በሕገወጥ የመሬት ወረራ በተሳተፉ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች አካላት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው

በአዲስ አበባ በሕገወጥ የመሬት ወረራ በተሳተፉ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች አካላት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ ሕገወጥ የመሬት ወረራና ቤት ግንባታ መከላከልን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው በርካታ የመሬት ይዞታዎች በሕገወጥና ባልተገባ መንገድ ተወረው ሕገወጥ የይዞታ ማረጋገጫ ጭምር ተሰርቶላቸው መገኘቱን ገልጸዋል።

በሕገወጥ የመሬት ወረራው የተሳተፉ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች አካላት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሆነም ነው አቶ ጥራቱ የተናገሩት።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተውን ጦርነትና 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ሽፋን በማድረግ የነበረውን የሕገወጥ መሬት ወረራ ፍላጎት ለመከላከል ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተግባራትን መከወኑን ጠቅሰዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከመሬት ይዞታና አገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር ለመግታት የተለያዩ ስርዓቶች እየተበጁ መሆኑን አመላክተዋል።

መዲናዋ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የዲፕሎማቲክ መናኸሪያ በመሆኗ ዘመናዊና ለነዋሪዎቿም ምቹ ገጽታ እንድትላበስ ለማድረግ የመሬት ፕላን ተዘጋጅቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሕገወጥ የመሬት ወረራ በተጨባጭ የወንጀል ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ የስራ ኃላፊዎችን የመለየት ስራ መከናወኑንም ገልጸዋል።

ከልየታው በኋላም በሕገወጥ የመሬት ወረራ ድርጊት ላይ የተሳተፉ አካላት ላይ አስተዳደራዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

በየደረጃው ያሉ የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት ማኔጅመንት የቢሮ ኃላፊዎች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ማድረግን ጨምሮ ዝርዝር ማስረጃዎችን በመንተራስ በፍትህ አካላት በወንጀል እንዲጠየቁ የማድረግ ሂደት መጀመሩንም ገልጸዋል።

ሕገወጥ የመሬት ወረራውን ለመከላከል ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ፣ የአርሶ አደሩን መብት ሽፋን በማድረግ መብቱ ለማይገባቸው አካላት የይዞታ ማረጋገጫ የሰጡና መታወቂያ የሰሩ ከክፍለ ከተማ ስራ አስፈፃሚ እስከ ወረዳ ድረስ በሚገኙ አመራሮች ላይ እርምጃው መቀጠሉንም ጠቁመዋል።

አቶ ጥራቱ አክለውም መሬት በሕገወጥ መንገድ በመሸጥና በማስተላለፍ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመደገፍ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ አካላትን ፍላጎትም የመሬት እንቅስቃሴውን በመግታት ማምከን ተችሏል ብለዋል።

ለመዲናዋ አርሶ አደሮች 2 ሺህ 170 ካርታዎች መተላለፋቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከዚሁ ውስጥ 497 የሚሆኑት በሕገወጥ መንገድ ለማይመለከታቸው አካላት መተላለፉ ተገልጿል።

በሕገወጥ መንገድ የተያዘ ከ100 ሄክታር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉን የገለፀው ከተማ አስተዳደሩ 252 ከሚሆኑት አረንጓዴ ስፍራዎች 35ቱ በሕገወጥ መንገድ በግለሰቦች ተይዘው መገኘታቸው ተነግሯል።

አቃቂ፣ ኮልፌ፣ ቦሌ፣ ለሚ ኩራ እና የካ ክፍለ ከተሞች በቅደም ተከተል ከፍተኛ ሕገወጥ የመሬት ወረራ የታየባቸው አካባቢዎች መሆናቸውም ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

የከተማዋ ነዋሪ ሕገወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል እስካሁን ሲያደርግ የቆየውን ጥቆማ የመስጠት ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ተጠይቋል።

ENA

Leave a Reply