እስከአሁን ህዝብ እያሸበሩ፣ በሰው ማዕበል ከተማ በማስለቀቅ ያለ ጥይት ተኩስ ሰተት ብሎ እየገቡ መዝረፍና መግደል የህወሀት ስትራቴጂ ሆኖ ቆይቷል። ደሴ ላይ አልሰራም። በመከላከያ ሰራዊት መሪነት፣ በአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሺያ እንዲሁም በፋኖ ብርቱ ክንድ የህወሀት ጀሌ መዓት እየወረደበት ነው። አሁን ለህወሀት ሃይል ፍቱን የሆነው መድሃኒት በሚገባ እየተሰጠው ነው። ጀግኖቹ ገጥመዋል። የሚደርሱኝ የፎቶግራፍ ምስሎች ስሜትን የሚሰቅዙ ቢሆንም የህወሀት ወራሪ ሃይል እንደ ቅጠል እየረገፈ ለመሆኑ ማሳያ ናቸው። ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ የህወሀት ወራሪ ሃይል ላይ የደረሰው ዕልቂት የጦርነቱን ማርሽ ቀይሮታል። የድል በር ለኢትዮጵያውያን ሃይሎች ወለል ብሎ ተከፍቷል። ህወሀትን በመረጠው የውጊያ ስትራቴጂ በመግጠም ለደም ግብሩ ያሰለፈውን ጀሌ እንደ ቅጠል እያረገፉት ያሉት የኢትዮጵያ ሃይሎች የዚህን የክፋት ቡድን የጥፋት ሩጫ ደሴ አፋፍ ላይ በአስደናቂና ልብ በሚያሞቅ ጀግንነት አስቁመውታል።

በእርግጥ እየሆነ ያለው ያሳዝናል። ለህወሀት የእብደት ጦርነት የትግራይ ወጣቶች በገፍ እያለቁ ነው። የህወሀት መሪዎች ቆመንለታል እያሉ ሌት ተቀን ለሚምሉለት የትግራይ ህዝብ የሚራራ አንጀት በፍጹም እንደሌላቸው የደሴ ዙሪያው የሰሞኑ እልቂት ተጨማሪ ምስክር ሆኖ ቀርቧል። የትግራይ ኢሊቶችም የወጣቶች መርገፍ፣ የእናቶች ደም የወሎን ምድር ማጠብ ጉዳያቸው አላደረጉትም። የትግራይ ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ዝምታቸው በብርቱ ያስፈራል። ሀይ ባይ ያጣ፣ መክሮ፣ ገስጾና ለምኖም ቢሆን ህወህቶችን ከጥፋት ግስጋሴአቸው የሚመልሳቸው አካል አለመኖሩ መጪውን ጊዜ በድቅድቅ ጨለማ የተዋጠ እንዲሆን አድርጎታል። እነአሜሪካም ኢትዮጵያ ምድር ላይ እየሆነ ያለውን አሰቃቂ ትዕይንት የሆሊውድ ፊልም ይመስል በትራጄዲው ተመስጠው ለህወሀት እብደት በጭፍን የሚሰጡትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸውን በግልጽ እየታዘብን ነው።

ስለአሜሪካንና ሸሪኮቿ ከሰሞኑ የሰማሁት አሳዛኝም ፣አስደንጋጭም ነው። አሜሪካ ለህወሀት የሳተላይት መረጃ በማቅረብ በጦርነቱ አሸናፊ እንዲሆን አይኗን ጨፍና እያገዘች መሆኗን ሰምቼ ለማጣራት የጠየኳቸው የፌደራል መንግስቱ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን የመረጃውን ትክክለኛነት ካረጋገጡልኝ በኋላ “የሚገርመው….” አሉ ባለስልጣኑ። ጆሮዬን ተክዬ መስማቴን ቀጠልኩ። ” የሚገርመው አሜሪካን ህወሀት በጦርነቱ አሸንፏል ብላ ታምናለች። መንግስት ላይ ጫና የምትፈጥረውም ከዚህ እምነቷ ተነስታ ነው። ህወሀት እንዲያሸንፍ መመኘት አንድ ነገር ነው። እናንተ ተሸንፋችኋልና ህወሀትን ስልጣን አጋሩት፣ የሚል ግትር አቋም እያራመደች ናት።” በእውነቱ የአሜሪካን ነገር ግራ የሚያጋባ ነው።

ጌታቸው ረዳ ምላሱን አዳልጦት በሚመስል መልኩ አንድ የመንግስታቱ ድርጅት የስራ ሃላፊ በሚስጢር የነገሩትን በአደባባይ ዘርግፎታል። ሃላፊው ህወሀት እያሸነፈ ነው የሚል አቋም እንዳላቸው ለጌታቸው ሹክ እንዳሉት ነው የነገረን። ህወሀት ድል እያደረገ እንደሆነ በየጊዜው ቢገልጽም እነአሜሪካና UN ሰዎች በሚያምኑት ደረጃ አሸንፌአለሁ በሚል አፍ ሞልቶ የተናገረ አይመስለኝም። የእነአሜሪካ እንዲህ ዓይነት አካሄድ ምን ለመፍጠር እንደሆነ ለመግለጽ የሚከብድ ነው። በጣዕረ ሞት ላይ ያለን የህወሀት ሃይል እያሸነፈ ነው ብሎ በጭፍን ማመን ለዕልቂቱ ደንታ እንደሌላቸው፣ ህዝብ እንደ ቅጠል ቢረግፍ ምንም ስሜት እንደማይሰጣቸው የሚያረጋግጥ ነው።

ህወሀት ወደፊቱ ዳገት ሆኖበታል። ወደኋላም ቢሆን እሳት እንጂ ሌላ ነገር እንደሌለ አውቆታል። ደሴን አይረግጣትም። ኮምቦልቻን በህልሙም አይደርሳትም። ጨዋታው ተቀይሯል። ደሴ ዙሪያ የገጠመውን የኢትዮጵያ ሃይል መስበር ሲሳነው የተራረፈና የተበታተነ ሃይሉን ለሽብር ተግባር እያሰማራ ይገኛል። ትላንት ሀሙስ የጦር አመራሮቹ በራዲዮ መልዕክት ሲለዋወጡ ከተጠለፈው ንግግራቸው መረዳት እንደተቻለው ወደፊት መግፋት የማይታሰብ እንደሆነ አብዛኞቹ አምነዋል። የተወሰኑት ያለቀው ይለቅና ደሴን መያዝ አለብን የሚል ሀሳብ ቢያቀርቡም ተስፋ የሌለው መሆኑን፣ ሃይላቸውና መሳሪያቸው በመመናመኑ ወደ ደሴ የመግፋት እድሉ ፈጽሞ መዘጋቱን፣ ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ በመጥቀስ የስትራቴጂ ለውጥ እንዲደረግ ይወተውታሉ። የመከላከያ አንድ ከፍተኛ አዛዥ እንዳሉኝ የተጠለፈው የሬዲዮ መልዕክት ልውውጥ ህወሀት በጦርነቱ ተስፋ መቁረጡንና እንደማያሸንፍ ማረጋገጡን የሚያሳይ ቢሆንም ወደለየለት የሽብር ተግባር በመግባት ሰላማዊ ዜጎችና መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት በመፈጸም መረበሹንና ማሸበሩን በስፋት መፈጸሙ የማይቀር ነው። የስትራቴጂ ለውጥ ይደረግ እያሉ የሚመካከሩትም ይህንን የሽብር ተግባር ለመፈጸም እንደሆነ የመከላከያው አዛዥ እርግጠኛ ሆነው ገልጸውልኛል። እናም መንግስትና ህዝብ ሁኔታውን ተረድተው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው ስጋት ባጠላው ድምጸት የነገሩኝ።

በእርግጥም የአዛዡ ስጋት ልክ ነው። ህወሀቶች የጦርነቱ ነገር እንዳልሆነላቸው ሲረዱ የሽብር ተግባሩን ከወዲሁ ጀምረውታል። የመብራት ማከፋፊያ ጣቢያን መምታታቸውን ከመሸ ሰምቼአለሁ። በፕሮፖጋንዳው ሳይበገር ከተማዋን ላለማስነካት ሆ ብሎ የተነሳውን የደሴን ነዋሪ በሰርጎ ገቦች አማካኝነት ለመበጥበጥ ሙከራ እያደረገ እንደሆነም ይነገራል። ደሴ ዙሪያ በተለያዩ አቅጣጫዎች ከቅርብ ርቀት መሳሪያዎችን እየተኮሰ ነዋሪው እንዳይረጋጋና ከተማዋን ለቆ እንዲሰደድ ለማድረግ እየተፍጨረጨረ እንዳለም ከአከባቢው ከሚወጡ መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል። ምናልባትም እነአሜሪካንን ላለማሳፈር በየቦታው የተበታተኑቱን ጀሌዎቹን ለቃቅሞ የመጨረሻውን የማጥቃት ሙከራ ከማድረግ እንደማይመለስም ጥርጣሬአቸውን ያጋሩኝ ወገኖችም አሉ። ህወሀትን አውቀነዋል። መቃብሩ እስኪገባ ድረስ ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ የሚል አይደለም። በሽብር ተግባሩም ሆነ በፊት ለፊት ግጥሚያው በጥንቃቄና በፍጹም ሀገራዊ ወኔ ተዘጋጅቶ መጠበቅ የወቅቱ የህልውና ጉዳይ ነው።

ህወሀት በቁሙ ተስካሩን እየበላ ነው። የእነአሜሪካን የሳተላይት መረጃ ድጋፍ ለድል አላበቃውም። የምዕራብ ሀገራትና ተቋማት አይን ያወጣ እገዛ የሰው ሃይሉን ከዕልቂት አላዳነውም። ያም ቢሆን ለተወሰኑ ጊዜያት የጎን ውጋት እየሆነ መቀጠሉ አይቀርም። የመጨረሻ እስትንፋሱ እስክትቋረጥ መረበሹን አያቆምም። አፉን ከፍቶ ከሚጠብቀው ዘላለማዊ መቃብሩ እስኪገባ ድረስም የኢትዮጵያውያን የተስፋ መንገድ ላይ እንቅፋት እየሆነ መደንቀሩ የማይቀር ነው። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በጽናት፣ በቁርጠኝነት፣ በመናበብ፣ በፍጹም ሀገራዊ አንድነት ይህን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ለመሻገር ከወሰንን እግሩ ተቆርጦ፣ እንደእባብ እየዳኸ ያለውን የህወሀት ሃይል አናቱን በመቀጥቀጥ ከነነቀርሳው እስከወዲያኛው መሸኘትና ለዘመናት የተጣቡንን ተውሳኮችና በሽታዎች ተገላግለን ጠንካራዋንና ገናናዋን ሀገራችንን ከእጃችን ማስገባት እንችላለን። የኢትዮጵያ ትንሳዔ በህወሀት መቃብር ላይ እውን መሆኑ ከፊታችን የሚታይ ግዙፍ እውነት ነው። እድሜ ሰጥቶን ለማየት ያብቃን!

መሳይ መኮንን


Leave a Reply