የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አማጺው ቡድን በኮምቦልቻ ከተማ ከ100 በላይ ወጣቶችን ገድሏል ማለቱን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገበ። 

“ህወሓት በኮምቦልቻ ከተማ ሰርጎ በመግባት ዛሬ ሌሊቱን ከ100 በላይ የከተማዋን ወጣቶችን አሰልፎ ጨፍጭፏል” ሲል ኢቢሲ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ጠቅሶ ዘግቧል።

ሚንስትሩ ህወሓት “ሰርጎ በገባባቸው” ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች የግል እና የመንግሥት ሃብቶችን እየዘረፈ እና እያወደመ ነው ስለማለታቸው ተዘግቧል። 

በኢቢሲ ዘገባ ላይ ሚንስትሩ ህወሓት ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች “ሰርጎ ገብቷል” ከማለታቸው ውጪ ሁለቱ ከተሞች በየትኛው አካል ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ አልተገለጸም። 

በዚህም ሁለቱ የደቡብ ወሎ ከተሞች ደሴ እና ኮምቦልቻ እስካሁን በየትኛው አካል ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ በግልጽ ማወቅ አልተቻለም። 

ባለፈው ሳምንት ለቀናት ሲካሄድ የነበረው ውጊያ የህወሓት ኃይሎች ደሴን ለመያዝ የፌደራሉ ሠራዊትና አጋሮቹ ደግሞ ከተማዋን ለመከላከል ሲያደርጉት የቆየ ነው። 

በዚህም ከባድ መሳሪያ ወደ ከተማዋ በተደጋጋሚ መተኮሱንና በነዋሪዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን የከተማዋ ባለሥልጣናትና ነዋሪዎች ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ለቀናት ሲካሄድ የነበረው ከተማዋን ለመከላከልና በቁጥጥር ስር ለማስገባት በተደረገው ውጊያ በሳምንቱ ማብቂያ ላይም ቀጥሎ ቅዳሜ ዕለት በደሴ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ተኩስ መሰማቱንና የአማጺያኑ ተዋጊዎች መታየታቸውን ነዋሪዎች ለተለያዩ የዜና ወኪሎች ገልጸዋል። 

አርብ አመሻሽ ላይ በአንዳንድ የደሴ ከተማ አካባቢዎች ላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ የተነገረ ሲሆን ከቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ደግሞ በደሴ ከተማ የስልክ ግንኙነት በመቋረጡ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። 

ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ ከደሴ ከተማ ውጪ ባሉ የደቡብ ወሎ አካባቢዎች ውጊያ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ጦርነቱ ወደ ከተማዋ ተቃርቦ ቆይቷል።

በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ትላልቅ ከተሞች አንዷ የሆነችው ተራራማዋ የደሴ ከተማ ጦርነቱ ሲስፋፋ ከሰሜን ወሎ የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎችን በተፈናቃይነት አስጠልላ መቆየቷ ይታወሳል። 

ባለፈው ሳምንት አማጺያኑ ወደ ከተማዋ መቃረባቸው ሲነገር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ኃይል እንዲሁም ከተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ሚሊሻዎችና ኢመደበኛ የሆኑ ታጣቂዎች ሲሰማሩ መቆየታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ ነበር።

ቅዳሜ ረፋድ ላይ በከተማዋ የነበረው እንቅስቃሴን በተመለከተ ቢቢሲን ጨምሮ ለተለያዩ የዜና ምንጮች ነዋሪዎች እንደገለጹት በከተማዋ ዙሪያ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማና እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን ገልጸው ነበር።

የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በዚያኑ ዕለት የመንግሥት ወታደሮች ከከተማዋ እያፈገፈጉ መሆናቸውን ሲዘግብ ሮይተርስ የዜና ወኪል ደግሞ የአማጺያኑን ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳን ጠቅሶ ከተማዋ በህወሓት ኃይሎች እጅ መግባቷን ዘግቦ ነበር። 

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የአገሪቱ ሠራዊት የፀረ ማጥቃት እርምጃ በመውሰድ በደሴ ከተማ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት መክቶ “ደሴን ለመያዝ አሰፍስፎ የመጣውን ወራሪ ኃይል በመመከት” ከተማዋ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንዳለች ገልጾ ነበር።

ህወሓት በበኩሉ በደሴ በኩል በተካሄደው ውጊያ የበላይነት ይዞ ከተማዋን ከመቆጣጠሩ ባሻገር ከደሴ ከ20 ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኘውን የኢንዱስትሪ ከተማዋን ኮምቦልቻን ተዋጊዎቻቸው መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል። 

እነዚህ የደቡብ ወሎ ዞን ዋነኛ ከተሞችን በተመለከተ በመንግሥት በኩል የተሰጠ ግልጽ ማብራሪያ ባይኖርም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ ከአማጺያኑ ጋር የሚደረገው “ከባድ ውጊያ” እንደቀጠለ አመልክቷል። 

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ሰኞ ረፋድ ላይ በትዊተር ገጻቸው ላይ አገራቸው እየወጡ ባሉ “ህወሓት ደሴንና ኮምቦልቻን መያዙን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች” እንዳሳሰባት ገልጸዋል።

ጨምረውም የቀጠለው ውጊያ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ የሚያራዝመው በመሆኑ፣ ሁሉም ወገኖች ወታደራዊ ዘመቻቸውን አቁመው ካለቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ድርድር መጀመር አለባቸው ብለዋል። 

መረጃ 

እነዚህ ከተሞች አሁን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ከአማጺው ወገን ከሚሰጠው መረጃ እና በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ከሚባለው ውጪ የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ አስተማማኝ መረጃ ከነዋሪዎች ማግኘት አልተቻለም።

ከመንግሥት በኩልም ቢሆን ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ከመሆኑ ውጪ ከተሞቹ ያሉበትን ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ ማግኘት አዳጋች ሆኗል።

ከዚህ ውጪ በወሎ ግንባር እየተካሄደ ያለውን ከባድ ውጊያ ተከትሎ የአማራ ክልል መንግሥት ሁሉም መዋቅር እንዲሁም አቅሙ ያለው ነዋሪ “የህልውና” ያለውን ዘመቻ እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ጦርነቱን አስመልክተው እሁድ ምሽት ባስተላለፉት መልዕክት የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት “በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ጥቃት ለመመከት በሁሉም ግንባሮች ተሰልፏል” በማለት “ሠራዊቱ በምድርና በአየር እየታገዘ እንዳይነሳ አድርጎ እየሰበረው ይገኛል” ብለዋል።

ጨምረውም አማጺው ያለውን ኃይል በሙሉ አሰባስቦ በወሎ ግንባር በኩል መሰለፉንና “ሰፊ ቁጥር ያለው ኃይሉን ያጣ ሲሆን፣ ጀግናው ሠራዊታችን በሁሉም መስክ መስዋዕትነትን ከፍሎ እየተጋደለ ነው” ሲሉ ውጊያው መቀጠሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም በዘመቻው እንዲሳተፍ ጥሪ ባቀረቡበት በዚህ መልዕክታቸው “ሕዝባችን የክት ጉዳዩን ለጊዜው አቆይቶ. . . ማናቸውንም መሣሪያና አቅም ይዞ፣ በሕጋዊ አደረጃጀት መዝመት አለበት” ሲሉ ሁሉም በሚችለው ሁሉ የበኩሉን እንዲያበረክት ጠይቀዋል። 

ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ወራትን ባስቆጠረበት ጊዜ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደርና በአፋር ክልል ውስጥ የነበሩት ጦርነቶች ለረጅም ጊዜ የቆዩ አልነበሩም።

ነገር ግን በሰሜ እና በደቡብ ወሎ ያለው ጦርነት ግን እየተጣናከረና እየተቀዛቀዘ እስካሁን ዘልቋል። በዚህም ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ግጭቱን በመሸሽ በተለይ በደሴ ከተማ ተጠልለው ቆይተዋል።

አሁን በደሴ ከተማ ያለው ሁኔታ በውል አለመታወቁ ከነዋሪወቹ ባሻገር ተፈናቅለው በችግር ላይ የሚገኙትን ሰዎች ለከፋ ሰቆቃ ሊዳርጋቸው እንደሚችል ተሰግቷል።

BBC Amharic

Leave a Reply