የጎንደር አርሶአደሮች ወደ ውሎ እና አፋር ግንባር ዘመቱ

በሰልፍ በሰልፍ ሆነው አውራ ጎዳናው ላይ ይታያሉ። ሁሉም ያለውን መሳሪያ አንግቧል። ህጻናቱ የጀግኖቹን ስንቅ እና ጓዝ ተሸክመው በማገዝ እየሸኟቸው ነው። “ወሎም አፋርም የእኛው ወገን ነው፤ ሁሉም ኢትዮጵያ ነው ብለን ወደግንባር እየዘመትን ነው” የሚሉት አትንኩኝ ባይነት ስሜት የሚነበብባቸው የጎንደር አርሶአደሮች ናቸው። አርሶአደሮቹ ወደግንባር ሲጓዙ ያገኟቸው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች አነጋግረዋቸዋል።

ከአንዳቤት ወረዳ የመጡት አርሶአደር አልማው እንይ እና ቢያርጌ ውቡ መሳሪያቸው ይዘው ወደ ወሎ ግንባር የሚዘምቱት እንደነሱ ንጹሃን የሆኑ ወገኖቻቸውንከአሸባሪው ጥቃት ለማዳን መሆኑን ይናገራሉ።የአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም አፋርን በወረራ የያዘው አሸባሪ ሁድን ወገኖቻችንን እያሰቃየ መሆኑ እንቅልፍ ነስቶናል። ስለዚህ በቦታው ተገኝተን ልንዋጋው እያቀናን ነው።

በመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ተቀናጅተን በጀግንነት በመፋለም ንጹሃን ወገኖቻችችን ነጻ እንደምናወጣቸውም እርግጠኛ ነን ሲሉ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል። የላይ ጋይንት ወረዳ አርሶአደር 10 ዓለቃ ደስታው ተስፋው በበኩላቸው፤ ሀገር በወራሪ ስትደፈር እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ እንደሌለለብን እናውቃለን። በመሆኑም ወራሪውን ከአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎች ጠራርጎ ለማስወጣት ቆርጠን ተነስተናል።

መንግስት ያወጣውን የክተት ጥሪ በመቀበል ወደግንባር ስንዘምት በደስታ ነው ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።ከልጃቸው ጋር ያገኘናቸው ሌላኛው ዘማች አርሶአደር ካሳው መልካሙ ናቸው። ከአባቱ ጋር በእግሩ 15 ኪሎሜትር ተጉዞ የመጣው ልጃቸው አቅፎ ከሳመ በኋላ “በጀግንነት እንደምትመለስ አልጠራጠርም” ብሎ ሲሰናበታቸው አገኘናቸው። አባትም “የሀገር አደራ ነውና በጀግንነት እንደምመለስ አልጠራጠርም።

ሀገር ስተወረር ዝም ብሎ የሚቀመጥ ልብ የለኝም፤ አገሬ ተወርራ ከማይ ሞቴን እመርጣለሁ ብዬ ተነስቻለሁ” ብለው ወደግንባር ዘምተዋል።ከጎንደር አርማጭሆ፣ በለሳ፣ እብናት፣ እስቴ ጉና እና ከተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ አርሶአደር እና ሚሊሻዎች ወደየግንባሮቹ በመዝመት ላይ ናቸው። ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍልም የእኛን አርዓያ በመከተል በነቂስ ወደየግንባሮቹ ሊዘምት ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

\በጌትነት ተስፋማርያም (ጋይንት ኢ ፕ ድ)

You may also like...

Leave a Reply