አየር ሃይል የተመረጠ የታጣቂ ማሰልጠኛና መሳሪያ ማከማቻ አጠቃ

የኢትዮጵያ አየር ሃይል ቀደም ሲል የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ይጠቀምባቸዋል ያላቸው የመገናኛ አውታሮችና መሳሪያዎች፣ ዛሬ ደግሞ የጦር መሣሪያ ማምረቻ እና የጦር ትጥቅ ጥገና ይካሄደበታል ያለውን ጣቢያ መርጦ እንዳጠቃ ታውቋል። አቶ ጌታቸው የመኖሪያ አካባቢን ማዕከል ያደረገ እንደሆነ ጠቁመው ድርጊቱን ኮንነዋል። ጥቃቱን ተከትሎ ግን በንጹሃን ሰዎች ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ አልተሰማም።

ስለ ጥቃቱ የስልክ መልስ እንዳልሰጠና መረጃ እንደከለከለ ቢወቀስም የመንግሥት የወቅታዊ መረጃ አጣሪ በትዊተር ገጹ እንዳለው ጥቃቱን አስመልክቶ የተዛባ መረጃ እንደሚሰራጭ አውስቶ መረጃ ሰጥቷል።

የአየር ጥቃት መፈጸሙን ያረጋገጠው የመንግስት አንደበት ” ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው የህወሓት የጦር መሳሪያ ማምረቻና መጠገኛ ጣቢያዎችን ነው” ብሏል። አክሎም ኦፕሬሽኑ ያነጣጠረው እነዚህኑ “የጦር መሣሪያ ማምረቻና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎችን ብቻ ነው” ሲል ማረጋገጫ ሰጥቷል።

የመንግስት የውቅታዊ መረጃ “የሽብር ድርጅቱ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ለመሸሸግ የሚጠቀምባቸውንና ወደ ወታደራዊ መገልገያነት የቀየራቸውን የተወሰኑ ቦታዎች ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ያለመ ነው” እንደሆነ አመልክቷል።

አካባቢውን በደንብ የሚያውቁ ስለ አየር ጥቃቱ ሲጽፉ እንዳሉት በመቐለ የሚገኘው መስፍን ኢንደስትሪያል መሆኑን፣ ድርጅቱ ቅርጹን ቀይሮ የጦር መሳሪያ ማዘጋጃና የሎጅስቲክ ማቀናበሪያ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ምልልሱ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ በይፋ ባይገለጽም ዛሬ ረፋዱ ላይ የተካሄደው የአየር ጥቃት ዒላማውን ያሳካ እንደነበር ተመልክቷል። አቶ ጌታቸው ረዳ ጥቃቱ መሰንዘሩን ተከትሎ በቲውተር አምዳቸው ” በግንባር እየተሸነፈ ነው” ያሉት መንግስት ያካሄደው ጥቃት መኖሪያ ቤቶችን ዒላማ ያደረገ መሆኑንን አመልክተዋል።

በጥቃቱ የደረሰውን ጉዳት ያላብራሩት አቶ ጌታቸው የንጹሃን ሕይወት ስለማለፉ በቀቱ ያሉት ነገር የለም። እሳቸውን፣ የዕርዳታ ሰራተኞችንና ምንጮቻቸውን የጠቀሱ ሚዲያዎችም ሰው ስለመሞቱ አልዘገቡም። ይልቁኑም ወታደራዊ ተቋም መመታቱን አምነው የጻፉም አሉ።

ጥቃቱ የደረሰበት ስፍራ መስፍን ኢንጂነሪንግ

“ደሴን እይዛለሁ” ብሎ የአማራ ክልልን ዘልቆ የገባው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በትግራይ አየር ክልል የአየር ጥቃት ከቶውንም እንደማይታሰብ በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ ነበር።

“ሰኞ በተካሄደው የአየር ጥቃት ዒላማ የነበሩት ትህነግ ይጠቀምባቸዋል የተባሉ የመገናኛ መረቦችና መሳሪያዎች መሆናቸውን፣ በጥቃቱ ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎ በተሳካ ሁኔታ ተፈጽሟል” ሲል ኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ሰላማዊ ዜጎችን እያፈናቀለና በግልጽ ዓላማው ግልጽ ባልሆነ ጥቃት በርካቶችን ለመከራ እየዳረገ ያለው ጦርነት አስከፊ እየሆነ ነው። ትህነግ ሰፊ የአማራ ክልል የወረረበትና ዝርፊያና ጭፍጨፋ በንጹሃን አርሶ አደሮች ላይ የሚፈጽምበት፣ የአፋርን ሕዝብ የሚገልበት ምክንያት ለበርካቶች ግራ እንደሆነ ነው የሚነገረው።

በወልቃይትና ራያ በኩልን ያለን የማንነት ጥያቄ መንግስት እያለ በወጉ ያላስኬደው ትህነግ፣ አሁንም ጉዳዩን በአገሪቱ ሕግ መሰረት ማስኬድ እየቻለ ለምን ይህን መንገድ እንደመረጠ ሊያስረዳ አለመቻሉም ሌላው ግራ የሚያጋባ ጉዳይ እንደሆነ በርካቶች ይገልጻሉ። በሰላማዊ መንገድ ካልተቻለ “የኔ” የሚለውን ስፍራ ለማስለቀቅ ” የኔ” በሚለው ስፍራ ሃይል ለመጠቀም መሞከር ቢያንስ ምክንያታዊ ያደርጋል የሚሉ ወገኖች ” ወሎዬን፣ አፋርን፣ ድፍን ጎንደሬን …ለማጥፋት መነሳት ወደ ከፋ ቀውስ ከማምራት የዘለል መፍትሄ አያመጣም” ይላሉ።

የትግራይ ወጣት እያለቀ ነው። ከመከላከያም፣ ከሚሊሻም፣ ከልዩ ሃይልም በተመሳሳይ እየሞቱ ነው። በትግራይም በሌሎችም ከተሞች ሃብት እየወደመ ነው። ሕዝብ የሚበላ አጥቶ እየረገፈ ይገኛል። ኮሮና በፍጥነት እየቀጠፈ ነው። የኑሮ ውድነትና እጥረቱ ሁሉንም የህበረተሰብ ክፍል እያነደደው ነው። ይህ ሁሉ ውድመትና ጥፋት ለጥቂት ስልጣን ላይ ካልሆኑ መኖር ለማይችሉ ቁንጮ ፖለቲከኞች ሲባል መሆኑ በስፋት ይገለጻል።

በሌላ በኩል በዚህ የህዝብ ስቃይና የአገር መከራ ለመነገድ የሚሯሯጡ መኖራቸው ሲታይ ቢያንስ ለነብሰጡርና ለህጻናት እንኳን አለማዘናቸው ሲታሰብ ነገሩን ተስፋ አስቆራጭ ያደርገዋል።

Leave a Reply