የትግራይ ነጻ አውጪ ኩታበር ገባሁ አለ፤ መንግስት ሙትና ቁስለኛ ሆኖ መበተኑና የተቀረውም እየታደነ መሆኑን ገለጸ

ፎቶ የትግራይ ሃይሎች በወረሯቸው አካባቢዎች የደረሰ ዕህል በደቦ ሲያጭዱ የሚያሳይ፣ ምንጭ የደሴ ወጣቶች

መቀለ የሚገኘው የጀርመን ድምጽ ዘጋቢ ትህነግ በሰጠው መግለጫ ኩታበርን መቆጣጠሩን እንደዘገበለት በመጥቀስ በፌስ ቡክ ገጹ አስፍሯል። የጀርመን ድምጽ የኢትዮጵያን መንግስት ዘገባ ለምን እንዳካተተ አላስታወቀም። ይሁን እንጂ መንግስት ማምሻውን ባሰራጨው መግለጫ በወሎ ግንባር በወረባቦ፣ በተሁለደሬ፣ ኩታበርና ደላንታ በወሰዱት የፀረ ማጥቃት ርምጃ በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሱ መሆኑን ይፋ አድርጓል። እማኞች አስከሬን በሲኖ ትራክና በከፍተኛ የጭነት መኪኖች ሲጓጓዙ ማየታቸውን አመልክተዋል።

አቶ የሚሊዮን ኃይለስላሴ የሚባሉት የጀርመን ድምጽ ዘጋቢ ክመቀለ መግለጫ ሰማሁ ብሎ እንደገለጸው ጦሩ ኮምቦልቻ በመቃረቡ የአየር እንቅስቃሴን ማገዱን ልክ አቶ ጌታቸው በቲውተር ገጻቸው እንዳሉት በተመሳሳይ አስታውቋል።

ይህ ከተባለ በሁዋላ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ” የወገን ጥምር ጦር የፀረ ማጥቃት ርምጃ፣ ወራሪውን መንጋ መውጫ መግቢያ እያሳጣው ነው” ሲል ስፍራዎችን ዘርዝሮ መግለጫ አሰራጭቷል። ይህ መግለጫ ከተሰራጨ በሁዋላም ቢሆን የጀርመን ድምጽ ዜናውን አላመጣጠነም። መግለጫው ከስር ያለው ነው።

ጀግናው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት የአማራ ልዩ ኃይል ፋኖና ሚሊሺያ በወሎ ግንባር በወረባቦ፣ በተሁለደሬ፣ ኩታበርና ደላንታ በወሰዱት የፀረ ማጥቃት ርምጃ በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሱ ነው።

ጠላት በእነዚህ አካባቢዎች ያሰለፈው ኃይል ሙትና ቁስለኛ ሆኗል። ከጥቃቱ የተረፈውም እግሬ አውጪኝ በማለት እየፈረጠጠ ይገኛል። ጠላት ያሰለፈው መንጋ ይዞት የመጣው መሣሪያ ገሚሱ ከጥቅም ውጭ ሲደረግ ገሚሱ ተማርኳል።

የጸጥታ ኃይላችን በወራሪው የሽብር መንጋ ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ኪሳራ በመሸሽ በየሸጡ፣ በየወንዙና በየጋራው እየተሽሎከሎከ የሚገኘውን የተበታተነ የጁንታ መንጋ፣ የየአካባቢው ሚሊሺያና አርሶ አደር ተደራጅቶ በመከታተል፣ የሀገር ደጀንነቱን ሊያጠናክር ይገባል።

እስካሁንም ከጀግናው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ጎን የቆመው የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሺያ ከየአካባቢዎቹ ነዋሪ ጋር እየፈጸመው የሚገኘው አኩሪ የጦር ሜዳ ገድል ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Leave a Reply