መከላከያ ከመከላከል አልፎ እየደመሰሰ መሆኑን አስታወቀ!!

“…ጦርነቱን እናሳጥረዋለን ፤ በሁለት ሳምንት አዲስ አበባ እንገባለን ፤ ፖለቲካዊ ፣ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታን እንቀይራለን …” በሚል ስሌት የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ሰራዊት በሁሉም ግንባር የከፍተውን ጦርነት በመመከት ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑንን የአገር መከላከያ ሰራዊት አስታውቋል።

ቀደም ሲል አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ሲቀጥልም የቀድሞው ሌተናል ጀነራል ጻድቃን የኢትዮጵያ መንግስት በድሮን፣ በተዋጊ አውሮፕላኖችና በከባድ መሳሪያ ሲደበድባቸው ቆይቶ እግረኛ ጦሩን ባለፈው ሰኞ ማነቀሳቀሱን ለውጭ አገር ሚዲያዎች አስታወቀዋል።

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ማጥቃት እንዳልጀመረ ጠቅሶ፣ ሲታዘዝ ግን ማንኛውንም ጥቃት ለመፈጸም በሙሉ ዝግጅት ላይ መሆኑንን አመልክቶ፣ ጥቃት ተፈጸመብኝ ሲል ትህነግ ያሰራጨውን መግለጫ “የተለመደ ቅጥፈት” ሲል በማጣጣል አጭር መልዕክት በሚታወቀው የማህበራዊ አምዱ በኩል አሰራጭቶ ነበር። በዚሁ አጭር መግለጫው ጥቃት ከጀመረ ” ድረሱልኝ” ለማለት እንኳን ጊዜ እንደማይሰጥ ማስታወሱም አይዘነጋም።

“ጥቃት ከፈተብን” የሚለው መረጃ ይፋ ከሆነበት ካለፈው ዓርብ ጀምሮ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ቢሆንም፣ ጻድቃን ” ጦርነቱ የሚራዘም አይመስለኝም። በቀናት፣ ቢበዛ በሳምንታት ይጠናቀቃል” ሲሉ ለኒውዮርክ ታይም መናገራቸው ” ነገሩ እንዴት ነው” የሚል ጥያቄ በሁሉም ወገን አስነስቷል።

ዘገባው ዝርዝር ጉዳዩን በትኖ በመጠየቅ የጦርነቱ ፈጥኖ መጠናቀቅ እንዴትና በማን አሸናፊነት እንደሆነ ፍንጭ አልሰጠም። ይሁን እንጂ በዚሁ ሪፖርት ላይ ” የአየር ጥቃቱን ለመሸሽ ከባድ መሳሪያና ሰራዊታችንን ወደ ሩቅ ገጠራማ አካባቢዎች አሽሽተናል ወይም አፈግፍገናል” ሲሉ ጻድቃን መናገራቸው ተጠቁሟል። ይህን ያነበቡ ” ጦርነቱን በቀናት አለያም በሳምንታት ይጠናቀቃል” ለሚለው ግምት ” በማን አሸናፊነት” የሚለው ጥያቄ ብዙም አነጋጋሪ አይሆንባቸውም። ይሁን እንጂ በጫናና በማስፈራሪያ የተወጠረችው ኢትዮጵያ ጻድቃን እንዳሉት ምን አይነት ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ወጥመድ እንደተበጀላት መገመት የቻሉ የሉም።

Advertisements

ጦርነቱ ወደ ሰሜን ካመዘነ የትግራይ ሃይሎች መጠቃታቸውን አመላካች ሲሆን ጦርነቱ ወደ ደቡብና ምዕራብ ካመዘነ የትግራይ ሃይሎች እያተቁ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑንን ያመለከቱ እንዳሉት አሁን ላይ በኦፊሳል ባይገለጽም የጦርነቱ አፍ ወደ ሰሜን እየዞረ መሆኑንን አመላካች መረጃዎች እየተሰማ መሆኑንን ይናገራሉ። አቶ ጌታቸውም ሆኑ ጀነራል ጻድቃን በሰጡት መግለጫ ፍንጭ ሰጥተዋል። በተለይ ጻድቃን ” እያፈገፈግን ነው” ማለታቸው በትህነግ ደጋፊዎች ዘንድ ሳይቀር አነጋጋሪ ሆኗል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ መግለጫ የሰጠው የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ” የመከላከያ ሠራዊታችን የጁንታውን ጥቃት የመመከት ውጊያ እያካሄደ የጠላትን ወራሪ ሀይል መመከት ብቻ ሳይሆን እየደመሰሰ የኢትዮጵያን ደህንነት እና ህልውና የማስከበር ታሪካዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ በጠላት ላይ ከባድ ኪሳራ እያደረሰና ሽንፈት እያከናነበው ይገኛል ፡፡ ይህንንም ገድል አጠናክሮ ይቀጥላል” ከማለት ውጭ ስለ ጦርነቱና አድራሻለሁ ስላለው ኪሳራ የዘረዘረው ነገር የለም። መግለጫውን ከስር ያንብቡ


ጻድቃን ጦርነቱ በቀናት፣ ግፋ ቢል በሳምንታት ይጠናቀቃል አሉ፤ ጦራቸው ወደ ሩቅ ገጠሮች ማፈግፈጉን አስታውቀ

  • … በአየር ጥቃቱ አብዛኛውን ከባድ መሳሪያና ሰራዊታቸውን ወደ ሩቅ ገጠራማ ስፍራ እንዲያሸሹና እንዲያፈገፍጉ እንዳደረጋቸው ጻድቃን ለኒውዮርክ ታይም ነግረዋል….

ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በወቅታዊ ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ

አሸባሪው ህወሀት የጀመረውን ማጥቃት ፤ በማያዳግም ሁኔታ እንቀለብሳለን !

ህወሀት በሰሜን እዝ ሠራዊታችን ላይ ወረራ ( ጭፍጨፋ ) ከፈጸመ በኋላ መንግስት በወሰደው ህግን የማስከበር ዘመቻ የጠላት አከርካሪ ተሰብሮ ጁንታው ተደምስሶና የተረፈው ተበትኖ ዋሻ ገብቷል ፡፡ መንግስት ለ8 ወር ትግራይን የማረጋጋትና የመልሶ ግንባታ ስራ እየሰራ ነበር ፡፡ TPLF ግን ከተበተነበት እየተሰበሰበ በክልሉ ውስጥ ቀውስ የማባባስ ስራ እየሰራ ጎን ለጎን ደግሞ መንግስትን እና መከላከያን እየከሰሰ ቆይቷል ፡፡ የሰብዓዊ ቀውስ እንዳይባባስ ፤ ቀጣይ አመት የምግብ እጥረት እንዳይከሰት ለአርሶ አደሩ የእርሻ እድል ለመስጠት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በመወሰን ሰራዊታችን ከትግራይ እንዲወጣ ተደርጓል ፡፡

በአጠቃላይ ለክልሉ የጥሞና ጊዜ በመስጠት ህዝቡ የሚሻለውን አስቦ እንዲወስን እድል ለመክፈት ሲባል መንግስት ተኩስ በማቆም ሀላፊነት የተሞላው ውሳኔ ወስኖ እንደነበር ይታወቃል ፡፡

አሸባሪው ህወሀት ግን ተመሳሳይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የመከላከያ ሰራዊታችንን ተከታትሎ በማጥቃት ግጭቱን ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በማስፋፋት በትግራይ እንዳይደርስ የተፈለገውን ቀውስ ወደ ሁለቱ ክልሎች አስፋፍቶታል ፡፡

ግጭቱን ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በማስፋፋት የህዝብ መሰረተ-ልማቶችን እያፈረሰ ወስዷል ፡፡ መውሰድ ያልቻለውን አውድሟል ፡፡ ንጹሀን ዜጎችን ገድሏል ፡፡ የአርሶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን ቤት አቃጥሏል ፤ ከብቶቻቸውን የሚበላውን በልቶ ቀሪውን ገድሏል ፤ እጸዋቶችን አጥፍቷል ፤ አዝዕርቶችን አጭዶ ወስዷል ፡፡

ጁንታው “የጅቡቲን መስመር ለመቁረጥና ወልቃይት ጠገዴን በማጥቃት በሱዳን በኩል ኮሪደር ለማስከፈት” የሚል ዓላማ ይዞ ተደጋጋሚ እና መጠነ ሰፊ ማጥቃት ፈጽሟል ፡፡ “በሁለት ሳምንት አዲስ አበባ ለመግባት” በሚል በሰሜን ወሎ በኩል ሰፊ ማጥቃት ስያከናውን ከርሟል ፡፡ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ይህንን ሀገር የማፍረስ የጁንታ እቅድ እንዲመክን አድርጓል ፡፡ እጅግ ከባድ ኪሳራም አድርሶበታል ፡፡

ከሦስት ቀን በፊት በራሳቸው አንደበት ሌ/ጀ ጻድቃን የተባለው የጁንታው አባል ፤ ” …ጦርነቱን እናሳጥረዋለን ፤ በሁለት ሳምንት አዲስ አበባ እንገባለን ፤ ፖለቲካዊ ፣ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታን እንቀይራለን …” በሚል ባወጀው ጦርነት በሁሉም ግንባሮች ውጊያ ከፍቶ ይገኛል ፡፡ ራሳቸውም በለኮሱት ውጊያ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን እና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጥምረት እየተቀጠቀጠ ይገኛል ፡፡

ያጁንታው መሪ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ከሦስት ቀን በፊት የሌ/ጀ ጻድቃንን መግለጫ በማጠናከር “…ኢትዮጵያውያንን እንደ አባቶቻቸው በመቅበር ሰላማችንን እናረጋግጣለን…” የሚል ዕቅድ እንዳላቸው በሚዲያ ገልጸው እቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በሁሉም ግንባር ከሰኞ ጀምሮ ውጊያ ከፍተዋል ፡፡ በጀመሩት ውጊያ አይቀጡ ቅጣት እየደረሰባቸው ይገኛል ፡፡

የመከላከያ ሠራዊታችን የጁንታውን ጥቃት የመመከት ውጊያ እያካሄደ የጠላትን ወራሪ ሀይል መመከት ብቻ ሳይሆን እየደመሰሰ የኢትዮጵያን ደህንነት እና ህልውና የማስከበር ታሪካዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ በጠላት ላይ ከባድ ኪሳራ እያደረሰና ሽንፈት እያከናነበው ይገኛል ፡፡ ይህንንም ገድል አጠናክሮ ይቀጥላል ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች ፡፡

Leave a Reply