ትህነግ በአማራ ክልል በወረራቸው አካባቢዎች ከ279 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሃብት ውድመት አድርሷል

አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ወረራ በፈፀመባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከ279 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ የሀብት ውድመት ማድረሱን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አንሙት በለጠ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት አሸባሪው በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል።

አሸባሪው ህወሀት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለችግር እንዲጋለጥ ያደረገ ሲሆን 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብን ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬው አፈናቅሏል።

በተጨማሪም እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ ውሃ፣ መስኖ፣ መንገድ ያሉ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም የፍትህ፣ የፖሊስና መሰል የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መዝረፉንና ማውደሙን ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገርም ንፁሃን ዜጎችን በጅምላ መግደሉን ጠቅሰው፣ የአርሶ አደሩን ሰብልና የቤት እንስሳትን ጭምር ማውደሙን አመልክተዋል።

ሃላፊው እንዳሉት የሽብር ቡድኑ ይሄን ያህል መጠን ያለው ጉዳት ማድረሱ የተረጋገጠው ወረራ በፈፀመባቸው የተለያዩ ዞኖች በሚገኙ 45 ወረዳዎች በተካሄደ ክልል አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ነው።

ዳሰሳ ጥናቱ አሸባሪው ለተወሰነ ጊዜ ቆይቶ በፀጥታ ሃይሉ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ በለቀቃቸው አካባቢዎች የተደረገ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ በአሸባሪው ህወሓት ተወረው የሚገኙ አካባቢዎችን እደማያካትት ገልፀዋል።

በጤናው ዘርፍ 1ሺህ 466 ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

አሸባሪው በ6 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እንዲሁም በ17 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ላይ ባደረሰው ጉዳትም 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሃብት መውደሙን ነው የገለጹት።

“እንዲሁም በመንገድ መሰረተ ልማትና በድልድዮች ላይ ባደረሰው ጉዳት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት አስከትሏል” ያሉት አቶ አንሙት፤ በመስኖ ተቋምትም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ሙሉ በመሉ ከጥቅም ውጭ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

እነዚህ ከላይ ለማሳያ ይቅረቡ እንጂ የሽብር ቡድኑ በግብርና፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በገንዘብ፣ በውሃ ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት፣ በንግድና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም የከፋ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል።

ለዝርዝሩ፡- https://www.ena.et/?p=150534

-አካባቢህን ጠብቅ

_ ወደ ግንባር ዝመት

_ መከላከያን ደግፍ

ባህር ዳር፤ ህዳር 2/2014 (ኢዜአ)

Leave a Reply