ስንዴንና ሩዝን ከውጪ ማስገባትን ለማስቀረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በእርዳታና በግዢ የሚገባ ስንዴንና ሩዝን ለማስቀረት እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ ከውጭ በግዢና በእርዳታ ይገቡ የነበሩትንና አሁንም በብዙ ወጪና ውጣ ወረድ ለምግብ ፍጆታ እንዲውል የሚገባውን የስንዴና የሩዝ እህልን በቀጣይ ከአምስት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት በግዢና በእርዳታ ከውጭ በዋናነት ስንዴ፣ ሩዝ፣ የምግብ ዘይት ፣ አልፎም የቢራ ገብስ፣ ታስገባ እንደነበር የተናገሩት አቶ ኢሳያስ ፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሀገር ደረጃ በአቅጣጫ ትኩረት ተሰጥቶት መንግሥት ስንዴን፣ ሩዝንና የምግብ ዘይትን ከውጭ ማስገባትን ለማስቀረት እየሠራበት ነው ብለዋል።

የሀገሪቱን የሰብል ልማት የትኩረት አቅጣጫ እውን ለማድረግና በአርሶ አደሮቹ ማሳ የሚመረተውን የስንዴ ምርት መጠን ከፍ ማድረግ እንዲቻል በባለሀብቶችም ጭምር በማሳተፍ በቀጣይ ከአራት መቶ ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት እንደሚታረስ አቶ ኢሳያስ ገልጸዋል።

በመስኖ ልማትን የመደገፍ ሥራ በሰሜኑ ሀገራችን ብቻ ሳይገደብ በደቡብም የሚቀጥልበት ሁኔታ መኖሩን አመላክተዋል።

የማስፋፊያ ሂደቱ በተጀመረባቸው በአፋር፣ በሶማሊ፣ የአፋር አጎራባች የከፊል ኦሮሚያ፣ የደቡብ ኦሞ አካባቢዎች፣ ስንዴ ለማምረት የተያዘ አቅጣጫ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህንንም ወደ ተግባር ለመቀየር በተደረገው ጥረት በኦሮሚያና በአማራ በውሃ ገብ አከማባቢዎች ላይ በስፋት ሥራው መጀመሩን ጠቁመዋል።

በተደረገው ጥረትም ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረበት የሙከራ ሥራ አሁን ወደ 187 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ ከ7ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ መገኘቱን ገልጸዋል። ተሞክሮውን በቀጣይ ለማስፋት እንደታሰበና ከዚህ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ተናግረው ፣ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ስንዴን ከውጭ የማስገባት ሥራን ለማስቀረት አንዱ መፍትሔ በቆላማ አካባቢዎች ስንዴን ምርት በስፋት ማምረት አንዱ ስልት ተደርጎ እየተሠራበት ነው ብለዋል።

ለዓመታት በባለሀብቶች የሚታረሰውና የሚለማው መሬት አነስተኛ እንደነበር የገለጹት አቶ ኢሳያስ ፣ የባለሀብቶቹ ምርት መጠን ከገበሬ በታች ነበር። በቀጣይ የባለሀብቶቹን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ዓመታት በሀገሪቱ የሰብል እርሻ ልማት ዘርፍ ባለሀብቶቹን በማበረታታትና ወደ ዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩ በማድረግ ምርታማነትን የማሳደግ ሥራም በትኩረት ይሠራል ሲሉ አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል።

ሙሳ ሙሀመድ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2014

Leave a Reply