” ነፍሴን ካወቅኩ ጀምሮ ግን እንደዚህ አይነት ድርቅ አይቼ አላዉቅም “

” ነፍሴን ካወቅኩ ጀምሮ ግን እንደዚህ አይነት ድርቅ አይቼ አላዉቅም ” – የ88 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው አቶ አብጃሀታኒ ሞሉ

• ” ምን እንደሚገጥመንም ፈጣሪ (ዋቃ) ብቻ ነዉ የሚያወቀው ” – ወ/ሮ ደቦ ዋቅቶላ

ወይዘሮ ደቦ ዋቅቶላ አካባቢቸውን ለቀው ወደ ሌላ ስፍራ ለስደት ከሄዱ አርብቶ አደሮችን መካከል ሲሆኑ ቀበሌያቸው በድርቅ በመጎዳቱ ለእንስሳቱ ዉሃና ሳር ለሰዉም የሚሆን ምግብ በመጥፋቱ እንስሳቶቹን እየነዱ ወደ ድሬ ወረዳ መሰደዳቸውን ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ኤፍ ኤም 91.5 ተናግረዋል።

ወ/ሮ ደቦ፥ ” ምን እንደሚገጥመንም ፈጣሪ (ዋቃ) ብቻ ነዉ የሚያወቀው ” ብለዋል፡፡

የ88 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው አቶ አብጃሀታኒ ሞሉ በበኩላቸው፥ ከዚህ በፊትም አልፎ አለፎ ድርቅ ይመጣል፣ ነፍሴን ካወቅኩ ጀምሮ ግን እንደዚህ አይነት ድርቅ አይቼ አላዉቅም ብለዋል።

” ከእኔ ብቻ 132 ከብቶች አልቀውብኛል ” የሚሉት እኚህ አባታችን ” አሁን ደግሞ እኔና በአካባቢዬ ያሉ ሰዎች እየተራብን ነዉ፣ በቦረና ሰማይ ላይ ደመናም አይታይም ስለዚህ ፈጣሪ፣ ህዝብና መንግስት ተረባርበዉ ካልደረሱልን እንኳን እንስሳት እኛም በረሀብ ልናልቅ ስለሆነ መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲረዳን ጥሪዬን አቀርባለሁ ” ብለዋል፡፡

በቦረና ዞን በድርቅ በተመቱት 5 ወረዳዎች ከሌሎች እንስሳት በተለየ መልኩ አህያዎች በራሳቸዉ ያሉበትን አካባቢ በመልቀቅ ደመና ወዳለበት እየጠፉ ሲሆን ይህም የተለመደ የአህያ ልዩ ባህሪይ በመሆኑ በርካታ አርብቶ አደሮች አህያዎቻቸውን ፍለጋ ተሰማርተዋል።

በቦረና ዞን በድርቅ በተመቱ አካባቢዎች በየቦታው የሞቱ እንስሳቶች ቅሪት ፣ በህይወት ያሉትም በጣም ተዳክመው አጥንታቸው ከቆዳቸው ጋር ተጣብቆ ይታያል።

ከሀዩ ኤፍ ኤም የተወሰደ።

Leave a Reply