“ጭፍራ ከተማና ሰላማዊ ዜጎች በከባድ መሳሪያ እየተደበደቡ ነው” አፋር ክልል

ጭፍራ ከተማን ለማውደም ትህነግ ከባድ መሳሪያ እያዘበ እንደሆነ፣ ድብደባው የታጠቀውን ሃይል ሳይሆን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑና የዘር ማጥፋት ተግባር እንደሆነ የአፋር ክልል ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት አመለከተ። የትግርያ ሕዝብ ነጻ አውጪ በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም። ሙሉ በሙሉ ከታች ያለውን ያንብቡ።

ጁንታው ሰላማዊ ዜጎችን ታርጌት ያደረገ የከባድ መሳሪያ ድብደባ በጭፍራ እያደረገ ነው! አሸባሪው ህወሀት በአፋር ጭፍራ ወረዳ በኩል ንፁሀን ሲቪሎችን ቀጥታ ኢላማ ባደረገ መልኩ፣ ከተማውን የማውደም እና የዘር ማጥፋትን ያለመ ጥቃት በከባድ መሳሪያ በመታገዝ እየፈፀመ ይገኛል።

ከተማን በከባድ መሳሪያ ማውደም ከባድ ወንጀል ነው። ጁንታው የተያያዘው ንፁሀንን ማሸበርና በመድፍ የታገዘ ድብደባ በጭፍራ ወረዳ እያካሄደ ነው። ወራሪው ጁንታ በጋሊኮማ ያደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል አልበቃ ብሎት ከሰሞኑ ደግሞ በአፋር በተለያዩ አካባቢዎች በበራህሌ፣ በመጋሌ፣ በኡዋ እና በጭፍራ በኩል ከርቀት ከባድ መሳሪያ ንፁሀንን ሲቪሎችን ኢላማ ያደረገ ተኩስ ከፍቷል።

ንፁሀንን መግደል እና ዘር ማጥፋት ዘመቻን ስራዬ ብሎ የተያያዘው ጁንታው በአፋር በፈንቲ ረሱ በኩል እና በኪልበቲ ረሱ ዞኖች በኩል ካሁን በፊት ያደረገውን ወረራ የአፋር ልዩ ሀይል፣ ሚሊሺያ እና ህዝባዊ ሰራዊት በሚገባ በመመከት ወደ መጣበት በመመለስ የደረሰበትን ኪሳራ ለመሸፈን በሚመሰል መልኩ ከሰሞኑ ከርቀት ከባድ መሳሪያዎችን ንፁሀንን ኢላማ ባደረገ መልኩ መተኮስ ይዟል።

ጁንታው በፈንቲ ረሱ ወረራ ባደረገ ጊዜ የተፈናቀሉ ሴቶች፣ ህፃናትና አዛውንቶች እና ህፃናት የተጠለሉበት ጊዚያዊ ማረፊያዎችን ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ኢላማ ባደረገ መልኩ ነው ዘመቻውን በአፋር ንፁሀን ላይ የከፈተው አሸባሪው የህወሀት ጁንታ። አሸባሪው ህወሀት በአፋር ታሪክ የማይሽር ጠባሳን በጋሊኮማ ንፁሀንን በመጨፍጨፍ ጥሎ ያለፈ ሲሆን አሁንም ዳግም ያንን ክፉ ታሪክ ለመድገም በሚመሰል መልኩ በከባድ መሳሪያ ድብደባ ጀምሯል።

በአፋር ንፁሀን ደም ላይ “ታላቋን ትግራይ” ለመመስረት አልሞ የተነሳው አሸባሪው ህወሀት በአፋር ባደረገው ወረራ በርካታ ንፁሀን አርብቶ አደሮችን ጨፍጭፏል፣ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል። በርካታ ህዝባዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣ ወዘተ እንዲሁም የሀይማኖት ተቋማት መስጂዶችና መድረሳዎችንም ጭምር አውድሟል። በዚህም የአፋር ህዝብ ላይ ትልቅ ኪሳራን አድርሷል።

ይሁንና የአፋር ህዝብ ባደረገው ብርቱ ተጋድሎ አሸባሪው ህወሀትን ወደመጣበት እንዲመለስ አድርጓል። አሁንም በድጋሚ አፋርን ለመውረር ከመጣ የአፋር ህዝብ ለጁንታው የሚገባውን ሰጥቶ ወደመጣበት በድጋሚ የሚመልሰው ይሆናል። እዚህ ላይ ምንም መረሳት የሌለበት ጉዳይ ምንም የማያውቁ ህፃናት እና አዛውንቶችን፣ ንፁሀን ሴቶችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት የፈሪነት ምልክት እንጂ ጀግንነት አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

አሸባሪው ወራሪው ህወሀት ህፃናት እና ሴቶችን እንዲሁም አዛውንቶችን ኢላማ ከማድረግ ባሻገር፣ የአፋር አርብቶ አደር የኢኮኖሚ መሰረት የሆነውን እንስሳውን ግመል፣ ከብት እና ፍየል ጭምር በከባድ መሳሪያ በመደብደብ ህዝባችን ላይ የሚደርሰው ጉዳት እጥፍ ድርብ እንዲሆን በማድረግ ላይ ይገኛል። በመጨረሻም የአፋር ህዝብ ካሁን ቀደም እንዳደረገው ሁሉ አሸባሪው ህወሀት በገባበት የአፋር ክልል በኩል ሁሉ መቀበሪያው እንደሚሆን ፣ ህዝባችንም ወረራን ለመመከት የቀድሞ ታሪኩን አሁንም የሚደግም ይሆናል።

ምንጭ፡ አፋር ክልል ኮምዩኒኬሽን

Leave a Reply