የአዲስ አበባ ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን ስምና ማንነት ይፋ ሳያደርግ እንዳስታወቀው ከሆነ በአዲስ አበባ ሁለት ስፍራዎች ከባድ የሚባል መሳሪያ ሲያዘዋሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
በቂርቆስ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በተሸከርካሪ ጭነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 3 ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ያስታወቀው። ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው የተያዘው ከትናንት በስቲያ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ለገሀር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

ከሸዋ ሮቢት ተነስቶ መዳረሻውን አዲስ አበባ መሳለሚያ ሊያደርግ የነበረው ኮድ 3 A 21299 አ/አ አይሱዙ ተሽከርካሪ በተሽከርካሪው መፍቻ ማስቀመጫ የብረት ሳጥን በኩል ሻግ በማሰራት ሶስት መትረየሥ ጠብ-መንጃ ከመሰል አንድ ጥይትና ባዶ የጥይት ማስቀመጫ ዝናር ጋር ጭኖ ተገኝቷል፡፡
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ብርቱ ክትትል ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው፣ ተሽከርካሪው እንዲሁም 2 ተጠርጣሪዎችን ይዞ አስፈላጊውን ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው መሳለሚያ እህል በረንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በኮድ 1 34301 አ/አ ላዳ ታክሲ በማዳበሪያ ተፈታቶ የተቀመጠ 1 ኤስኬኤስ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውር የነበረ አሽከርካሪ ተይዞ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በሀገርና በህዝብ ላይ የሚያደረሰውን ጉዳት በመገንዘብ ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮች ሲመለከት ለህግ አካላት እንዲጠቁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡