“ ስለ ሠራዊቱ የጦር ሜዳ ውሎ የጁንታውን ምርኮኞች ምስክርነት መስማት በቂ ነው” ብ/ጄ ተስፋዬ ረጋሳ

– ሠራዊቱ በተሳካ ሁኔታ ግዳጁን እየፈጸመ ይገኛል- ብ/ጄ ተስፋዬ ረጋሳ

በወሎ ግንባር የተሰለፈው የአገር መከላከያ ሰራዊት ግዳጁን በተሳካ ሁኔታ እየፈጸመና በጠላት ላይ ድል እየተቀዳጀ መሆኑን ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ገለጹ።

በወሎ ግንባር ከሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አዛዞች አንዱ የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ እንደሚሉት፥ ሠራዊቱ አሁን ላይ የተሳካ የግዳጅ አፈጸጸም ላይ ይገኛል።

አዛዡ አክለውም ሠራዊቱ አገሩን እያሰበ በእልህና በወኔ፥ ለህዝብና ለአገር ሰላም እና መረጋጋት ከጠላት ጋር እየተፋለመ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አሁን ላይ የሰራዊቱ የግዳጅ አፈጻጸም ስኬታማ ነው ያሉት አዛዡ፥ “ስለ ድሉ እኛ ከምናወራው ይልቅ የሠራዊቱ የጦር ሜዳ ውሎ እና የጁንታው ምርኮኞችን ምስክርነት መስማት በቂ ነው” ብለዋል።

የህዝቡ ደጀንነት ከቃላት በላይ ነው ሲሉ የገለጹት አዛዡ፥ በተለይም ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያለው ህብረተሰብ ከልጅ እስከ አዋቂ ግንባር ድረስ በመምጣት አጋርነት እያሳየ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ሠራዊቱ ከህዝቡ የተቀበለውን አደራ ሳያጓድል ጁንታውን አአስወግዶ የህዝቡን ፍላጎት ያሳካል፤ ለዚህ ደግሞ ህዝቡ ቅንጣት ታክል ሊጠራጠር አይገባም ነው ያሉት ጀኔራል መኮንኑ።

“ከህዝቡ የተቀበልነውን አደራ እናሳካለን” ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ፥ ጁንታው የወገንን መሬት ዳግሞ እንደማይረጋጥ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ሠራዊታችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የጁንታውን ወራሪ ሃይል ደምስሶ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ያረጋግጣልም ነው ያሉት።

በተመሳሳይ የግንባር ዜና

ደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ይርጋ ሲሳይ በተለይ ለአሚኮ እንደገለጹት ጠላት ከሰሞኑ በዳውንት መስመር አድርጎ በታች ጋይንት ወረዳ በኩል ቆርጦ ለመግባት ሙከራ አድርጓል።

ይሁን እንጂ ሕዝቡንና የታጠቀውን ሃይል በማነቃነቅ የጠላትን እንቅስቃሴ መገደብ እንደተቻለና ጠላትም ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን ነው አቶ ይርጋ የተናገሩት።

የወገን ጥምር ጦር በቅንጅት ባካሄዱት ውጊያ ከፍተኛ ድል ማስመዝገባቸውን ጠቅሰው፥ በዚህም የወገን ጦር ገዢ ቦታዎችን መያዝ ችሏል ብለዋል።

የአካባቢውን መልክዓምድራዊ ምቹነት በመጠቀምና ከሌሎች ግንባሮች ጋር በመናበብ የሚጠበቅብንን እያደረግን ነው ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪ ጥሩ ውጤት እየተገኘ እንደሆነ አመላክተዋል።

በውጊያው የታች ጋይንት ወረዳ ሕዝብ ደጀንነት በተለየ መልኩ ጠንካራ እንደሆነ በማንሳትም ወጣቶች እና አርሶ አደሩ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያደርገው ትብብር በግንባሩ የሚገኘው ውጤት በሚፈለገው መልኩ የተሳካ እንዲሆን አድርጎታልም ነው ያሉት።

የፖለቲካ መሪዎች እና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች መስዋዕትነት ለመክፈል ከፊት በመሰለፍ የማስተባበር፣ የማዋጋት፣ የመዋጋት እና የመምራት ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ እንደሆነም ነው የገለጹት።

የህልውና ትግሉን ለሠራዊቱ ብቻ አንሰጥም ያሉት አስተዳዳሪው ጠላትን ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ መሪዎች እና ሕዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት እየተፋለሙ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።

የስንቅና የትጥቅ አቅርቦቱም በተገቢ መልኩ እየቀረበ ነው ብለዋል።

FBC

Leave a Reply