የሽብር ወንጀልና የሚያስከትለው ተጠያቂነት

 1. መግቢያ
  የሽብር ድርጊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘ አንድ ወጥ ትርጉም የሌለው በመሆኑ በተለያዩ ሀገራት የድርጊቱ አረዳድ ላይ ልዩነት ይስተዋላል፡፡ በአንዱ አገር የሽብር ተግባር የሆነው ድርጊት በሌላው እንደ የነፃነት ትግል ሆኖ ይቆጠራል፤ በአንዱ የነፃነት ትግል ተደርጎ የሚታየው ተግባር በሌላው የሽብር ተግባር ሆኖ ይታያል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በዓለም ሰላም እና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ከሆኑ እና ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ከሚገኙ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ስለመሆኑ ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ወንጀሉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሀገራት በተናጠል እና በጋራ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሀገራችንም በተለያዩ ጊዜያት የወንጀሉ ሰለባ የነበረች ሲሆን ወንጀሉን ለመከላከል ህግ ማዕቀፍ ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዳለች፡፡ ከዚህ አንፃር የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ማውጣት አንዱ እርምጃ ሲሆን በአዋጁ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመቅረፍ አዋጁ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ሆኖ ተሻሽሎ ወጥቷል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ስለ ሽብር ምንነት፣ የሚያስከትለዉ ጉዳት፣ ወንጀሉን ለመከላከል ያለዉ ዓለም ዐቀፍና ሀገር አቀፍ ህጎች እና የወንጀሉ የሚያስከትለው ተጠያቂነት ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

 1. የሽብር ወንጀል ምንነት፣ የሚፈፀምበት ዓላማ እና የሚያስከትለው ጉዳት
  ሽብር የሚለው ቃል የተሰጠ ወጥ ትርጉም ባይኖርም ከብዙ ሀገራት ህጎች መረዳት የሚቻለዉ አንድን ርዕዮት ዓለም፣ የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት አስተሳሰብ በሕዝብ ወይም በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ወይም ለማሳካት ኃይልን በመጠቀም በዜጎች ላይ ፍርሃትን በመፍጠር የማይፈልጉትን እንዲቀበሉ የማድረግ ተግባር ነዉ፡፡ ከዚህ የምንረዳው ከሌሎቹ ወንጀሎች በተለየ መልኩ የድርጊቱ ፈጻሚ ድርጊቱን ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በሌላቸው ንጹሃን ሰዎች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ባለሥልጣኖች፣ ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ወታደራዊ ተቋማት ወዘተ ላይ በመፈጸም ሌላኛው ወገን መንግሥትና ሕዝብ እንዲገደድና ሃሳቡን ወይም አስተሳሰቡን እንዲቀበል ለማድረግ የሚፈጸም ተግባር መሆኑን ነው፡፡ ሌሎች ወንጀሎች ግን የሚፈፀሙት ቀጥታ ግንኙነት ባለው አካል ላይ ነው፡፡
  የሽብር ወንጀል መሠረታዊ ዓላማ ሲታይ ወንጀሉ የሚፈፀመው የፖለቲካ፤ የሐይማኖት ወይም የአይዲዮሎጂ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ ነው። ከዚህ አንፃር በሀገራችን ህግ መሰረት የሽብር ድርጊት ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ አገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ በሚል በሰው ወይም በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ መሆኑ ተገልፆል፡፡ ይህም በአዋጅ ቁጥር 1176/2012 በአንቀፅ 3 ላይ እንደተገለጸው ለሁለት ዓላማ ማለትም የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ እና ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ አገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን የማስገደድ አላማ ነው።

የሽብር ወንጀል የተለያዩ ጉዳቶችን የሚያስከትል ሲሆን በአብዛኛዉ በንብረት ወይም አገልግሎት ጉዳት የሚያድርስ፣ የሰውን ህይወትን የሚያጠፋ፣ በታሪካዊ ወይም የባሕል ቅርስ ወይም የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ነው፡፡ እንዲሁም የህዝብ አገልግሎትን ያስተጓጉላል፡፡

 1. የሽብር ወንጀል ታሪካዊ ዳራ
  የሽብር ወንጀል ጽንሰ ሃሳቡ ሲታይ በአብዛኛዉ ቃሉ ሽብርተኝነት (terrorism) በሚለው ቃል ቢገለፅ ይታያል፡፡ ይህ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ አብዮት ወቅት (እ.ኤ.አ መስከረም 1793- ሐምሌ 1794) የተገኘ ቃል እንደሆነ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ወቅት የፈረንሳይ የአብዮታዊ አስተዳደሩ የአብዮቱ ጠላት ናቸው በሚል በሚጠረጠሩ ዜጎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዙን እና ንጉስ ናፖሊዮን የስፔንን መውረር ተከትሎ ሕዝባዊ አመጽ መቀስቀሱንና የሽምቅ ተዋጊዎች መስፋፋትን መሰረት በማድረግ ሽብርተኝነት የ18ኛው ክፍለ ዘመን ክስተት አድርገው ያስቀምጣሉ፡፡

ወንጀሉ በተለያዩ ሀገራት ቅርጽና ይዘቱን እየቀያየረ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ቁሳዊ፤ ማህበራዊ እንዲሁም ሀይማኖታዊ ጉዳቶችን እያስከተለ እስካሁን የቀጠለ ጉዳይ ነዉ፡፡ በቅርቡ እንኳ እ.ኤ.አ ከ1990 ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የተለያዩ የውሳኔ ሀሳቦችን ከማሳለፍ ባለፈ፤ ሊብያ፣ ሱዳን እና አፍጋንስታንን ሽብረተኛን ይደግፋሉ በሚል የውሳኔ ሀሳብ በማስተላለፍ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥሎባቸዋል፡፡

ሌላዉ በዓለም ላይ አስደንጋጭ ክስተት የነበረው የአሜሪክ መንትዮች ህንጻ ላይ ከተፈጸመበት ከ2001 ጀምሮ ያለው ጊዜን ይመለከታል፡፡ በ2001 ዓ.ም በአሜሪካው ላይ የተፈጸመው ጥቃት ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ አገራት በሽብርተኝነት ላይ ያላቸውን አቋም እንዲፈትሹ ከማድረጉ ባለፈ ጠንካራ የህግ ማስፈጸም ስራ እንዲያከናውኑ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ክስተት አገራት ድርጊቱን ለመቆጣጠር ቀድሞ የነበራቸውን አጠፋዊ ምላሽ ስትራቴጂ ወደ ቀድሞ መከላከል እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል፡፡ የጸጥታው ምክር ቤትም አልቃይዳን ትኩረት ያደረገ የሽብር መከላከል ትኩረትን በመተው ሁሉን አቀፍ የሽብር ወንጀል መካለከል ላይ እንዲያተኮር፣ ሽብር የዓለም አቀፍ ደህንነትና ሰላምና ደህንነት ስጋት እንደሆነ በመቀበል ሁሉም አባል አገራት ድርጊቱን ወንጀል በማድረግ እንዲደነግጉ እና የህግ ማስፈጸም ስርዓታቸውን እንዲያጠናክሩ አቅጣጫ በማስቀመጡ በተለይ አባል ሀገራት ሽብር ህግ እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል፡፡

 1. ወንጀሉን ለመከላከል የሚያስችል አለም አቀፍ የህግ ማዕቀፍ
  የሽብር ወንጀል በየትኛዉም ሀገርና ዜጎች ላይ ሊፈጸም የሚችል ወይም የሚፈጸም ዉስብስብንና አስከፊ ወንጀል ነው፡፡ ይህ ማለት የሽብር ወንጀል ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች (Transnational Organized Crime) ከሚባሉት ዉስጥ አንዱ ነዉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሽብር ድርጊትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በተለያዩ ጊዜ የውሳኔ ሃሳብን አስተላልፏል፡፡ ድርጅቱ እራሱን የቻለ ሁሉን አቀፍ የሽብር ድርጊት መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል ዓለም አቀፍ ስምምነት ከማውጣት ይልቅ በጉዳይ የተነጣጠለ የውሳኔ ሃሳብ ሲያስተላልፍና ስምምነቶች እንዲወጡ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ወጥ የሆነ የህግ ማዕቀፍ አለመኖር በወንጀሉ ዙሪያ ያለው አረዳድ የተለያየ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ እነዚህ ስምምነቶች ሀገራት የሽብር ድርጊትን ለመከላከልና ለመቅጣት ህግ ማውጣት እንዳለባቸዉ፣ ለአፈጻጸሙም ትብብር ሊኖር እንደሚገባ እና ልዩ ትኩረት የመስጠት ግዴታ እንደተጣለባቸው ያስረዳሉ፡፡
 2. የሽብር ወንጀል እና የሚያስከትለው ተጠያቂነት በኢትዮጵያ ህግ ስርዓት
  በአገራችን በተለያየ ወቅት የሽብር ድርጊቶች የተፈፀሙ ሲሆን በ1970 ዎቹ ሲፈጸም የነበረው የቀይ ሽብርና የነጭ ሽብር ድርጊት በአገራችን በዜጎች ላይ ከፍተኛ ስጋትን ከፈጠሩ ሁኔታዎች ውስጥ የሚመደብ ነዉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ 1990 ዎቹ በትግራይ ሆቴል፣ በአክሱም ሆቴል፣ በጊዎን ሆቴል እና በድሬ ደዋ በራስ ሆቴል እንዲሁም በ2000 ዓ.ም በታክሲ ላይ በተፈጸመ ጥቃት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በሀገራችን በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ የሽብር ወንጀልን መከላከል እና ለመቅጣት ጥረት የተደረገ ሲሆን ወንጀሉ ካለዉ አስከፊ ባህሪ በ2001ዓ.ም ራሱን የቻለ አዋጅ ቁጥር 652/2001 ሊወጣ ችሏል፡፡ ነገር ግን አዋጅ ቁጥር 652/2001 መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶችን የሚገድብ ሆኖ በመገኘቱ በአዋጅ ቁጥር 1176/2012 እንዲተካ ተደርጓል፡፡

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ 1176/2012 አንቀጽ 3 መሰረት የሽብር ድርጊት ማለት፡-
1) ማንኛውም ሰው የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ አገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ፡- ሀ) በሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤ ለ) የሰውን ሕይወት ለአደጋ ያጋለጠ፤ ሐ) ሰውን ያገተ ወይም የጠለፈ፤ መ) በንብረት፣ በተፈጥሮ ሐብት ወይም አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤ ወይም ሠ) የሕዝብ ወይም ማህበራዊ አገልግሎት እንዳይሰጥ በከፍተኛ ሁኔታ ያስተጓጎለ እንደሆነ ከአስር ዓመት እስከ አስራ ስምንት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡

2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተጠቀሰውን አላማ ለማስፈጸም የተፈጸመው ተግባር ሰውን መግደል ወይም በታሪካዊ ወይም የባሕል ቅርስ ወይም የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ እንደሆነ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ መሆኑን ደንግጓል፡፡

በአዋጁ ከአንቀጽ 3 ውጭ ያሉ የሽብር ወንጀሎች፡-

 1. መዛት፡- በአዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 5 መሰረት ከላይ በአንቀፅ 3 ስር የተገለፀውን የሽብር ወንጀል ለመፈፀም መዛት ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ሊደርስ በሚችል ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ተግባር ተደርጎ ተደንግጓል፡፡ ዛቻ የፈጸመው ሰው አደርገዋለሁ ያለውን ድርጊት ለማድረግ ለመፈጸም ያለው አቅም፣ ዕድል ወይም በሌላ ሰው የሚያስደርግ ከሆነ ይህንን ለማድረግ አቅም ያለው መሆኑ ወይም በመዛቱ ምክንያት ህብረተሰቡ ወይም የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል የተሸበረ ወይም ሽብር ሊፈጥር የሚችል መሆኑን በመመዘን ነው፡፡
 2. ማቀድና መሰናዳት- የሽብር ድርጊትን ለመፈጸም ማቀድና ማሰናዳት በራሱ የሚያስቀጣ ተግባር ሲሆን በሁለቱ መካከል ግልጽ ወሰን ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ የአዋጅ ቁጥር 1176 አንቀጽ 6 በአዋጁ አንቀጽ 3 የተመለከተውን ድርጊት ለመፈጸም ማቀድና መሰናዳት የሚያስቀጣ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ድንጋጌው ለማቀድ ከሶስት እስከ ሰባት ዓመት እንዲሁም ለመሰናዳት ከአምስት እስከ አስራ ሁለት ዓመት የሚያስቀጣ ስለመሆኑ ያስቀምጣል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 6 ማቀድ ማለት በአዋጁ አንቀጽ 3 የተመለከተውን የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ከሀሳብ ባለፈ ወንጀሉን ለመፈጸም የሚፈጸምበትን ሁኔታ፣ ቦታ፣ ጊዜ ወይም መሰል ጉዳዮችን የመለየት ወይም የመወሰን ጉዳይ እንደሆነ ትርጉም ያስቀምጣል፡፡ ኢትዮጵያ የፈረመችው የአፍሪካ ህብረት የሽብር መከላከልና መቆጣጠር ኮንቬንሽን ማቀድ የሚያስቀጣ ተግባር ሆኖ እንዲካተት የሚያስቀምጥ ከመሆኑ አንጻር ማቀድ በአዋጁ ውስጥ ተካቷል፡፡
 3. ማደም ማለት ሁለትና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም የተስማሙ እንደሆነ ስለመሆኑ ከወንጀል ህጉ አንቀጽ 38 ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡ በአዋጁ የሽብር ወንጀልን ለመፈጸም ማደም ከአምስት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት ድረስ ሊያስቀጣ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ማደም ከማቀድ እና መሰናዳት ለየት የሚያደርገው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ሁለትና ከዛ በላይ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሰዎች ድርጊቱን ለመፈጸም የተስማሙ መሆኑን የሚጠይቅ ነው፡፡ ስምምነት መኖሩ በማስረጃ መረጋገጥ ያለበት ሲሆን በግልጽ ወይም በተዘዋዋሪ በሰዎቹ መካከል ስምምነት ለመኖሩ የሚያስረዳ ሁኔታ ካለ አድማ ስለመኖሩ ለማረጋገጥ በቂ ይሆናል፡፡
 4. በሐሰት ማስፈራራት- በሽብር ድርጊት በሀሰት ማስፈራራት በቀላል እስራት ወይም ጉዳት ያስከተለ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 8 ላይ ተደንግጓል፡፡ በሀሰት ማስፈራራት በሽብር ህግ ውስጥ እንዲካተት የተደረገበት ዋና ምክንያት ሰዎች በዘፈቀደ የሽብር ጥቃት እንደሚያደርሱ በመግለጽም ሆነ በማስመሰል ዜጎችን ለአደጋ እንዳያጋልጡ ማድረግ ነው፡፡
 5. ድጋፍ ማድረግ፡- ወንጀሉን የሚፈፅም ሰው መርዳት ከሰባት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ድርጊት ሆኖ በአዋጁ አንቀጽ 9 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የድጋፍ ዓይነቶችን ስንመለከት የሽብር ወንጀል አፈጻጸምን ለመርዳት በማሰብ ሰነድ ወይም መረጃ ማዘጋጀት፣ ማቅረብ፣ መስጠት፣ የምክር አገልግሎት፣ የሙያ ድጋፍ፣ ጉዳት ማድረስ የሚችሉ መሳሪያ፣ ኬሚካሎች ወይም ንጥረ-ነገሮች ያዘጋጀ፣ ያቀረበ የሰጠ ወይም የሸጠ ድጋፍ እንዳደረገ ይወሰዳል፡፡
 6. ማነሳሳት፡- አንድ ሰው ሌላው ሰው የሽብር ድርጊት እንዲፈጽም ለማድረግ በመጎትጎት፣ ተስፋ በመስጠት፣ በገንዘብ፣ በስጦታ፣ በማስፈራራት ወይም በማናቸውም ሌላ መሰል ዘዴ ያነሳሳ እንደሆነ ለድርጊቱ በአንቀጽ 3 ላይ በተቀመጠው ቅጣት እንደሚቀጣ በአንቀጽ 10(1) ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ድጋፍ ከማድረግ የሚለየው ድርጊቱን የሚፈጽመው ሰው በራሱ ፍላጎት የሚፈጽመው ሳይሆን ማነሳሳት በፈጸመው ሰው ምክንያት ሲሆን ድጋፍ ማድረግ ደግሞ ወንጀል አድራጊው ሀሳብ ያለው ሆኖ ድጋፍ የሚያደርገው ሰው የድርጊቱ ፈጻሚ ሀሳቡን እንዲያሳካ ማመቻቸት ወይም አስተዋጽዎ ማበርከትን የሚመለከት ነው፡፡

በአጠቃላይ የሽብር ወንጀል ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል አስከፊነት ድርጊት ነው፡፡ ድርጊቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሀገራችን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፣ በመወሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይበልጥ ወንጀሉን ለመከላከልና ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እንዲሁም ወንጀሉ ተፈፅሞ ከተገኘ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተለይ የህግ አስፈፃሚ የተቋማትና የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት ወሳኝ ጉዳይ ነዉ፡፡ ህብረተሰቡም ወንጀልን በመከላከልና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለህግ እንዲቀርቡ ከማድረግ አንፃር እገዛ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡

Attorney general

Leave a Reply