አፋር«አሸባሪውን ቡድን እየተደመሰሰ ነው የማጥቃት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል»

በባቲ በኩል ሚሌን ለመያዝ የሞከረው አሸባሪው ህወሃት በተባበረ ክንድ እየተደመሰሰ ነው


የአፋር ልዩ ኃይል፣ሚሊሻና ሕዝቡ ከአገር መከለካያ ሰራዊት ጋር በመሆን በባቲ በኩል ሚሌን ለመያዝ የሞከረውን አሸባሪ ቡድን በተባበረ ክንድ እየደመሰሱት መሆኑን የካሳ ጊታ ግንባር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ገለጹ።

የካሳ ጊታ ግንባር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ መሓመድ ኑር ሳሊን፤ አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ በአፋር ክልል የኢትዮ- ጅቡቲን መንገድ ለመዝጋት በባቲ በኩል ሚሌን ለመያዝ ወረራ መክፈታቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም አሸባሪዎቹ በአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአፋር ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ሕዝቡ የተባበረ ክንድ እየተደመሰሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ መስመር ጠላት ሚሌን ለመያዝ በማሰብና የጅቡቲን መንገድ ለመዝጋት ላለፉት 13 ቀናት የማጥቃት ሙከራ ቢያደርግም በተቀናጀ መልሶ ማጥቃት ሳይሳካለት እየተመታ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም ጠላት ከባድ ኪሳራ እያስተናገደ ይገኛል ያሉት አቶ መሀመድ አሸባሪውን ቡድን የማጥቃት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኮማንድ ፖስቱ ምክትል ስብሳቢ መዲና መሓመድ ኢብራሒም፤ የአፋር ክልል የጸጥታ ሃይልና ሕዝቡ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ተቀናጅተው በመመከት ጠላት ድል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

‘ዳጉ’ በሚባለው የመረጃ መለዋወጫ መንገድ የአካባቢው ማህበረሰብ የጠላትን እንቅስቃሴ በመከታተል መረጃ እያደረሱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም የጸጥታ ሃይሉ የጠላትን ዱካ ተከትሎ በማሳደድና በመደምሰስ የጥፋት ምኞቱ እንዳይሳካ እያደረገው መሆኑን ምክትል ስብሳቢዋ ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ልዩ ሃይል ምክትል ኮማንደር እስማኤል አህመድ፤ ሕዝቡ ለጠላት ፕሮፓጋንዳ ሳይንበረከክ ጠላት በየገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በጀግንነት እየተዋጋ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠላት ብዙ ሰራዊት ያለውና ብዙ የታጠቀ አስመስሎ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ለማደናገር ቢሞክርም ሊሳካለት አልቻለም ብለዋል።

ይህም በመሆኑ የአፋር ሕዝብ፣ሚሊሻና ልዩ ሃይል ጠላትን በገባበት ሁሉ እየተከታተለ ለወሬ ነጋሪ እንኳን እንዳይተርፍ እያደረገው ነው ብለዋል።

በአውደ ውጊያው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የክልሉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የጸጥታ አካላት ጠላት ከገባበት እንዳይወጣ ባለበት እያስቀሩት መሆኑን ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

DONATE US – ቢረዱን አስፍተን ለመስራት አቅም ይፈጥሩልናል

About topzena1 2654 Articles
A journalist

Be the first to comment

Leave a Reply