ኦፌኮ ብሔራዊ ውይይቱ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪና ሸኔ እንዲካተቱበት ጠየቀ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ በቅርቡ ይካሄዳል የተባለው የብሄራዊ ውይይት የታጠቁ ሃይሎች ሙሉ በሙሉ እንዲካተቱበት ሲል ጠየቀ። ወንጀል የሰሩና በከፍተኛ ደረጃ የመከላከያ ሰራዊትን ያሳረዱ፣ ሰላማዊ ዜጎች እንዲፈናቅሉና በጅምላ እንዲጨፈጨፉ፣ መጤ ተብለው እንዲሰደዱ አድርገዋል፣ አዘዋል፣ አመራር ሰጥተዋል በሚል ህግ ይጠይቃቸዋል የተባሉትን አስመልክቶ መግለጫው ስምና ድርጅት ጠቅሶ አልጠየቀም። ሙሉ መግለጫውን ያንብቡ

የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ በቅርቡ ብሔራዊ ውይይትን አስመልክቶ ስለአቀረበው ሐሳብ
ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተሰጠ መግለጫ

ባለፉት ሦስት ዓመታትም ሆነ ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ውስጥ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የኢትዮጵያን ሥር የሰደደና ከምንጊዜውም በላይ እየተባባሰ የመጣውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት የሚያግዝ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ በተደጋጋሚ መጠየቁ ይታወሳል። ለምሳሌ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲወጡ ፣ ኦፌኮ ወደ ዘላቂ ዴሞክራሲ ስኬታማ ሽግግር ለማድረግ ፍቱን ፍኖታ ካርታ ለማቀናጀት ብሔራዊ የውይይት መድረክ እንዲጠራ ገንቢ ሐሳብ አቅርበናል። በቅርቡም ፣ በ 2013 ዓም አገሪቱን አንድ ማድረግ ባልቻለው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት ላይ ፣ ኦፌኮ “ፍትሐዊ ያልሆነ እና ሁሉን አቀፍ ያልሆነ ምርጫ ዴሞክራሲን ሊሸከም አይችልም” በሚል ርዕስ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ውስጥ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር መንግስት የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ተማፅኖ አዘል ሐሳብ አቅርቧል።

በአካል ወይም በመገናኛ ብዙኃን በሚታዩ ስብሰባዎች ሁሉ በተገኘው አጋጣሚሁሉ የኦፌኮ አመራሮች ተሰባሪ ሽግግሩ አገሪቱን ወደ ተጨማሪ ትርምስ እንዳያወርድ ለመታደግ የውይይትና የድርድር ጥሪ ስናቀርብ ቆይተናል። እንደ አለመታደል ሆኖ የኦፌኮ ተደጋጋሚ ጥሪ መስማት የተሳነው ጆሮ ላይ ወደቀ። የ2012 ዓም ምርጫም ሲዘገይ፤ ኦፌኮ መንግስትን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ተአማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን ለማመቻቸት አስቀድሞ ብሔራዊ መግባባትን በመገንባት ዕድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርቧል። በሚያሳዝን ሁኔታ፤ ገዥው ፓርቲ ጥሪያችንን ከመስማት ይልቅ ፓርቲያችንን በማፈን ፣ ቢሮዎቻችንን በመዝጋትና በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የኦፌኮ መሪዎችን በማሰር ያልተጠበቀ ምላሽ ሰጥቷል።

የከፋ የፖለቲካ ቀውሶች በትግራይ ጦርነት ሲቀጣጠልም፤ ኦፌኮ እንደገና ተፋላሚ ወገኖች ግጭትን እንዲያቆሙና በውይይት ለችግሩ እልባት እንዲሰጡ በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል። ሆኖም፤ ገዥው ፓርቲ እና መንግስቱ እንዲሁም ደጋፊዎቹ ሐሳባችንን በበጎነት ከመውሰድ ፓርቲያችንን ማግለል እና ማስፈራራት ላይ ያነጣጠረ አሉታዊ የሚዲያ ዘመቻ አድርገዋል። በተጨማሪም መንግስት ምርጫ ማካሄዱን ሲያስታውቅ ኦፌኮ የሀገሪቱ ሁኔታ ነፃ ፣ ፍትሃዊ እና ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ ምቹ እንዳልሆነ አስጠንቅቋል። ስለዚህ ብሔራዊ ውይይት መካሄዱ ቅድሚያ እንደሰጠው ብንጠይቅም፤ አሁንም መንግሥት የእኛን ተደጋጋሚ ጥያቄ ችላ በማለት ኦፌኮን ጨምሮ ታላላቅ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያገለለ እና የመራጩን ከፍተኛ መብት ያሳጣውን የይስሙላ ምርጫን ቀጠለ። ከወቅቱ የአገሪቱ ለመረዳት እንደቻልነው፤ ምርጫው፤ ገዥው ፓርቲ እንዳወጀው ሕጋዊነትን ወይም መረጋጋትን አላመጣም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ስለብሔራዊ ውይይት አስፈላጊነት በለሆሳስ ማወጅ ጀምሯል። ብዙዎች ግለሰቦችና ቡድኖች የመንግሥትን የውይይት ማስታወቂያን በጣም ዘግይቷል ብለው ውድቅ ያደርጋሉ። ኦፌኮ ግን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከሚቀር ዘገየ እንላለን እንጂ የታሰበው ውይይት በትክክል እና በእውነቱ ተመርቶ ኢትዮጵያን ከውድቀት ቢታደግ እንመርጣለን፡፡ ስለሆነም ብሔራዊ ውይይቱ የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ይጠበቅባታል።

1. በአሁኑ ጊዜ በሕግ ማስከበር ተጀምሮ የሕልውና ማስጠበቅ እየተባለ የሚካሄደው ጦርነት በሁሉ አቅጣጫ በአስቸኳይ ቁሞ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ እናሳስባለን፡፡

2. ውይይቱም በአለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና እና ድጋፍ በተሰጣቸው ወገኖች ሁሉ ተቀባይነት ባለው ገለልተኛ እና ተዓማኒ፣ የማያዳላና በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ባለው አካል መመራት ይኖርበታል።

3. ብሔራዊ ውይይቱ ተቃዋሚ የታጠቁ ቡድኖችን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ ቡድኖች በእውነት ያካተተ መሆን አለበት። የእነዚያን ቡድኖች ውክልና ለማንቃትም ሕጋዊ እና የደህንነት መሰናክሎች ከወዲሁ መወገድ አለባቸው።

4. የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ተፈትተው በውይይቱ እንዲሳተፉ መፍቀድ አለበት እንላለን።

በማጠቃለያም፤ ለወቅቱ ቀውስ ዋነኛ አስተዋፅዖ ካደረጉት አንዱ የሆነው በኢትዮጵያ ኤሊቶች መሀከል የመተማመን ጉድለት ነው፡፡ ስለሆነም፤ በብሔራዊ ውይይት ስም ለአንድ ወገን ወገንተኛ የሆኑ አካላት በሚጠራው ብሔራዊ ውይይት ላይ ሁሉን አቀፍ ያልሆነ ስብሰባ ቢጠራ የእርስ በእርስ ግጭትን በውይይት የመፍታት ችሎታን የማይቻል እንዲሆን ያደርጋል፡፡ መተማመንን የበለጠ ለማዳከም ብቻ ሊያገለግል ይችላል። ኦፌኮ ለብሔራዊ መግባባት የሚደረገውን ውይይት አስፈላጊነትን በመጠየቅ ግንባር ቀደም የነበረ ፓርቲ ቢሆንም፣ የታቀደው ብሔራዊ ውይይት ሂደቱ እነዚህን አነስተኛ መመዘኛዎች እስካልጠበቀ ድረስ ፣ እና የብሔራዊ ውይይቱ ሂደት በእውነተኛ መንገድ ሐቅን ያልተከተለ ከሆነ የእኛ ተሳትፎ ትርጉም የለሽ፤ አጠቃላይ ሂደቱም ከንቱ እንደሚሆን ከወዲሁ እናሳስባለን። ይህንን ኃላፊነት በትክክል እንድንወጣ መላው ኢትዮጵያዊያንና ዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ እንዲቆሙ እንጠይቃለን፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)
ፊንፊኔ፤ ጥቅምት 15/2014

Related posts:

መንግስ የጸጥታ ሃይሎች ለየትኛውም ዓይነት ትንኮሳ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ማድረጉን አስታወቀ
በትግራይ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ እየደረሰ ነው፤ ከሺህ በላይ የጭነት መኪኖች ታግተዋል፤ 76 ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ተልኳል
የደህንነት ጥናት አዲሱ ምዕራፍ - ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ
ዳግም ጦርነት እንዳይጀመር ስጋት የገባው ኢሰመኮ የማስጠንቀቂያ ጥሪ አሰማ
"ህሊናን የሚፈታተን" የተባለ ሪፖርት ይፋ ሆነ - አማራ ክልል በተወረረበት ወቅት ግብረርሰዶም መፈጸሙ ተገለጸ
ፊንላንድ 3.6 ሚሊዮን ሕዝብ የሚይዙ ዋሻዎች አዘጋጀች - ለኢትዮጵያውያን ጠቃሚ የጥንቃቄ መረጃ
"አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድንና የጥፋት ኃይል ዳግም ከሞከረ የማያዳግም ቅጣት ይጠብቀዋልʺ
ሻዕቢያና ትህነግ - ሰሞኑን ይህ ሆነ
ትህነግ ጦርነት እንደሚከፍት ይፋ አደረገ፤ አማራ ክልል "ለክተት ተዘጋጁ"አለ፤ መከላከያ በተጠንቀቅ ላይ ነው
ወልቃይት "የወር ስንቅህን አዘጋጅተህ ለክትተ ጥሪ ተዘጋጅ”
በሶማሊያ በሚንቀሳቀሰው አልሸባብ የሽብር ተልዕኮ የተሰጣቸው ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አማራ ክልል ትህነግ ዳግም ጦርነት ስላወጀ የ"ዝግጁነትን" አዋጅ አወጣ
ኡጋንዳ ፀረ-ኢትዮጵያ ለሆኑ ሃይሎች ከለላና ድጋፍ እንደማታደርግ አስታወቀች፤ የሚወራው ሃሰት ነው አለች
በአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገ
በዳኝነት ስርአቱ ላይ የሚታዩ የሙስና ተግባራትን ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

Leave a Reply