አልጄሪያ የዓረብ ሊግ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ሚዛናዊና ትክክለኛ አቋም እንዲይዝ ትሰራለች

አልጄሪያ የዓረብ ሊግ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ሚዛናዊና ትክክለኛ አቋም እንዲይዝ ለማድረግ እንደምትሰራ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታን ላማምራ ገለጹ።

በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።

ውይይታቸውን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መግለጫ ሰጥተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከላይቤሪያ፣ ቡሩንዲ፣ አልጄሪያ፣ ዩጋንዳና ቤኒን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ከአልጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታን ላማምራ ጋር ባደረጉት ውይይት የዓረብ ሊግ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የያዘው አቋም የተዛባና የተሳሳተ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።

ይህን ተከትሎም የአልጄሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግድቡን በተመለከተ ሊጉ ሚዛናዊና ትክክለኛ አቋም እንዲይዝ ለማድረግ አገራቸው እንደምትሰራ ይፋ አድርገዋል።

በወቅቱ የዓረብ ሊግ ለግብጽ እና ለሱዳን ያደላ አቋም መያዙን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “ይህንን የተሳሳተ አቋም ማስተካከል አለበት” ብለዋል።

በቀጣዩ ወር የዓረብ ሊግ ሊቀ መንበርነትን የምትረከበው አልጄሪያ ሊጉ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያለውን አቋም እንድታጤነው ጠይቀዋል።

የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታን ላማምራ በበኩላቸው፤ የዓረብ ሊግ በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ሚዛናዊና ትክክለኛ አቋም እንዲይዝ አልጄሪያ ትሰራለች ማለታቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተመሳሳይ ከቡሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልበርት ሺንጊሮ ጋር መምከራቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ENA

Leave a Reply