የመረረውን ትግል ታግለን፣ ጣፋጩን ድል እናጣጥማለን።

የሽብር ቡድኑ ሕወሓት፣ ያሳደገች እናቱ ላይ የመከራ ቋጥኝ እንደሚጭን ክፉ ልጅ፣ አሁንም ለኢትዮጵያ የመከራ ቋት መሆኑን ቀጥሏል። በጥላቻ ፕሮፓጋንዳው አነሳስቶ የሰበሰባቸውን ኃይሎች ይዞ በአራት ግንባሮች ተኩስ ከፍቶ ሀገር የማፍረስ ተግባሩን ገፍቶበታል። መከላከያ ሠራዊታችና የእናት ሀገር ጥቃት ግድ የሚለው የወገን ጦር በአንድነት ሆነው ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ጥቃት ለመመከት በሁሉም ግንባሮች ተሰልፏል። ጠላት የመጨረሻ አቅሙን አሟጥጦ ለማጥቃት የሚያደርገውን ጥረት ሠራዊታችን በምድርና በአየር እየታገዘ እንዳይነሳ አድርጎ እየሰበረው ይገኛል።

በሦስቱ ግንባሮች እንደማያዋጣው የተገነዘበው አሸባሪው ሕወሐት፣ ሰሞኑን ያለ የሌለ ኃይሉን ወደ ወሎ ግንባር አምጥቷል። ለበቀለበት ሕዝብ ጨምሮ ለማንም ርህራሄ የሌለው ቡድኑ በዘመቻው ከ12 ዓመት ሕጻን እስከ 65 ዓመት አዛውንት ያገኘውን ሁሉ ሰብስቦ አዝምቷል። ይኼን ሲያደርግ ዓላማው ሁለት ነው። አንድም ያሰማራው ኃይል ጨርሶ ተስፋ እንዳይቆርጥና ሞራሉ እንዲያንሰራራ ለማድረግ በወሎ በኩል ድል የማግኘት ምኞት አድሮበታል። ሁለትም በቅርቡ አየር ኃይላችን ጥቃት ሰንዝሮ ያወደመበትን ከባድ መሣሪያ ከመከላከያ ሠራዊት ማርኮ ለመተካት በማሰብ የሞት ሽረት ትግል አድርጓል። ለድል ቋምጦ መጥቶ ጠላት በወሎው ግንባር ሰፊ ቁጥር ያለው ኃይሉን ያጣ ሲሆን፣ ጀግናው ሠራዊታችን በሁሉም መስክ መሥዋዕትነትን ከፍሎ እየተጋደለ ነው።

በቀጣይ ጊዜያትም ጠላት የተረፈውን ኃይል አሰባስቦ ተመሳሳይ ጥቃቶችን መሠንዘሩ አይቀርም። የጠላት የጥንካሬ ምንጭ የእኛ ድክመትና መዘናጋት እንደሆነ አውቀን ነቅተንና ተባብረን ልንጠብቀው ይገባል። ብዛታችን ጥንካሬ የሚሆነው ተግባብተን በአንድነት ስንቆም ነው። መነጣጠላችን ለጠላት ይመቻል። በሚነዛው ፕሮፓጋንዳ መረበሻችን እሱን ካልሆነ በቀር ማንንም አይጠቅምም። እርስ በእርሳችን መደማመጥና መተባበር ከቻልን መፍረክረክ የጀመረ የጠላት ጉልበት ይንበረከካል፤ እንደ ክር የሰለለ ምኞቱም ይጨነግፋል። ሀገር ለማጥፋት የመጣ መንጋ ሀገር ለማዳን የተነሣን ኃይል ይረብሸው ይሆናል፣ ሊያሸንፈው ግን አይችልም።

ሥራችንን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ ከማከናወን ባለፈ፣ በመካከላችን ሆኖ ለጠላት የሚሠራውን የሕወሐት ወኪል በንቃት መከታተል ያስፈልጋል። ለዘመናት ከጠላት ጋር የጥቅም ትስስር የፈጠሩ ሰዎች ዛሬም በጉያችን ሆነው የጠላትን ምኞት ከዳር ለማድረስ ደፋ ቀና ይላሉ። ስለዚህ ሁሉም ዜጋ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የጠላት ወኪሎችን ማጋለጥ ይገባል።

በሚገጥመን ፈተና ሳንረበሽ ሁላችንም የበኩላችንን ሚና ከተጫወትን ፈተናችን የሚወገድበት ጊዜው ሩቅ አይሆንም። በተቃራኒው ተግባሩን ትተን የምንጠይቅ ብቻ ከሆንን የድላችን እድሜ ይዘገያል። ሀገርን ከጥቃት የመከላከል ኃላፊነት የጥቂቶች ሳይሆን የሁላችንም ነው። እያንዳንዱ ዜጋ ከእኔ ምን ይጠበቃል? እኔ ምን እያደረኩ ነው? ማለት አለበት። የእሱ ደህንነት እንዲጠበቅ፣ እሱ ሰላም ውሎ እንዲያደር፣ ሠርቶ እንዲያተርፍ ለእሱ ሲሉ ሌሎች የሚሰውበት ምክንያት የለም። ሁሉም ከወዙ ጨልፎ፣ ከደሙ ቀንሶና ከአጥንቱ ፈልጦ በሚያተበረክተው አስተዋጽኦ ነው ሀገር ነፍስ ኖሯት፣ በሁለት እግሯ የምትቆመው። ለኢትዮጵያ የመሞት ግዴታ የሁላችንም እንጂ፣ የተለየ ሞት እንዲሞት የሚጠበቅበት የተለየ አካል የለም።

ስለዚህ ሕዝባችን የክት ጉዳዩን ለጊዜው አቆይቶ፣ ለማጥፋት የመጣውን አሸባሪውን ሕወሓት ለመመከት፣ ለመቀልበስና ለመቅበር ማናቸውንም መሣሪያና ዐቅም ይዞ፣ በሕጋዊ አደረጃጀት መዝመት አለበት። ይህ ታላቅ ሕዝብ ታላላቅ ታሪካዊ ፈተናዎችን ድል የነሳው ዳር ቆሞ በማየት ወይም በጥቂት ድል ረክቶ በመቀመጥ አይደለም። የተሰነዘሩብንን ጥቃቶች ያሸነፍነው በአንድነት ለሀገራችን ጸንተን ዘብ በመቆም ነው።

የቀደምት አያቶቻችንን የጀግንነት ፈለግ በመከተል ማንኛውንም እኩይ ተግባር ማክሸፍ እንደምንችል ማመን አለብን። አሁን የገጠሙን ፈተናዎች የማይታለፉ እና ውስብስብ ሊመስሉ ይችላሉ። ነገር ግን ቀደምቶቻችን ካዩት መከራ የሚከብዱ አይደሉም። ቁልፉ ጉዳይ በአንድነት መቆም፣ በጥሞና መደማመጥ እና ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ ናቸው። ይኼን ካደረግን የቀደመው ትውልድ ሀገርን ጠብቆ ወደ እኛ ማስተላለፍ እንደቻለው፣ እኛም ኢትዮጵያን አስከብረን ለቀጣዩ ትውልድ እናወርሳለን። ጫጫታና ማወናበዱ ቢበረታም ዛሬን በትኩረት እንድንቆም፣ ያለ አንዳች ማመንታት ኢትዮጵያን በአንድነት ከጥቃት እንድንከላከላት ጥሪዬን አቀርባለሁ።

Abiy Ahemed Ali pm

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

Related posts:

«ሕወሓት ጦርነትን እንደ አምልኮ የሚቆጥር ቡድን ነው» – ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ
«በሕገወጦች ላይ ያለ ምኅረት እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ይህ የመንግሥት ተግባር ነው» የአማራ ክልል
125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ
«በአገሩ መከላከያ ላይ አፉን የሚከፍት ሕዝብ የለም፤ መንግስትም አይታገስም» ክብር ለመከላከያ ሰራዊት!!
በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል የተደረገውን የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት ምክር ቤቱ አጸደቀ
የሞት ፍርደኛው የ25 ዓመታት ሰቆቃ! ከመሬት በታች የታፈኑት አባት
«ኢትዮዽያን ማስቀጠል ከሚፈልጉት ጎን በመሆናችን የሚከፋ ከአለ እርሱ መፍረሷን የሚናፍቅ ብቻ ነው!»
ደብዳቤ ለኢትዮጵያ - ከቢልለኔ ስዩም
የዓለም ባንክ የ300 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ፈረመ
"እናቴ ፍጹም እስር ቤት እንድትገባ አልፈግም" ብሎ እግሩን ያጣው ወጣት ምስክርነት ለሮይተርስ
"አልዘምትም" ወይም "ከጠላት ጎን እሰለፋለሁ" ማለት ሲቻል ማውሰብሰብና ማድበስበስ አይገባም!
አብዱላሂ ፋርማጆ ለአዲሱን ፕሬዝዳንት «ሁሉም ወገኖቼ እንዲደግፉህና እንዲጸልዩልህም እጠይቃለሁ»
መንግስ የጸጥታ ሃይሎች ለየትኛውም ዓይነት ትንኮሳ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ማድረጉን አስታወቀ
በትግራይ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ እየደረሰ ነው፤ ከሺህ በላይ የጭነት መኪኖች ታግተዋል፤ 76 ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ተልኳል
የደህንነት ጥናት አዲሱ ምዕራፍ - ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ

Leave a Reply