨምሮ በሰሜን አቅጣጫ የቀሩ ቦታዎችን ለማስመለስ መንግስት መላ ሃይሉን አስተባብሮ ጥቃት መጀመሩ ባለፉት ሶስት ቀናት ይፋ ሆኗል። የአውሮፓ ፓርላማ እስከወሩ መጨረሻ መሻሻል ካልታየ ማዕቀብ እንደሚጥል ይፋ ባደረገ ማግስት እንደተጀመረ የተነገረለት የአየር ጥቃት በስፋት ድሮኖች የተሳተፉበትና ለጊዜው በውል ያልተገለጸ ጉዳት ያስከተለ መሆኑንን አቶ ጌታቸውን ጠቅሶ ኤፒ ዘግቧል።

የአውሮፓ ፓርላማ አሜሪካን ተከትሎ ባደረገው ስብሰባ ሃያ ዘጠኝ ነጥቦችን በማስቀመጥ እስከ ወሩ መጨረሻ ጊዜ በመስጠት ሁለቱም ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ አሳስቧል። ይህ ካልሆነ ማዕቀብ እንደሚጥል ገልጿል።

ትህነግ ከአማራና ከአፋር ክልል በአስቸኳይ እንዲወጣ፤ የአማራ ክልል መንግስትም ትህነግ ህጋዊ ድንበሬ ነው ከሚለው የምዕራብ ትግራይ ( ወልቃይት ጠገዴ) ጦሩን እንዲያስወጣ አጽንዖት ሰጥቶ አስታውቋል። ፓርላማው ይህን ሲል ትህነግ ሙሉ በሙሉ ከአፋር በሃይል እንዲወጣ ተደርጓል። አቶ ጌታቸውም “ለአፋር ሕዝብ ካለን ፍቅር በመነሳት ጦር ማንቀሳቀስ ስላለብን አፋርን ለቀናል” ማለታቸው በነጮቹ ሚዲያ መሳፉን የአውሮፓ ፓርላማ ይስማ አይስማ አልታወቀም።

የወቅልቃይት ጉዳይ የቆየና ብዙ ዋጋ ያስከፍለ ስለመሆኑ የዘነጋው የአውሮፓ ፓርላማ፣ የአማራ ክልል ሃይል ከወልቃይትና ጠገዴ እንዲወጣ ላቀረበው ጥያቄ በይፋ መልስ ባይሰጥም “ በሃይል የተያዙትና ዚጎች እየተሰቃዩ ያሉባቸው ቦታዎች እስኪለቀቁ በየትናውም ሰዓትና ጊዘ በሁሉም ግንባር ማጥቃት ይጀመራል” ሲል ክልሉ ይህ በተባለ ቀናት ውስጥ አቋሙን ይፋ አድርጓል።


READ MORE STORIES


ለኢትዮጵያ የጦር መሳርያ ሽያጭ እንዳያካሂዱም በመጠየቅ እስከወሩ መጨረሻ ፤ ማለትም በመጭዎቹ ሦስት ሳምንታት ሁኔታዎች ካልተሻሻሉ ኅብረቱ በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት አመራሮች ላይ የማዕቀብ ርምጃ መዉሰድ እንዳለበት ያሳሰበው የአውሮፓ ህብረት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚታየዉ ጦርነት እንዲቆም ፤ ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እና ዉይይት እንዲመጡ፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቆሙ፤ የሰብዓዊ ርዳታን በሁሉም ቦታዎች ማድረስ እንዲቻል እንዲደረግ፤ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፤ የሚጠይቁ 29 ነጥቦችን ያካተተ ዉሳኔን የአውሮፓ ፓርላማ አሳልፏል። ተግባራዊ እንዲሆንም ለህብረቱና አስፈልጊ ላላቸው ሁሉ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው ጥቃቱ ከሰማይ እንዲሁም ከምደር በከባድ መሳሪያ የተጀመረው። በይፋ አንድ ሁለት ብሎ መናገር ባይቻልም የመንግስት ወገን የሆነው ሃይል ክፉኛ ጉዳት ማድረሱ ተሰምቷል። ለትህነግ ሰዎች ቅርብ የሆኑ ሚዲያዎችና በእርዳታ ስራ የተሰማሩም ይህንኑ እየገለጹ ነው። ከመንግስት ወገን በይፋ ምን እየሆነ እንደሆነ የተነፈሰ አካል የለም።

መንግስት “ እጅ በአፍ የሚያጭን” ያለውን ጥቃት “ ቃል በገባነው መሰረት እናበስራለን” ሲል በአዲስ አመት ዋዜማ በድጋሚ ማስታወቁ አይዘነጋም። ባልፈው ሳምንት አዲስ መንግስት ምስረታ ላይም ፕሬዚዳንቷ ዓመቱ ለሰላምና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑንን አመልክተው ነበር። ሕዝብም በገሃድ “ የትህነግ ጉዳይ እንዲያበቃ” መንግስትን በተለያዩ አግባቦች ጠይቋል።

አዲስ መንግስት በተመሰረተ ማግስት ጥቃት የጀመረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወደ መቀለ የመግባት ዕቅድ ይኑረው አይኑረው ባይታወቅም የአየር ድብደባው ሲቆም እግረኛውን እንደሚያንቀሳቅስ እየተሰማ ነው። በተለያዩ ግንባሮች የተሰለፉት ሃይሎች ሙሉ ዝግጅት ጨርሰው በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን የአገር መከላከያ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

የትህነግ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው በጽሁፍ መልዕክት ጥቃቱ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል። ጥቃቱ መድረሱን ሲያስታውቁ እንዳሉት ስለደረሰው ጉዳት ለጊዜው መረጃ የላቸውም። ስም ጠቅሰው እንደገለጹት ከሆነ ጥቃቱ መቀለ ዙሪያ በተመረጡ ቦታዎች ተካሂዷል ተብሎ የሚሰራጨውን ዘገባ በተዘዋዋሪ አስተባብለዋል።

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በቪ8 ተጭነው በአጀብ ሲሄዱ በነበሩ የሰራዊት አመራሮች ላይ ከአየር ላይ ጥቃት መፈጸሙን የመከላከያ ምንጮች እያስታወቁ ነው። ከደጁ ምንም መረጃ የማይወጣው የጀነራል መርዳሳ አየር ሃይል ስለ ሁኔታው ያለው ነገር የለም።

አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መንገዶች ጫናቸው እየበረታ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ የኢትዪጵያ መንግስት “የተደራደር” ጫናውን ወደ ጎን በመተው በጥድፊያ ጥቃት የሰነዘረው የትህነግን የመደራደሪያ አቅም ለማራከስና “ አውራዎቹ ሁሌም ከአሸናፊዎች ግራ ይሆናሉ” የሚባለውን አባባል ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ።

ትህነግም ቢሆን ይህን በወጉ ስለሚረዳ አሁን የተከፈተበትን ጥቃት ለመመከት የሞት ሽረት ትግል እንደሚያደርግ አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል። ለትህነግ አሁን ላይ ያለው ምርጫ ተናንቆ ወደ ድርድር መሄድ በመሆኑ ግጥሚያው ቀላል እንደማይሆን ታዛቢዎች ይናገራሉ። ትህነግ የመከላከል አቅሙ ጠንካራ ሆኖ ጦርነቱ ከተካረረ ሰብአዊ ቀውሱ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው የሚገልጹም ጥቂት አይደሉም።

ጦርነቱ ከውዲህም ሆነ ከወዲያ እልህ፣ ቂምና ጥላቻ የተሞላ መሆኑ የሚወስደውን እርምጃ እንዳከረው የሚሰጉ መንግስት፣ የአማራ ክልልና በዙሪያው ያሉ ከወዲሁ ሕዝብን ከፖለቲካው ጥቂት አመራሮች እንዲለዩና እንዲመለቱ በስፋት መሰራት እንደሚኖርበት ይመክራሉ።

ከዚህም በላይ ሁኔታውን በማየት፣ የሚመጣውን በመገመት፣ አስቀድሞ መከራን የሚቀንስ፣ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ውሳኔ በቡድን ደረጃ እንኳን ባይቻል፣ በግል መወሰን አግባብ እንደሚሆን የሚጠይቁም አሉ። ከጊዜ ጋር ትንቅንቅ የገባው ዘመቻ መልከ ዥጉርጉር ጣጣዎች አሉበት!!

Leave a Reply