• ቱርክ በዓለም አቀፍ ውጊያዎች ስኬታማ ሆነዋል የተባሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖቿን ሽያጭ ወደ ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ ማስፋፋቷን አራት የመረጃ ምንጮች ለሬውተርስ ተናገሩ። አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የቱርክ ባለሥልጣን ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ የመለዋወጫ አቅርቦት እና ሥልጠናን ባካተተ ሥምምነት ባይራክታር ቲቢ2 (Bayraktar TB2) የተባሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለመግዛት መጠየቃቸውን እንደተናገሩ ሬውተርስ ዘግቧል።

• ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ (African Growth and Opportunity Act) በኩል ያላት ተጠቃሚነት ላይ አሜሪካ በቅርቡ ከውሳኔ እንደምትደርስ የአገሪቱ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይ ተናገሩ። ኃላፊዋ “በይፋዊ መንገድ እና በግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በኩል የሚደርሱን መረጃዎች አበረታች አይደሉም። በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ነው” ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም መንግሥታቸው በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ በአፋጣኝ መፍትሔ ለማበጀት ቁርጠኛ መሆኑን ለሬውተርስ ገልጸዋል። ቢልለኔ “ሰብዓዊ ቀውስ አጎዋ ዕድል ከፈጠረላቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶች የሥራ ዕድል በመንጠቅ አይገታም። እንዲያውም ያባብሰዋል” ብለዋል።

• በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ አፈና እና እንግልት መባባሱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አስታወቀ። ጉባኤው በሁለቱ ክልሎች ባለፈው መስከረም በታጣቂዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች እና እገታዎችን ዘርዘር አድርጎ ባቀረበበት መግለጫ “የጸጥታ ሥጋት ባለባቸው ቦታዎች በአፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ ካልተወሰደ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ከዚህ በከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚደርስ” አስጠንቅቋል።

• በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ ስድስት ሰዎች ተገደሉ። የአገሪቱ ጦር በቤይሩት ጎዳናዎች የበረታውን ግጭት ለመቆጣጠር ታንክ እና ወታደሮች እስከ ማሰማራት ደርሷል። ቤይሩት የጠመንጃ ተኩስ፣ የቦምብ ፍንዳታ እና የአምቡላንሶች ጩኸት ሲሰማባት ውላለች።

• በየመን ከማሪድ ከተማ በስተደቡብ ለአራተኛ ቀን በተደረገ የአየር ድብደባ ከ150 በላይ የሑቲ አማጽያን መገደላቸውን ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጥምረት አስታወቀ። ጥምረቱ ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ አስራ አንድ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን እና “አሸባሪ” ያላቸው 150 የሑቲ ታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውቋል።ዜናውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

ዜናዎቹ የጀርመን ድምጽ ናቸው ሙሉውን እዚህ ላይ ይጫኑ ፦https://p.dw.com/p/41hEt?maca=amh-Facebook-dw

Leave a Reply