ሱዳን – የቁም እስረኛው ሓምዱክ ሕዝቡ አብዮቱን እንዲጠብቅ ጥሪ አቀረቡ

በወታደራዊ ቡድኑ የቁም እስረኛ ሆነው የሚገኙት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ሕዝቡ ሰላማዊ ትግልን እንዲቀጥልና ‹አብዮቱን እንዲጠብቅ›› ጥሪ ማቅረባቸው ተሰማ። የሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገፁ ይፋ እንዳደረገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝቡ የሰላማዊ ትግል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን አስሮ የሚገኘው የወታደራዊ ቡድኑ አብደላ ሃምዶክ የመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊ እንደሆኑ አድርገው ለሕዝቡ መግለጫ እንዲሰጡ ጫና እያሳደረ መሆኑን የሚኒስቴሩ ገጽ አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠየቁትን ባለማድረጋቸው ባልታወቀ ቦታ እንዲታሰሩ መደረጉን ገጹ አስረድቷል።

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ማንነታቸው ባልታወቁ ወታደራዊ ኃይሎች ዛሬ ማለዳ መኖሪያ ቤታቸው ተከብቦ የቤት ውስጥ እስረኛ እንደተደረጉ አል ሃዳድ የተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል።

ሃምዶክ ላይ ይህ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የሱዳን ጦር የጠቅላይ አዛዥ የሚዲያ አማካሪና የሀገሪቱን ገዥ ሉዓላዊ ምክር ቤት አባል ጨምሮ በርካታ የሲቪል ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ባለፈው ወር ያልተሳካ የመፈንቅለ መንግስት ሴራ መደረጉን መንግስት ማሳወቁን ተከትሎ በወታደራዊውና በሲቪል ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል። በካርቱም የኢንተርኔት አገልግሎት በዚህ ሰዓት የተቋረጠ በመሆኑ ምን እየተደረገ እንዳለ መረጃ ለማግኘት አዳጋች እንደሆነ ተገልጿል። የመረጃ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ቃል አቀባይ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቁሟል።

እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሚንስትሮች፣ የመንግስት ሀላፊዎች እና የፓርቲ መሪዎች መካከል ቀጥሎ የተጠቀሱት አሉበት ተብሏል፡፡

1. የመገናኛ ሚንስትር ሃሺም ሀሰበአልረሱል

2. የኢንዱስትሪ ሚንስትር ኢብራሂም አልሼክ

3. የማስታወቅያ ሚንስትር ሀምዛ በሉል

4. የሚንስትሮች የካቢኒ ጉዳዮች ሀላፊ ካሊድ ዩሱፍ

5. ሉዓላዊ የሽግግር ምክር-ቤት አመራር አባል መሀመድ አልፈኪ

6. የሱዳን ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበር ኡመር አደግበር

7. የአረብ ትንሳኦ ፓርቲ ሊቀመንበር አሊ አልረያህ አልሰንሁሪ

8. የካርቱም ከተማ ከንቲባ አይመን ኒሚር እና

9. የዲሞክራሲያዊ ለውጥ አብዮት ቃል-አቀባይ ጃፈር ሀሰን መሆናቸው ተገልጿል። የሀሚቲ ጦር የካርቱም ከተማ አስፈላጊ ቦታዎችን እንዲጠብቅ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።

Leave a Reply