በጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ግምጃ ተደብቆ የነበረ የጦር መሳሪያ ተያዘ፤ ከ8 ኪሎ በላይ ወርቅ ብር ግለሰብ ቤት ተገኘ፤

አራት ኪሎ በሚገኘው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ በንብረት ግምጃ ቤት ውስጥ የተቀመጡ ከ1 ሺሕ 800 በላይ ጥይቶች በሕዝብ ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ብርበራ ተያዙ፡፡ጥይቶቹ የተያዙት ረቡዕ ኅዳር 8 ነው፡፡

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለሽብር ተግባሩ የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ጭምር ሲያከማች እና በሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦችን በተላላኪነት እያሰማራ በበርካታ ንፁሃን ላይ አሰቃቂ እልቂት ሲፈፅም እንደቆየ ይታወሳል፡፡የአዲስ አበባ ፖሊስ የሽብር ቡድኑን ሴራ የተረዳው የከተማዋ ነዋሪ በተለያዩ ቦታዎች የሚመለከታቸውን አጠራጣሪ ጉዳዮችን ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እየሰጠ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብሏል፡፡በቤተ ክህነቱ ግቢ በሚገኝ የንብረት ግምጃ ቤት በሚገኝ የፅህፈት እና የፅዳት እቃዎች ማስቀመጫ ውስጥ በተደረገው ብርበራ የተገኙት 1ሺህ 363 የብሬን እና 493 የሽጉጥ ጥይቶች ናቸው፡፡በተጨማሪም 2 የጥይት ማስቀመጫ ሳጥኖች እና 1 የክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ካዝና ተይዟል፡፡ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 1 ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራ ሲሆን ሕብረተሰቡ በስልክ፣ በአካል እና ሌሎች የመገናኛ አማራጮችን በመጠቀም እየሰጠ የሚገኘው ጥቆማ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።

በሌላ የፖሊስ የምርመራ ዘና በአዲስ አበባ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ብርበራ ከ8 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅና የብር ጌጣጌጥ ተከማችቶ መገኘቱ በህዝብ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።

ዜናው እንዳለው በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ብርበራ ከ8 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅና የብር ጌጣጌጥ ተከማችቶ የተገኘው። ተጠርጣሪው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአንድ ንግድ አክስዮን ማህበር ስራ አስኪያጅና የሌላ ንግድ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ከመሆናቸው ውጭ በንግድ ሥራ የማይተዳደሩ ስለመሆናቸው የምርመራ መዝገባቸው ያስረዳል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከህብረተሰቡ የደረሰውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ የምርመራና የክትትል ቡድን አቋቁሞ ህዳር 7 ቀን 2014 ዓ.ም ግለሰቡን በቁጥጥር ስር በማዋል ቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን መኖሪያ ቤታቸውን እንዲያሳዩ ተደርጎ ፖሊስ ባደረገው ብርበራ ለጊዜው የዋጋ ግምታቸው ያልታወቀ አንድ ኪሎ ግራም ተኩል የወርቅና ስድስት ኪሎ ግራም ተኩል የብር ጌጣጌጥ ተከማችተው ተገኝተዋል፡፡

በኤግዚቢቱ ዙሪያ አስፈላጊው ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት ከመጠበቅ ባሻገር አጠራጣሪ ነገር ሲመለከት ለሚመለከተው የፀጥታ አካል በመጠቆም የዜግነት ኃላፊነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

You may also like...

Leave a Reply