መከላከያ በአየር ጥቃት እየሰነዘረ ነው፤ አቶ ጌታቸው “እናሸንፋለን”

አቶ ጌታቸው የመከላከል ሃይላችንን በማደራጀት ጥቃቱን እንደምናሸንፍ ወይም እንደምንመክት አልጠራጠርም ብለዋል። እንደሚባለው ከሆነ መንግስት ወደ ሙሉ ማጥቃት ገና አልገባም። ግን በአየር ጥቃት የትህነግን ሃይል እያዳከመና ለእግረኛው ሃይል መንገድ እየጠረገ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሁሉንም ሃይሉን አስተባብሮ ሙሉ ማጥቃት መጀመሩን የሚያመላክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው። መረጃዎቹ የኢትዮጵያ አየር ሃይል በተመረጡ ቦታዎች ጥቃት ማካሄዱንና ጥቃቶ ከወትሮው የከረረ ስለመሆኑ እየዘገቡ ነው። አቶ ጌታቸው ረዳም ይህንኑ አረጋግተዋል። በተለይ ለኤፒ በዝርዝር በጽሁፍ መልዕክት አስረድተዋል።

ከኢትዮጵያ ወገን በይፋ መግለጫ ማግኘት እንዳልቻሉ የጠቆሙት አልጀዚራ፣ ብሎምበርግ፣ ኤፒና ሌሎች መገናኛዎች ባወጡት መረጃ ” እንደሚባለው ” የሚል ሃረግ በማከል የክረምቱ ወር በማለቁ የመከላከያ ሃይል እንዳሻው ለመንቀሳቀስና ለመደረጃት በጋው ጥሩ አጋጣሚ ስለሆነለት ክረምቱ እስኪወጣ ሲጠባበቁ እንደነበር ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በቲውተር አድራሻቸው “In order to liberate our people who are suffering due to the terrorist TPLF, there might be irreversible operations in all fronts, at any time or hour.” በትህነግ በተያዙት የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚሰቃዩትን ወገኖች ነጻ ለማውጣት ሊቀለበስ የማይችል ጥቃት በሁሉም ግንባር በየትኛውም ሰዓትና ጊዜ ሊከፈት እንደሚችል ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቃቸውን ሚዲያዎቹ አመላክተዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት በአየር ሃይል የሚመራ የተደራጀ ጥቃት ማካሄድ የተጀመረው የአዲስ መንግስት ምስረታው በተጠናቀቅ ማግስት መሆኑንን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አስታውቀው ይህም የሆነው አዲሱ መንግስት ” የአገር ሉዓላዊነት ማስከበርና የዜጎችን ሰላም ማረጋገጥ ቅድሚያ ተግባሬ ነው” በማለት ይፋ ባደረገው መሰረት እንደሚሆን ግምታቸውን አኑረዋል።

የትህነግ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸውን ጠቅሰው ሚዲያዎቹ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ቀናት የአየር ድብደባ በሰሜናዊው የአማራ ክልል ክፍሎች ( በትህነግ በተያዙት አካባቢዎች ለማለት ነው) እና ከትግራይ ጋር ድንበር በሆኑ አካባቢዎች ጥቃት መፈጸሙን አመልክተዋል። የጉዳቱን መጠን እንዳልታወቀ ” The number of casualties, if any, was unclear” ሲሉ ነው ያስታወቁት።

አቶ ጌታቸው ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የአየር ድብደባው በሦስት አከባቢዎች ማለትም በውርጌሳ ፣ በወገል ጠና እና የአፋር ክልልን ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ነው።በውርጌሳ አካባቢ የአየር ድብደባ መፈጸሙን የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለሮይተርስ ማረጋገጣቸው ተዘግቧል። የትኞቹና የት ያሉት የዲፕሎማት ምንጮች እንደሆኑ ግን የተባለ ነገር የለም።

“የመከላከያ አቋማችንን እናጠናክራለን። በሁሉም አቅጣጫዎች የሚደረገውን ጥቃት እንደምናከሽፍ እርግጠኞች ነን። ከበባው እስኪያቆም ጸንተን እንቆማለን” ሲሉ አቶ ጌታቸው

ከገለልተኛ አካላት በይፋ ባይገልጽም በአየር ጥቃት በተሽከርካሪ እየተጓዙ ባሉ ወታደራዊ አመራሮች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተሰምቷል። ጥቃቱ የተፈጸመው በመኪናቸው ታጅበው እየሄዱ ባለበት ወቅት ነው።

የአገር መከላከያ ሰራዊት በእግረኛ ጥቃት እንደሚጀምርና የተያዙትን ስፍራዎች ለማስለቀቅ ሙሉ ኦፕሬሽን እንደሚከፍት ተሰምቷል። በአፋር በኩል ወደ ውቅሮ የተጠጋው ሰራዊት በየትኛውም ሰዓት ወደ መቀለ ሊያመራ እንደሚችል እየተጠቆመ ነው።

የጦርነቱ ዜና ያሳሰባቸው የሰላም ንግግር ቢደረግ እንደሚሻል፣ ለተወሰኑ ሰዎች ሲባል ህዝብ የሚጎዳበትና የሚሰቃይበት አግባብ ሊቆም እንደሚገባ እየገለጹ ነው። የትግራይ ልሂቃን ይህንን ጉዳይ ሊገፉበት እንደሚገባ የሚመክሩም አሉ።

በተመሳሳይ ዜና በኢትዮጵያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ቲቦር ናጂ ለትግራይ ልሂቃን የሚከተለውን ጥያቄ አንስተዋል። ” ይሄንን ጦርነትና ይዞት የመጣውን መከራ ከማቆም ባለፈ ምንድን እንደምትፈልጉ የትግራይ ተወላጆችን ልጠይቅ እፈልጋለሁ” ካሉ በሁዋላ “ነጻ ሀገር መመስረት ነው የምትፈልጉት ? ህወሃት ትግራይን እንዲያስተዳድር ነው የምትፈልጉት ? ወይንስ የትግራይ መሬት የምትሉትን ማስመለስ ? አልያስ የትግራይ የበላይነት ማምጣት ?

አምባሳደሩ ይህን ጥያቄ ከጠየቁ በሁዋላ በግልጽ ቋንቋ “በአሜሪካ መንግስት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳገለግል እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክረናል። መልስ ልናገኝላቸው ግን አልተቻለንም። ” ሲሉ በጥያቄ ጀምረው በአስተያየት ጠቅልለዋል።

You may also like...

Leave a Reply