አሸባሪን በመደግፍ በ1 ራስ 2 ምላስ የሆኑት አሜሪካና አጋሮቿ

የዴሞክራሲ ሰባኪ ነን የሚሉት አሜሪካና አጋሮቿ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ሊያስተካክሉት እየሞከሩ ነው ሲሉ በካናዳና እንግሊዝ የሚገኙ 2 የፖለቲካና ፀጥታ ተመራማሪዎች ገለፁ፡፡

በእንግሊዙ ዊልፍሪድ ዩኒቨርሲቲ የዓለም ዐቀፍ ፀጥታ ጉዳዮች ፕሮፌሰሯ አን ፊትዝ ግራልድ እና የካናዳ ምክር ቤት የፀረ ሽብርተኝነት ልዩ ኮሚቴ የቀድሞው ሊቀመንበር እንዲሁም የካናዳው ኪዩንስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም ዐቀፍ ፖሊሲ ተመራማሪው ሁህ ሴጋል በጋራ ባወጡት ሰፊ ሐተታ ነው ይህን ያሉት፡፡

የሁለቱ ተመራማሪዎች ጽሑፍ 78 አገራት በኮቪድ-19 ምክንያት ምርጫን ሲያራዝሙ ዓለምም ይህንኑ ይደግፍ ነበር በማለት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በወረርሽኙ ምርጫ ሲያራዝም ግን የሽብር ቡድኑ ሕወሓት በትግራይ ምርጫ በማድረግ ሕግ መጣስና ጦር መስበቅ መጀመሩን ያስታውሳል፡፡

የሕወሓት የበላይነት የነበረበት የ27 ዓመታት አገዛዝ ለማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮት የታመነና እጅግ ጨቋኝ እንደነበር፤ ይህም አሜሪካ ቆሜለታለሁ ከምትለው እሳቤ ጋር ተቃራኒ እንደነበር ሁለቱ ተመራማሪዎች በጽሑፋቸው ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም ዴሞክራሲያዊት ነኝ የምትለው አሜሪካ ግን በወቅቱ ከሕወሓት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበራት፡፡

የሽብር ቡድኑ የዛሬ ዓመት በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ጦርነቱን እንደጀመረ በማስታወስም ከኔቶ አባል አገራት አንዱ ላይ መሰል አደጋ ቢደቀን በሁሉም ዘርፍ ተባብሮ ለመፋለም ጥያቄ የሚያነሳ አለወይ? የሚሉት ተመራማሪዎቹ በኢትዮጵያ ላይ ሽብርተኛን መዋጋት ወንጀል የሆነበትን ሚዛን ይተቻሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሽብርተኛ የተባለውን ሕወሓት ግን አንዳንድ አገራት ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨትና የሳተላይት መረጃዎችን በመስጠት ጭምር ድጋፍ እያደረጉለት መሆኑን በመጥቀስም ተቃውመውታል፡፡

የሽብር ቡድኑ የመከላከያ ሰራዊትን ባጠቃ ሰዓታት ልዩነት መልሶ ‹መንግሥት በትግራይ የዘር መጥፋት ፈፀመ› ብሎ ሲከስ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ጸሐፊዎቹ በተጨማሪም መንግሥትና ኢትዮጵያዊያን የሽብር ቡድኑ በፈጠረው ሰብኣዊ ቀውስ 70 በመቶውን የሰብኣዊ ድጋፍ ለክልሉ እያቀረቡም ቡድኑ መንግሥትና ሕዝብን ይወቅሳል ሲል ከእውነት የተፋታውን መሰረተ ቢስ ውንጀላ ውድቅ ያደርጉታል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽንና በተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በጥምር የተደረገው ምርመራ ትናንት ይፋ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት የዘር ማጥፋት አለመፈፀሙንም ሆነ ፆታዊ ጥቃትና ሰብኣዊ እርዳታን እንደጦርነት መሳሪያ አለመጠቀሙን ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡

አሜሪካና ሌሎች አገራት በምርጫ መሳተፍ ከሚችለው አጠቃላይ ሕዝብ 80 በመቶው ሕዝብ የተሳተፈበትን የሰኔና መስከረሙን ምርጫ እየተመለከቱም የኢትዮጵያን መንግሥት ሲተቹ ይውላሉ የሚለው ሐተታው ምርጫው ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ግልፅነት የታየበት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይህን ደግሞ 100 ሺሕ የአገር ውስጥ ምርጫ ተቆጣጣሪዎችና 100 ዓለም ዐቀፍ ታዛቢዎች ማረጋገጣቸውን ያሰምርበታል፡፡

ሐተታው በዚህ መንገድ ያሸነፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ና ፓርቲያቸው ብልፅግና ግን የዴሞክራሲ መምህር ነን ከሚሉ የምዕራባዊያን አገራት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትን በሚጠበቀው ልክ አለማግኘታቸውን ጠቅሶ የዓለም ዐቀፉን ማኅበረሰብ ድብቅ ፍላጎት ይጠይቃል፡፡ የሆነው ሆኖ ምዕራባዊያን የራሳቸውን አቋም ጥያቄ ውስጥ አስገብተውታል ሲሉ ሁለቱ ተመራማሪዎች ሴራውን ገልጠዋል፡፡

በዚህም የተወሰኑ የዓለም መሪዎች የምርጫ ውጤት ለሆነው የኢትዮጵያ ሕጋዊ መንግሥት እያሳዩት ያለው ቸልተኝነት ከ100 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያንን ድምፅ ካለማክበር በዘለለ በየአገራቱ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎችን ቸል ማለት ነው ሲልም ጽሑፉ ይተቻል፡፡

ይልቁንም ምዕራባዊያን አሸባሪው ሕወሓት እየፈፀመ ያለውን የሽብር ድርጊት እንዲያቆም መጠየቅ አለመቻላቸው የቡድኑ ደጋፊነታቸውን እና ለሚሉት ዴሞክራሲያዊ እሴት እንደማይታመኑ ማሳያ ነው ሲሉ ይተቹታል፡፡

ይህን ማድረግ ተስኗቸው በኢትዮጵያና በሕጋዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥት ላይ ዱላ ማበርታትን እንደመረጡም ጠቅሰው ተመራማሪዎቹ አውግዘውታል፡፡

የአሜሪካና አጋሮቿ አሸባሪ ቡድንን ከሕጋዊ መንግሥት ጋር የማስተካከል አካሄድ ራሳቸው ከሚሉት የዴሞክራሲ እሴት የተናጠለና በአንድ ራስ ሁለት ምላስነታቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ እንደሆነ ጽሑፉ ያሰምርበታል፡፡

ጥቅምት25/2014 (ዋልታ)

Leave a Reply