ከአማራ ክልል መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

የሰሜን ጎንደር፣ የሰሜን ወሎና የዋግኽምራ ህዝብ ከወራሪው ቡድን ነጻ ለማውጣት በሚደረገው ትግል መሳሪያ ያለው በመሳሪያው፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ትርፍ ሀብትና ንብረት ያለው በገንዘቡ፣ ሐሳብ ያለው በሐሳቡ ከአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ከሚሊሺያና ፋኖ ጎን በመሰለፍ የአሸባሪውን ቡድን ግብአተ መሬት ማረጋገጥ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

የአማራ ሕዝብ ህልውና ጸንቶ የሚኖረው በአሸባሪው ትህነግ መቃብር ላይ ነው።

የጀመርነውን የህልውና ዘመቻ ሳንቋጭ ሀሳብና ተግባራችን ከዓላማና ግባችን መንቀል ከፍተኛ ዋጋ እንዳያስከፍለን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የህልውና ዘመቻው ተገደን የገባንበት እንደህዝብ የመኖርና ያለመኖር መጻኢ እጣፋንታችን የምንወስንበት እንጂ የፓለቲካ ማሳለጫ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ፓለቲካም ይሁን ስልጣን ህዝብና አገር ከመኖራቸው በሗላ የሚታሰቡ እና የሚመጡ ናቸው። ያለህዝብና ያለአገር የሚኖር ፖለቲከኛም ሆነ ስልጣን አይኖርም። አይታሰብምም።

በአማራ ህዝብ ላይ እያንዣበበ ያለው የህልውና አደጋ፤ አደጋ ብቻ አይደለም። ለክልሉ መንግስት ይሁን የአማራ ህዝብ “ከህልውና ዘመቻው” የሚቀድም አንዳች አጀንዳ አይኖረውም። በሴራና በተንኮል ጥርሱን ነቅሎ ያደገው አሸባሪው ቡድን የእድሜ ልክ ምኞቱና ፍላጎቱ በስውር የአማራን ህዝብ አንገት ማስደፋት እና ማህበራዊ እረፍት መንሳት ነበር። ይህ በሴራ ተጠንስሶ በሴራ ተወልዶ የኖረን ቡድን ከዘመናት ሴራና ተንኮሉ ባሻገር በግላጭ በአማራ ህዝብ ላይ ወረራ ፈጽሟል።

በክልሉ በግልጽ ወረራ በፈጸመባቸው በሰሜን ወሎ፣ ዋግኽምራ፣ በከፊል ደቡብ እና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ቁጥሩ በውል የማይታወቅ የአማራ ህዝብ በጅምላ ተጨፍጭጭፏል። ለዘመናት ለፍቶ ፣ ጥሮና ግሮ ያፈራው ሀብትና ንብረቱን በወራሪው ሀይል ተዘርፏል፤ ወድሟል። የመንግሥት እና የግል አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ዘርፏል።

ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የአማራ ህዝብ ከሞቀ ሀብትና ንብረቱ ተፈናቅሎ ለአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ተዳርጓል። ከሕጻን እስከ እርጅና የእድሜ ደረጃ የሚገኙ እህቶቻችን በዚህ አሸባሪ ቡድን በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍረዋል። አሁንም የሚፈጽመው ወረራ፣ ዝርፊያና ጭካኔ የተሞላበት ጅምላ ጭፍጨፋው እንደቀጠለ ነው። ለዚህ አሸባሪና ወራሪ ቡድን ጊዜ በተሰጠው ቁጥር ችግሩና ጥፋቱ ከዚህም የከፋ ይሆናል።

ከጦርነት ቀጣናው ባሻገር ባሉና አማራ በሚኖርባቸው በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በደቡብ ክልል ማንነትንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ግድያና መፈናቀል የሚመነጨው ከዚሁ አሸባሪ ቡድንና የእርሱ ተላላኪ ባንዳዎች መሆኑን መናገር ደግሞ ለቀባሪ ማርዳት ነው። ዛሬም ሆነ ትናንት በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚፈጠሩ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጅምላ ግድያዎች እና ግጭቶች ተዋናይ፣ አጋፋሪውና መሪው ከዚህ የጥፋት ቡድን የሴራና ተንኮል መንገድ የሚመነጩ እና የተቀዱ ናቸው።

አሸባሪው ትህነግና ግብረ አበሮቹ ከኢትዮጵያ ምድር እስከወዲያኛው እስካልተነቀሉ ድረስ የአማራ ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ህልውና በጽኑ መሰረት ላይ አይቆምም። ከዚህ አኳያ የአማራ ህዝብ ህልውናም ሆነ የኢትዮጵያ ትንሳኤ የሚረጋገጠው ትህነግ መቃብር ላይ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም።

ስለሆነም በአሸባሪው ቡድን እኩይ ተግባር ምክንያት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ በጋራ መረባረብ ይኖርብናል። የሰሜን ጎንደር፣ የሰሜን ወሎና የዋግኽምራ ህዝብ ከወራሪው ቡድን ነጻ ለማውጣት በሚደረገው ትግል መሳሪያ ያለው በመሳሪያው፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ትርፍ ሀብትና ንብረት ያለው በገንዘቡ፣ ሐሳብ ያለው በሐሳቡ ከአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ከሚሊሺያና ፋኖ ጎን በመሰለፍ የአሸባሪውን ቡድን ግብአተ መሬት ማረጋገጥ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

ምክንያቱም የአማራ ህዝብ ህልውናም ሆነ የሀገራችን ሰላም የሚረጋገጠው በአሸባሪው ትህነግ መቃብር ላይ ነው!

Leave a Reply