በሰሜን ወሎ ዞን በአሸባሪው ህወሓት 832 ትምህርት ቤቶች ወድመዋል

አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን ለወራት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በፈጸመው ወረራ እና ምዝበራ በሰሜን ወሎ ዞን ብቻ 832 ትምህርት ቤቶች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ በዞኑ በፈጠረው ዘርፈ ብዙ ችግር በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ከ330 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ለመሆን ተገደዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ በአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጋዜጠኞች ቡድን ተገኝቶ ሽብርተኛው ትህነግ ያደረሰውን ጉዳት ተመልክቷል፡፡ በትምህርት ቤቱ የተማሪ መማሪያ ክፍሎች በጥይት ተበሳስተዋል፤ የመማሪያ ክፍሎች መጸዳጃ ሆነዋል፤ ወንበሮች ተፈልጠው ተማግደዋል፤ ጥቁር ሰሌዳ ተሰባብሮ መኝታ ሆኗል፤ የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት እና መረጃ ወድሟል፡፡

የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በመማሪያ ክፍሎች ላይ የሕፃናትን አዕምሮ የሚጎዱ የጥላቻ ጽሑፎችን ጽፏል፡፡

በመቄት ወረዳ 80 የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል እና አምስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ዋጋው መንበር ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ከ44 ሺህ በላይ ተማሪዎች አሉ፡፡ አቶ ዋጋው እንደተናገሩት የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በ19 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 580 ኮምፒውተሮችን እና 60 ፕላዝማዎችን ዘርፏል፤ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የተለያየ ዓይነት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

እስካሁን የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ተደምስሶ ነፃ በወጡ 28 ቀበሌዎች 60 ትምህርት ቤቶች በደረሰባቸው ጉዳት የመማር ማስተማር ሥራውን መጀመር አልቻሉም፡፡

የአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በወረራቸው ሁሉም የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች 832 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ዘረፋ እና ውድመት ደርሶባቸዋል ያሉት ደግሞ የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኅላፊ አቶ ሰጠ ታደሰ ናቸው፡፡ በ2014 የትምህርት ዘመን መማር የነበረባቸው 330 ሺህ 638 ተማሪዎች እስካሁንም ከትምህርት እድል ውጭ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሥራ በባህሪው በእቅድ እና ቅደም ተከተል የሚመራ ነው ያሉት ምክትል መምሪያ ኅላፊው ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሃብትና ንብረታቸው በመዘረፉ እና ሽብርተኛው ትህነግ የጦር ካምፕ አድርጓቸው ስለነበር መማር ማስተማሩን በቅርብ ለመጀመር ፈታኝ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

ምክትል መምሪያ ኅላፊው እንደገለጹት ሽብርተኛው ትህነግ በፈጠረው መጠነ ሰፊ ማኅበራዊ ቀውስ አርሶ አደሮች በክረምቱ የእርሻ ወቅት በሚገባ ሥራቸውን ማከናወን አልቻሉም ነበር፤ ማኅበረሰቡ በጭንቅ ውስጥም ሆኖ ያረሰውን የተወሰነ ሰብል የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ሰለጨፈጨፉበት እና ስለዘረፉበት በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል ከ265 ሺህ በላይ የሚሆኑት የትምህርት ቤት ምገባ ያስፈልጋቸዋል፡፡

የሽብርተኛው ትህነግን ወራሪ ቡድንን በተባበረ ክንድ በመደምሰስ አካባቢውን በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው አለመሆኑን አቶ ሰጠ ገልጸዋል፡፡
የባከነውን የትምህርት ጊዜ በሚያካክስ መልኩ ወደ ሥራ ለመግባትም መንግሥት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ተቋማት እና ሕዝቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

(አሚኮ)

You may also like...

Leave a Reply