ደሃ ጋላቢ ዘንዶዎች ሲፎክሩ “ያለቀው አልቆ ስልጣን”

ይህ ጊዜ አልፎ የደሃ ጋላቢ ዘንዶዎች ገበና ሲገለጥ ምንኛ ጉድ ይባል ይሆን? የፈሰሰው ደም፣ የተጨፈጨፉ ዜጎች ቁጥር ከጓዳ ወደ አደባባይ ሲወጣ ማን ይሆን ሂሳቡን የሚከፍለው? ምንስ ምክንያት ይቀርብለት ይሆን? ዛሬ በተራ የዘንዶው መንፈስ፣ በብሄር ካቲካላ የሰከሩ ሲሰክኑ ምን ይሉ ይሆን? ዛሬ በዚሁ የጎሳ አረቄ ሰክረው የሚተፉ የዛኔ እንዴት ይልሱት ይሆን? ደሃ ጋላቢዎችና የጅምላ አጫፋሪዎች እባካችሁን ከደሃ ጫንቃ ውረዱ!!

ነጻ አስተያየት – ሰለሞን መንበሩ ድሬደዋ

በግልጽ ቋንቋ ሃዘኔታ የሚባል ነገር የነጠፈብን ሆነናል። የቁጥር ጨዋታው እንዳለ ሆኖ፣ ንጹሃንን ቀስቅሶ ለመማገድ ነዳጅ ይሆን ዘንድ “መቶ ሺህ፣ አስር ሺህ፣ አምስት ሺህ …. ጨፈጭፍኩ፣ አንተ ልዩ ጀግና ” እየተባለ የሚወጡት መረጃዎችን ተከትሎ የሚመታው አታሞ ልቦናችን መደንደኑን አመላካች ነው። ይኸው እልቂት ” ሰበር” እየተባለ የንጹሃን ደም ላይ ሳንቲም ለመልቀም በተሰለፉ ህሊና ቢሶች ( ሁሉም አይደሉም) ከዳር እስከዳር እንደ ኩራት ዜና ይሰራጫል።

ከዛም ከዚህም አንድ ሕዝብ፣ አንድ ወገን፣ የአንድ ማተብ ልጆች እንዲባሉና እንዲጫረሱ መርዝ ሲረጩ የኖሩ ምን ያህል ሰው ሲሞት፣ ምን ያህል ህጻናት ሲረግፉ፣ ስንት ሚሊዮን ሕዝብ ሲፈናቀል፣ ስንት እናቶች ሃዘን አንጀታቸው ዘልቆ ሲሞቱ … በጥቅሉ ምን ያህል ሊትር የደም ጎርፍ ሲጎርፍ ወደ ልባቸው እንደሚመለሱ እንኳን ሊታወቅ ምልክት ማየት አልተቻለም።

” ያለቀው አልቆ የተረፉት በሰላም የሚኖሩበት አግባብ እስኪፈጠር” ሲሉ አቶ ጌታቸው ጦርነቱ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በሳቸው አባባልና ሂሳብ ስንት ሞቶ ስንት እንደሚተርፍ፣ መቼ ሞቱ እንደሚያበቃ፣ መቼ የልባቸው ደርሶ ቀሪ የትግራይ ልጆች የገነት ኑሮ እንደሚኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም።

“በቀናት፣ ግፋ ቢል በሳምንታት ጦርነቱ ያልቃል” ተብሎ የሰው ልጅ እንደ ጉንዳን እየትግተለተለ የገባበት ጦርነት ” ተያዘ ተለቀቀ” ከሚለው ሰበር ዜና አልፎ በረጋ ልቦና ለሚመረምረው ከዛም ሆነ ከዚህ ስንት ረገፈ? መጫረሱ በዚህ ከቀጠለ ” ስንት ይተርፋል” የሚለውን መገመት መገመት፣ ለመገመት መሞከር አይታሰብም። መሪዎቹም ” የሞተው ሞቶ” ሲሉ ” በነካ አንድበትዎ ስሌቱን ያስሉልን” ብሎ ለመተየቀ የሚዳዳው የለም።

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አዲስ አበባ ገብቶ የሚፈልገውን ሃይል አስቀምጦ፣ የሚፈልገውን የማድረግ እቅድ እንዳለው አመልክቷል። የሽግግር መንግስትም እንደሚያቆም ተናግሯል። የሽግግር መንግስቱን ምልምሎችም አስተዋውቋል። ከአገር ቤት ከመሃል ያለው እውነታ ግን ይህን የሚፈቅድ አይመስለም። እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ መንግስት የሚወድቅ ስለመሆኑ ምልክት የለም። ይልቁኑም ሕዝብ እያመረረና ጦርነቱ ” ሕዝባዊ” ሆኖ የሕዝብ ማዕበል ወደ ግንባር በመትመም ላይ መሆኑ ነው እየታየ ያለው። ደጀኑም ሰለቸኝ ሳይል የአገር ዘቦቹን እየቀለበ፣ በሰው ሃይል እያገዘ፣ ወኒያቸውን እየጠገን እንደሆነ ነው የሚታየው። ይህ እውነት ነው።

ዶክተር ደብረጽዮን “የትግራይ ሕዝብ ሁሉ ወታደር ነው” በማለት እንዳስታወቁት ሁሉ ከዚህም ወገን በሚሊዮኖች ነፍጥ ይዘው አካባቢያቸውንና አገራቸውን ለመተበቅ እየተነሱ ነው። መረጃዎችና አደባባይ ላይ ያለው ሃቅ እንደሚያስረዳው አሁን ወደ ግንባር እየሄደ ያለው ጦር የሚዋጋው በቀዬውና በደጁ፣ በደጀኑና በአጋሩ መካከል ሆኖ ነው።

እንደሚሰማው ከሆነ መከላከያ የውጊያ ስልቱን ቀይሮ ደጀን ሕዝብን በመጠቀም ሽምቅ ማጥቃት ጀምሯል። ስም መዘርዘር ባይቻልም የግንባር ዜና የሃይል ሚዛንና የጉዳት መጠኑ ከቀድሞው በተለየ መልኩን ቀይሯል። እናም የትግራይ ልጆች ለምን ብለው ከሚሴ መጥተው፣ ኮምቦልቻ ገብተው፣ ደሴ ደርሰው፣ ቆቦ፣ ላሊበላ፣ ወልደያ፣ ዋጋ ምድር … ወዘተ ግብተው ባይተዋር ሆነው ያልቃሉ? ከዚህም ወገን የሚሞት ቢኖርም የሚብሰው ከደጀኑ በወጣው ላይ ነውና!!

አዲስ አበባን ይዞ መንግስት ለመሆን ወይም የሚፈልጉትን መንግስት ለመትከል ካልተቻለ ወይም የማይቻል ከሆነ የትግራይ ሕጻናት ደም ማን ያወራርደዋል? ሚሌን ለመያዝ ሁለት ሳምንት ሙሉ እጅግ ከባድ የተባለ ጦርነት ተካሂዷል። በጦርነቱ ጀትና ሄሊኮፕተር ተሳትፏል። ስንት ወጣት አለቀ? በከሚሴ በኩል በዳዌ ሚሌን ለመያዝ እጅግ የበዛ ሃይል የተሳተፈበት የከፋ ውጊያ ተካሂዷል። ስንት ሰው አለቀ? ስንት እናት ያለ ጧሪ ቀረች?

ጦርነት ክፉ ነው። ትህነግ ወደ ትግራይ ከሄደ ጀምሮ ዳግም ወደ መንበሩ ለመመለስ የፌደራል ሃይሎች ብሎ ዘመቻውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ እነ ሴኮ እንዳመኑት በአገር መከላከያ ላይ ጥቃት እስከፈጸመበት ቀን ድረስ በመላው አገሪቱ የሆነው ጥፋትና ዘግናኝ የሰው ልጅ እልቂት በውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይገባው ነበር? ማንም ይፈጽመው ማን፣ ኢትዮጵያዊያን በንዲህ ያለ የክፋት ጥግ ሲታረዱ፣ ሲፈናቀሉ፣ ሲረሸኑ፣ ሲታፈኑ፣ መማር አቅቷቸው ሲነክራተቱ ያሳለፉት ህይወት አንሶ ዛሬም በሚልዮኖች መፈናቀላቸው ምን ስለበደሉ ነው? የንፋስ መውጫ፣ የጋይንት፣ የኮምቦልቻ፣ የዋግ፣ የወልደያ፣ የቆቦ፣ የሺና፣ የጋሊሶማ አፋር… ምስኪን አፈር ገፊ ስለምን ይህ ሁሉ መከራ ይደርስበታል? በትግራይ በጦርነቱ ወቅት ተፈጸመ ለተባለ ህገወጥ ተግባር አጥፊዎች እንዲጠየቁ መስራት፣ መታገል፣ መዋደቅ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ሰላማዊ ሕዝብ ደጅ ድረስ እየሄዱ መጭፍጨፍ፣ መጨረስ፣ መዝረፍ፣ ማሳ ማጨድ፣ ሊጥ ማጋዝ፣ ዶሮ ማፈን፣ የጤናና የትምህርት እንዲሁም የልማት አውታር ማውደም በየትኛው የፍትህ ሂሳብ ልክ ይሆናል?

ይህ ስሜት አሁን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሕዝብ ማዕበል ፈጥሯል። አሁን ወደፊት የሚሆነው እስካሁን ከሆነው ጋር የሚወዳደር አይሆንም። የተራ ቀረርቶና የአጉል ምኞት ካልሆነ በቀር አሁን ላይ ያለው አያያዝ እንደ ቀደም ሳምንታት ወይም ወራት አልጋ በአልጋ የሚሆን አይመስልም። እልህ መጋባቱ ጣሪያ ነክቷል። ይህን ማሰብና አደጋውን ለመቀነስ መሞከር እንዴት አይቻልም? ምን እስኪሆን ነው የሚጠበቀው?

ትግራይ በወልቃይት በኩል አላት የሚባለውን ጥያቄ በህግ፣ በዓለም አቀፍ ደንቦች፣ ከምንም በላይ አብረው በሚኖር አንድ ሕዝብ ፍላጎት መፍትሄ እንዲያገኝ ሁሉንም ሰላማዊ አማራጮች አሟጦ መጠቀም እያለ፣ ከድሮውም ጀመሮ የተለያዩ የቅርጽና የአስተዳደር አወቃቀሮችን መተግበርን ጨምሮ ምሁራን መክረው አስታራቂ ሃሳብ እንዲያመጡ ባለመደረጉ የተፈጠረ ክፍተት መሆኑንን በመረዳት መስራት እየተቻለ እንዲህ ያለ መጫረስ ውስጥ መግባት ታሪካዊ ሃፍረት ነው።

ስጨርስ ትህነግ የአማራን ሕዝብ ጨፍጭፎ ሊጨርስ አይችልም። ይህ እውነት ነው። የትግራይ ሕዝብም ሊያልቅ አይችልም። ይህም እውነት ነው። ከሁሉም በላይ ትህነግ ኢትዮጵያን እንደአገር ሊረታ አይቻለውም። ሌላው ትህነግ ዳግም ወደ ስልጣን እንዲመጣ የሚፈቅድ ሕዝብ የለም። ምን አልባትም ከትግራይ ውጪ ትህነግ ቦታ የለውም። እና የትግራይ ሕዝብ፣ በተለይም ወጣቱ ከትግራይ ወጥቶ የሚማገደው ምን ለማግኘት ነው? የትግራይ ህዝብ ትህነግ እንደሚለው መገንጠል ከፈልገ ከከልሉ ወጥቶ ሳይሞት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ አድርጎለት የመገንጠል መብቱ ነው።

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ለትግራይም ሆነ ለማናቸውም የብሄረሰብ አካላት እኩል ክብር አለው። የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ተጨቁኖና በደል ደርሶበት ከሆነ ሌላ ቂምና ቁርሾ ሳይደርት፣ “የእስካሁኑ ይብቃ” ብሎ በግልጽ የመገንጠል ጥያቄውን ያንሳ። ሕዝብ ድጋፍ ያደርጋል። ግልጽ መነጋገሩ ወደ መፍትሄ ስለሚያመጣ መንግስትም ይህን ጥያቄ በግልጽ አስቀምጦ ትግራይን ፍላጎቷ ከሆነ ያሰናብት። ግማሽ ክፍለ ዘመን ከትግራይ በሚነሳ እሳት ኢትዮጵያ የምትለበለብበት ምክንያት ሊያበቃ ይገባል። አብሮ መሆንም ከትፈለገ በግልጽ መስመር ይበጅለት።

የማስረሻ ልጅ 49 ዓመቱ ነው። ከትግራይ በሚነሳ ጉዳይ፣ ትህነግ በሚያነሳው አጀንዳና ስልጣን ከያዘም ብሁዋላ መንበሩን ለማስጠበቅ ትህነግ ሲያድረስ በነበረው ጉዳት እድሜውን ሁሉ ሰላሙን እንዳጣ ይናገራል። አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ጭንቀት ውስጥ ገብቷል። ከልጅነት እስከ እውቀት በትህነግ አማካይነት እንደ እሱ የተማረሩ ትህነግ እንደስሙ ትግራይ ተሰጥታው ሌላው ክልል ስለማ እንዲሆን እንደ እሱ የታከታቸው ምንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ሲል በማህበራዊ ገጹ ጽፏል። እሱ እንደሚለው የትግራይ ሕዝብ ፍልጎት ከሆነ ህዝብ መንግስት ላይ ጫና ማድረጉን ካሁኑ መጀመር አለበ። ምክንያቱም ትግርያ በኢትዮጵያ ስድስት ከመቶ አስተዋጾ እንጂ የወሳኝነት ሚና የላትም። በቁመናዋ ልክ የማይበቃት ከሆን የሌሎችን የመቀማት ዓላማ ነውና ያላት ባስቸኳይ ፍቺ አድርጎ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሁሉም ወገኖች እነሱን ጨምሮ እፎይ ሊሉ ይገባል። ኢትዮጵያ የሚሉትን ሳያካትት!!

የማስረሻ ልጅ ያለውን ለማሳያ ያነሳሁት ስንት ሊትር ደም፣ ስንት ሚሊዮን ወይም ሺህ፣ ስንት እናት፣ ስንት አባት፣ ምን ያህል ንብረት፣ ስንት እንስሳ … አልቆ ነው ሰላም የሚሆነው የሚለውን ሳስብ ጫንጭሉን እንኳን ማየት ባለመቻሌ። አለቆቹም ፍንጭ ስለማይሰጡ ነው። እውነት ለመናገር ከደም ግብር በሁዋላ ላስፈጁት ሕዝብ ምን ስጦታ እንዳላቸውም መረዳት ስለማይቻል ነው። አንድ ሃቅ ቢኖር ሟቹ ብዙ፣ ተጠቃሚው ጥቂት መሆኑ ብቻ ነው። ሟቹ ደሃ፣ ተጠቃሚው ደሃን ጋላቢዎች መሆናቸው ነው። ይህ ደሃን የሚጋለብ የጥፋት ዘንዶ ይወጋ!!

Leave a Reply