መሀል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል!!

ካርቱም ከግድቡ ድርድር መታገድና የህብረቱ ሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት | ቅኝት
እስሌማን ዓባይ – የዓባይ ልጅ

ሱዳን ከአፍሪካ ህብረት ሁሉም ተሳትፎዎቿ በመታገዷ በግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር አትሳተፍም። በሱዳን የሽግግር ሂደቱን ይመራ የነበረው የሲቪል አስተዳደር ወደ ቦታው እስከሚመለስ ድረስ ሱዳን ከአባልነት ታግዳ እንደምትቆይ ተገልጿል። እገዳው በሁሉም የህብረቱ እንቅስቃሴዎች ላይ የተጣለባት ሲሆን በህብረቱ የሚመራውን የግድቡ ድርድር ሂደትን እንደሚያካትትም አል-አይን የህብረቱ ምንጮች ነገሩኝ በማለት ዘግቧል። ሱዳን በአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር-ቤት ፕሮቶኮል አንቀጽ 7 መሠረት ነው ከአባልነት የታገደችው።

°የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት
”በአባል አገራት መካከል ጣልቃ አለመግባት” የቀደመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መርህ ነበር። ይሁንና በአህጉረ አፍሪካ ተደጋግመው ሲከሰቱ ለሚታዩት ጥሰቶች አስፈላጊውን፣ ሁሉን አቀፍና የተቀናጀ መፍትሄ ሊሰጥ አለመቻሉን ከግምት ያስገባ ምክክር እንዲደረግ ሆኗል። አፍሪካ አንድነት ድርጅትም በአፍሪካ ህብረት ተተክቶ 2002እኤአ ላይ የምረቃ ጉባዔውን አካሄደ።

በ1990ዎቹ በአፍሪካ የተከሰቱት ግጭቶች በተለይም በሩዋንዳ የተከሰተው የዘር ማጥፋት ግጭት የአፍሪካ አገራት ጣልቃ ያለመግባት አካሄዳቸውን ትተው የተባበረና የጋራ የደህንነት ኃይል ማቋቋም እንዳለባቸው ያስገነዘበ ነበር።
ለዚህም የድርጅቱን ጣልቃ ያለ መግባት መርህ ቀይሮ በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት መተዳደሪያ ደንብ ”በህብረቱ አገሮች ውስጥ የጦር ወንጀል ሲፈፀም፣ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሲካሄድ፣ የሰባዓዊ መብት ጥሰት ሲኖርና የመሳሰሉት ተግባራት ሲፈጸሙ ጣልቃ እንደሚገባ በደንቡ አንቀጽ 2 እና 4 ላይ ደነገገ።

ይህን ለማሰፈጸም ያስችለው ዘንድ በ2002 በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ በተካሄደው የህብረቱ የምረቃ ጉባዔ ላይ አባል አገራቱ በአጽንኦት ትኩረት ከሰጡት ጉዳይ መካከል የአፍሪካ አገራት የጋራ መከላከያና የፀጥታ ስርዓት ዝርጋታ አንዱ ነበር። በአህጉሩ የሚነሱ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች የተቀናጀና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል የህብረቱ የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ፕሮቶኮል በህብረቱ መሪዎች ተቀባይነት አገኘ።

ይህ ፕሮቶኮል በይዘቱ የአፍሪካን የሰላምና ፀጥታ መዋቅር ( African peace and security Architecture) የሚዘረጋ ሲሆን በዋናነት ግጭትን ለመከላከል፣ ስለ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ፣ ጣልቃ ስለ መግባት፣ ስለ ሰብዓዊ እርምጃዎች እና አደጋን ስለ መከላከል የሚሉትን ያቀፈ ነው።

See also  የተከበበው የትህነግ ሃይል ሙሉ በሙሉ ተደመሰሰ፤ ማንነት የመለየት ስራ እየተሰራ ነው

ህብረቱ በ2003 በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ ባቀረበው ሪፓርት ላይ አህጉሩን በአምስት ቀጣና ከፍሎ ቀጠናዎቹ የራሳቸውን ተጠባባቂ የጦር ኃይል እንዲያቋቁሙ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ አዘጋጅቶ አቀረበ።

እነዚህ በአምስቱ ቀጠናዎች የሚቋቋሙት ተጠባባቂ የጦር ኃይሎች የሰሜን አፍሪካ (NASBRIG)፣ የምስራቅ አፍሪካ (EASBRIG)፣ የመካከለኛው አፍሪካ (FOMAC)፣ የደቡብ አፍሪካ (SADCBRIG) እና የምዕራብ አፍሪካ (ECOWAS) ሲሆኑ በዚህ አጭር ትንታኔ ውስጥ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል (EASBRIG)፣

የምስራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ብርጌድ አባል አገራት ቡሩንዲ፣ ኮሞሮስ፣ ጂቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሲሸልስ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ ሲሆኑ ብርጌዱ የአፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል አካል ሆኖ እንዲቋቋም እ.አ.አ በ2004 በአዲስ አበባ በተካሄደው የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ውሳኔ ተላልፏል። የመግባቢያ ሰነዱም በ2011 ተሻሽሎና ተፈርሞ ብርጌዱ ተቋቁሟል። በ2007 የቀጠናው የመከላከያና የፀጥታ ሚኒስትሮች ባስተላለፉት ውሳኔ ስያሜው ከብርጌድ ወደ ኃይል እንዲቀየርም ተደርጓል።

በ2014 በኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ከተማ ማላቦ የክፍለ አህጉሩ መሪዎች ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ ኃይሉ የተቋቋመበትን የመግባቢያ ሰነድ ወደ ስምምነት ለማሳደግና ለማሻሻል የቀረበውን ሃሳብ ተቀብሎ አባል አገራቱ እንዲያጸደቁት ጠይቋል። የስምምነት ሰነዱ የምስራቅ አፍሪካን የተጠንቀቅ ኃይል ስለመቋቋሙ፣ ስለ ተግባሩና ዓላማው፣ በውስጡ ስለሚይዛቸው አካላትና ተግባራቸው እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዙ 27 አንቀጾችን ይዟል።

አገሮቹ ስምምነቱን ማድረግ ያስፈለጋቸው በዋናነት ክልላዊ ሰላምን፣ ፀጥታንና መረጋጋትን ለማስፈን የሚተላለፉትን ውሳኔዎችን በብቃት ለመወጣት የሚያስችላቸውን ተቋማዊ አሰራር እንዲሁም የእርስ በእርስ፣ በአገራት መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመፍታት የሚያስችል አሰራር ለመፍጠር ነው።

የተጠንቀቅ ኃይሉ በህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ፍቃድ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ግዳጁን በሚመለከት ውሳኔ የሚሰጠው የህብረቱ የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ነው።

በስምምነቱ መሰረት የመሪዎች ጉባዔ፣ የመከላከያና የፀጥታ ሚኒስትሮች ምክር ቤትና የመከላከያ ዋና ሹሞች የተጠንቀቅ ኃይሉ የፖሊሲ አካላት ሲሆኑ የመሪዎች ጉባዔ የህብረቱ አባል አገሮች ርዕሳነ ብሔሮችና ርዕሰ መንግስታት ሆነው የኃይሉን ፖሊሲ ማውጣት፣ መምራት፣ መቆጣጠር፣ ከአገራት የሚቀርቡ የአባልነት ጥያቄ መቀበልና መወሰን፣ ለኃይሉ የሚያስፈልጉ ተቋማትን መፍጠር፣ የስምሪት ፍቃድና ሹመት መስጠት የሚሉትን ተግባራት ያከናውናሉ። የተጠንቀቅ ኃይሉ ዋና ማዕከልና የአቅርቦት ክፍሉ መቀመጫው በአዲስ አበባ ይገኛል።

See also  "አሸባሪው ሃይል በጋራ ክንድ እየተነቀለ ነው" ተመስገን ጥሩነህ

የዓባይ ልጅ – እስሌማን ዓባይ

Leave a Reply